Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

ሁለተኛ መልስ ለኢሳቱ አቶ ፋሲል – ግርማ ካሳ

$
0
0

ሁለተኛ መልስ ለኢሳቱ አቶ ፋሲል – ግርማ ካሳ
=============================

ጤና ይስጥልኝ፣ ዉድ ወንድሜ አቶ ፋሲል። «የአንድነት ፓርቲ የመጪው ጊዜ ፈተና» በሚል ርእስ በጻፉት ላይ ለሰጠኹት አስተያየት፣ ለአንባቢያን ያቀረቡትን የመልስ መልስ አነበብኩ። ግሩም አቀራረብና ለዉይይት የሚረዱ ነጥቦች በማንሳትዎ ተደስቻለሁ። ዜጎች የተለያዩ ሃሳቦች ሊኗራቸው ይችላል። ብዙ ጊዜ፣ በተለይም በዳያስፖራ ፖለቲካ የተለመደው ፣ የሃሳብ ልዩነቶች በተፈጠሩ ጊዜ ያኛው ወገንን ማገድ፣ መሳደብ፣ ወያኔ ነው ሆዳም ነው እያሉ መጥራት ነዉ። ብዙ ጊዜ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መልኩ የመወያየትና የመቻቻል ባህል አይታይም።

እርስዎም ላቀረብኳቸው ሃሳቦች አክብሮት በተላበሰ የኢትዮጵያዊ ጨዋነት ምላሽ ስለሰጡኝ ላመሰግንዎት እወዳለሁ። ሌሎች በራሳቸው አይን ላይ ያለውን ጉድፍ ማየት ተስኗቸው፣ እነርሱን አገር ወዳድ ሌላዉ ግን አገር አጥፊ አድርገዉ የሚወስዱ የዳያስፖራ ጸንፈኛ አክራሪዎች፣ ከርስዎ ትልቅ ትምህርት ይወስዳሉ ብዬ አስባለሁ።

ባለፈዉ ጽሁፉዎ አቶ ልደቱ አያሌው ነበሩ የተነሱት። በዚህኛው ደግሞ አቶ ኃይሉ ሻዉል እና ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ተነስተዋል። በቅድሚያ ስለ ወ/ት ብርቱካን ትንሽ ልበልዎት።

«ወ/ት ብርቱካን እስር ቤት ከገቡ በኋላ ፓርቲዋ ( አመራሩ) ረስቷት ነበር። እንዴያውም አንዳንዶች “እንኳን ታሰረች” ሳይሉ ሁሉ አልቀረም። ያን ጊዜ ማን ነበር ለብርቱካን አብዝቶ የጮኸው? ዲያስፖራው እና በተለይ ኢሳት አልነበሩምን? የካናዳው ልጅ ተክሌ ”ብርቱካኔ ብረሳሽ ቀኜ ይርሳሽ” ብሎ ዜማ ያወጣላት አምስተርዳም የኢሳት ስቱዲዮ ውስጥ ሆኖ ነው» ያሉት አባባል ትንሽ ቆረቆረኝ። እርግጥ ነዉ ወንድም ተክሌ ለወ/ት ብርቱካን መፈታት ብዙ ሲጽፍ እንደነበረ አውቃለሁ። ከብርቱካን ትፈታ ግብረ ኃይል ጋር ብዙ ሰርቷል። ነገር ግን ኢሳት፣ አሁን እርስዎ እንደሚሉት ለወ/ቷ መፈታት፣ ብዙ የአየር ሰዓት ሰጥቶ መታገሉን ግን አላስታወስም። የማላውቀዉን ስላሳወቁኝ አመሰግናለሁ።

«ወ/ት ብርቱካን ከታሰሩ በኋላ ፓርቲዋ ፣ አመራሯ ረስቷት ነበር» ያሉት አባባል ግን ከእዉነት የራቀ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ እርስዎ በጽሁፍዎ እያሞካሹት ያለው፣ እኔም የማከብረዉና የምወደው ወንድሜ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ የዚሁ «ብርቱካንን ረስቷል» ያሉት የአንድነት አመራር አባል እንደነበረም አይርሱት። የፓርቲዉ አመራር አባላት፣ ምን ያደርጉ እንደነበረ ብዙ መረጃ ያልዎት አልመሰለኝም። ምናልባት ያኔ ትኩርትዎት ከመረብ በስተሰሜን ስለነበረ ሊሆን ይችላል።፡«ተሳስቼ ከሆነ ሃሳቤን አወራርዳለሁ» እንዳሉ፣ ሃሳብዎትን ይመረምሩ ዘንድ፣ ከብዙዎች፣ ሶስት እዉነታዎችን ብቻ ልንገርዎት፡

1. በዳያስፖራ በቀዳሚነት ለብርቱካን መፈታት ሲታገል የነበረዉ፣ የብርቱካን ትፈታ ግብረ ኃይል ነበር። ይህ ግብረ ኃይል በየወሩ ለብርቱካን ቤተሰቦች የገንዘብ እርዳታ እንዲሰጥ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ዘመቻዎችን በሁሉም አቅጣጫዎች ይሰራና ይመራ የነበረ ነዉ። ከሊቀመንበሩ አቶ ግርማ ግዛው (አሁን የአንድነት ሰሜን አሜሪካ አመራር አባል) በስተቀር፣ የግብረ ኃይሉ ሌሎች አባላት ብዙም አይታወቁም ነበር።

ይህ ግብረ ኃይል እንዴት እንደተቋቋመ ልንገርዎት። ያኔ በአቶ አክሎግ ልመንህ የሚመራዉ የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ድርጅት፣ አዲስ አበባ ካለዉ የአንድነት ፓርቲ ጋር በመመካከር፣ «የብርቱካን ጉዳይ የፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ጉዳይ ነው» በሚል ነዉ፣ የብርቱካን ትፈታ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም የተደረገዉ። ስለዚህ የብርቱካን ግብረ ኃይልን ሲያዩ፣ ለዚያ ምክንያት የሆነውን ፣ «ብርቱካንን ረስተዋት ነበር» ያሏቸዉን የፓርቲዉ አመራሮች ማየት አለብዎት።

2. ወ/ት ብርቱካን እሥር ቤት በነበሩበት ወቅት፣ ሳያቋርጡ፣ ተራ በተራ፣ ከሰኞ እስከ አርብ፣ እርስዎ «ብርቱካንን ረስተዋት ነበር» ያሏቸው የአንድነት አመራር አባላት፣ ቃሊቲ ድረስ ምግብ ሲያመላልሱ እንደነበረስ ያዉቁ ኖሯል ? ጨዋዎችና ትሁቶች በመሆናቸው «እንዲህ እያደረግን ነዉ» ብለው አልተናገሩም። በብርቱካን ስም ለመነገድ አልሞከሩም፡፡ ይሄን ያደርጉ እንደነበረ የታወቀዉም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቃሊት እሥር ቤት እንደወጡ፣ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በመሄድ ለአመራር አባላቱ ምስጋናቸውን እንዳቀረቡ በተዘገበበት ወቅት ነዉ። (ቅዳሜና እሁድ ወ/ሮ አልማዝ ነበሩ ምግብ ለልጃቸዉ ይዘዉ ይሄዱ የነበሩት) በወቅቱ፣ የአንድነት አመራር አባላት፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ለመጎብኘት ብዙ ጊዜ ሞክረዉ፣ ገዢዉ ፓርቲ ፈቃድ ሊሰጣቸዉ ስላልቻለ ብዙም ለመጠየቅ አልቻሉምም ነበር።

3. ፓርቲዉ በሚሰጣቸው አመራሮች፣ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች፣ የብርቱካን ፎቶ ያለበት ኬኔቴራ እያደረጉ፣ ለወይዘሪቷ መፈታት ብዙ ዘመቻ በአገር ዉስጥ ተደርጓል። ብዙዎች የብርቱካንን ከኔቴራ ካላወለቃችሁ ተብለው የታሰሩም ነበሩ። በአንድነት ጽ/ቤት በየጊዜዉ የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓትም ይደረግ ነበር።

እነዚህን ጥቂቶች እንደምሳሌ ሳቀርብ፣ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት ያኔ የበለጠ መስራት አልነበረባቸውም ነበር ማለቴ አይደለም። በወቅቱ በአንድነት ፓርቲ ስለነበሩት ችግሮችና ስህተቶች ንገረኝ የሚሉኝ ከሆነ፣ ብዙ ልነግርዎት እችላለሁ። የፓርቲዉ አመራሮች ብዙ ያጠፏቸው ጥፋቶች፣ የሰሯቸው ስህተቶች አሉ። ማን የማይሳሳት አለ ? ነገር ግን «ብርቱካንን ረስተው ነበር» ያሉት ክስ፣ በአክብሮት እዉነቱን ልንገርዎትና፣ ከመስመር ያለፈ፣ የአንድነት አመራር አባላትን ይቅርታ ሊጠይቁበት የሚገባ መሰለኝ።

አሁን ወደ አቶ ኃይሉ ሻዉልና የስነ ምግባር ኮዱ ልምጣ። በአሁኑ ጊዜ የአንድነት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ ንግግር ላይ ስላለ ወደ ኋላ ተመልሼ ስለአቶ ኃይሉ ሻውልም ሆነ ስለመኢአድ ማውራት አልፈልግም። መኢአድም ፣ አንድነትም ካለፈው ስህተቶቻቸው ተመረው አብሮ ለመስራት ትልቅ ፍላጎት አላቸው። በዚህም ረገድ በርቱ፣ ተበራቱ እያልኳቸው፣ አቶ ኃይሉ ሻወል የተናገሩት ትቼ ወደ ስነ ምግባር ኮዱ ልምጣ።

እርስዎ እንዳሉት፣ የስነ ምግባር ኮዱን መፈረም ለዉጥ አያመጣም። በዚስ ትክክል ኖት ። ሰነዱ እኮ ተራ ወረቀት ነው። በዚያኛዉ ወገን ደግሞ፣ የስነ ምግባር ኮዱን አለመፈረምም በራሱ ያመጣው ፋይዳም አልነበረም። መኢአድና ሌሎች መፈረማቸው ምንም አልጠቀማቸዉም እንዳሉት ሁሉ፣ መድረክና ሌሎችም አለመፈረማቸው ምን ያመጣላቸው ጥቅም የለም። አንድ ሰው «ሰነዱን ፈረሙ ወይም አልፈረሙም» ብሎ የሚደሰት ወይንም የሚቆጣ ከሆነ፣ ያ ሰው ብስለት የጎደለው ሰው ነዉ ማለት ነዉ።

የአንድነት ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣዉ፣ ሰነዱን ስላልፈረመ ሳይሆን፣ ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ እየሰራ ስላለ ነዉ። የሚሊየነሞች ድምጽ ለነጻነት የተስኘው እንቅስቅሴ አይነት እንቅስቅሴዎች በማድረጉ ነዉ። ይዞ የሚያራምዳቸው የሰለጠነ፣ የፍቅርና የኢትዮጵያዊነት ዴሞክራቲክ ፖለቲካዉና እሴቶቹ ናቸው።

በሴምፕቴበር 2012፣ አቶ በረከት ስምኦን በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በሰጡት አስተያየት «መድረኩ የስነ-ምግባር ኮዱን ካልፈረመ አንደራደርም» ማለታቸውን ተመርኩዤ፣ ሴምፕቴምበር 20 2012፣ ለአንባቢያን ባቀረብኩትና ፍኖት ባወጣው ጽሁፌ፣ ሰሞኑን ከማካፍላቸው ሃሳቦች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ነጥቦች፣ ያኔም አስፍሬ ነበር።

«የመድረክ አመራር አባላት፣ ያኔ የስነ ምግባር ሰነዱን አለመፈረማቸው በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ስናየው፣ ሊያስኬድ ቢችልም፣ አሁን ባለንበት ወቅት ግን ፣ ይህን ሰነድ በመፈረም ኳሷን ወደ ኢሕአዴግ ሜዳ ቢልኳት ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡ ቢያንስ ቢያንስ፣ አቶ በረከት «መድረኩ አመጸኛ ነው» ለሚሉት ክሳቸው እንደምክንያት የሚያቀርቡትን አንድ ነጥብ ያሳጣቸዋል» ብዬ በመጻፍ የመድረክ አለመፈረም ገዢዉ ፓርቲ የበለጠ መድረክን ለማግለል እንደመሳሪያ መጠቀሙን ለማሳየት ሞክሪያለሁ።

ሳክልም «የስነ ምግባር ኮዱ፣ ሕግ እንደመሆኑ፣ የመድረክ አለመፈረም ችግር ሊያመጣ እንደማይገባዉም፣ ለሰላም ሲባል መፈረሙም ችግር የለዉም። ይህ በጣም ትንሽ ጉዳይ ነዉ። ትንሹ ጉዳይ ደግሞ በትልቁ ነገር ላይ እንዳንወያይ ሊያድገን አይገባም። በመሆኑም ለሰላም ሲባል፣ መድረኩ በአስቸኳይ የስነ-ምግባር ኮዱን በራሱ አነሳሽነት በመፈረም ጉልህ እንቅስቃሴዎች እንዲያደርግ እመክራለሁ። ይሄንንም ያደርጋል የሚል ሙሉ ተስፋ አለኝ» ብዬ ነበር የጻፍኩት። ለርስዎ ጽሁፍ በመለስኩት የመጀመሪያው ጽሁፌ፣ ሰነዱ ያኔ መድረክ ያለፈረመው፣ በራሱ ሰነዱ ችግሮ ኖርቶ ሳይሆን ፣ ሌሎች ሰነዶች አብረዉ ካተፈረሙ በሚል ነበር። ሁሉም ወይም ባዶ የሚል አቋም ከመያዝ፣ ከባዶ አንድ ይሻላል፣ አንዱ ይዘን ወደ ሁለቱን እንሂድ የሚል ነበር አስተሳሰቤ።

በወቅቱ የመድረክ አመራር ፣ ሆነ የአንድነት፣ ሃሳቤን ለማስተናገድ ፈቃደኛ አልነበሩም። አሁን ያለውም አዲሱ አመራር ይቀበል አይቀበል አላውቅም። በሂደት የምናየው ይሆናል።

የአንድነት ፓርቲ ከኢሕአዴግ ጋር ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን የሚል አቋሙን ጠንከር ባለ መልኩ አዲሱ አመራር ይፋ አድርጓል። የአለም አቀፍ ማህበረሰብም ፣ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዉያ ሁሉ፣ ዉይይቶችና ንግግሮች እንዲደረጉ ይፈልጋል። ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ፣ ጤነኛ አካላት፣ ድርጅታቸው ወደ ዉይይት እንዲመጣ ይፈልጋሉ። በአሁኑ ወቅት ስልጣኑን ጨብጠው ያሉ የሕወሃት/ኢሕአዴግ አክራሪዎች ግን በስልጣናቸው እንዲቆዩ ጠንካራ የሚሉትን ድርጅት ማዳከም እንጂ ለዚያ ድርጅት መድረክ መስጠት አይፈልጉም። በአለም አቀፍ ማህበረሰቡም ሆነ በኢሕአደግ ዉስጥ ባሉ ሞደሬቶች «ለምን ከአንድነት ጋር አትነጋገሩም ? » የሚል ግፊት ሲመጣባቸው ፣ ከማንም ተቃዋሚ ጋር መነጋገር የማይፈልጉት አክራሪዎቹ፣ የሚመልሱት መልስ «እኛ ለመነጋገር ዝግጁ ነን። እነርሱ ናቸው ፍቃደኛ ያልሆኑ። ፍቃደኛ ከሆኑ ለምን ሰነዱን አይፈርሙም ? » የሚል ነዉ።

እንግዲህ የኔ ትሁት አስተያየት፣ የአንድነት ፓርቲ የስነ ምግባር ኮዱን በመፈረም፣ ለሰላምና ለድርድር መሰናክል የሆነውን ጉዳይ ከመንገዱ እንዲወገድ ቢያደርግ ጥሩ ሊሆን ይችላል እላለሁ። ያን በማድረጉ አገዛዙ ለዉይይት ይዘጋጃል ማለት አይደለም።\ እዚህ ላይ ልብ ይበሉ። እርስዎም ስለአገዛዙ አምባገነንነት ቅልብጭ አርገው እንደሚያውቁትም እኛም በደንብ እናውቃለን። ነገር ግን አንድነት በኢሕአዴግ ዉስጥ ላሉ ሞደሬቶች፣ ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡ፣ ትልቅ መልእክት ያስተላልፍበታል። የሕወሃት/ኢሕአዴግ አካራሪዎች አንድነት የአመጽ ኃይል ነው የሚሉበትን መከራከሪያ ያሳጣቸዋል።። በሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድም፣ ለሰላም እስከ ጫፍ መሄዳቸውን፣ የሰለጠነ ፖለቲካ የሚያራምዱ መሆናቸውን በማሳየት፣ ዝም ብሎ የነበረዉን የአብዛኛው የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ ሊያገኙበት ይችላሉ። ይህን በማድረጋቸው ትልቅነታቸውን በገሃድ ያስመሰክራሉ። ሌላም ደግሞ ትልቁ ምክንያቴ ሰነዱ ኢሕአዴግ ኖረን አልኖረም ለወደፊት የሚጠቅም ሰነድ በመሆኑም ነዉ። ከምርጫ በኋላ ችግሮች፣ ደም መፋሰሶች እንዳይኖሩ የምርጫዉን ሂደት ሰላማዊ በሆነ መልክይ ጋይድ ሊያደርግ የሚችል ሰነድ ነው። እርስዎ እንደሚያስቡት ክፉ ሰነድ አይደለም።

አንድ ነገር ግን ግልጽ ላድርግ። በዉጭ ያለን፣ እኔም ፣ እርስዎም፣ ስለአንድነት ፓርቲ ብዙ ልናውቅ ብንችልም፣ ከኛ፣ በበለጠ ግን፣ አገር ቤት ያሉት፣ ስላለው ሁኔታ ያውቃሉ። እንግዲህ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት፣ እኔም፣ እርስዎም፣ እንዲሁም ሌሎች ከተለያዩ ማእዘናት የምናቀርባቸውን አስተያየቶችን አገናዝበው የሚወስኑትን ይወስናሉ የሚል እምነት አለኝ። ውይይቱ፣ ክርክሩ መልካም ነዉ። ይቀጥልበት እላለሁ።

በመጨረሻ ይችን አጭር ወንድማዊ ምክር ጣል ላድርግልዎትና ላብቃ። የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ስድስት ወራት ይጠብቁና፣ በአንድነት ዉስጥ እየተሰራ ያለውን ገምግመው፣ አመዛዝነው፣ በኢንጂነር ግዛቸውም ሆነ ሌሎች የድርጅቱ አመራሮች ተግባራት ላይ ትችት እንዲጽፍ አበረታታቸዋለሁ። በጎም ይሆን መጥፎ። ጋዜጠኞች የፖለቲካ መሪዎችን ማፋጠጥ አለባችው። የድርጂቶች ፕሮፖጋንዲስቶ መሆን የለባቸዉ። ግን ሲተቹ፣ በመላምትና በስሜት ሳይሆን፣ መረጃና እዉነታን በመያዝ፣ የጋዜጠኝነትን ፕሮፌሽናሊዝምን በጠበቀ መልኩ።

ሌላዉ አቶ ፋሲል፣ ገለልተኝነትዎትን ማሳየት አለብዎት ባይ ነኝ። የሌሎች የፖለቲክ መሪዎች የሥራ እንቅስቃሴ ቢመረምሩና ጋዜጣዊ አስተያየታቸውን ቢያስነብቡንም መልካም ይሆናል። ለምሳሌ ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ ይኸው ለስድስት አመታታ ግንቦት ሰባትን እየመሩ ናቸው፤ ብቸኛው መሪ ናቸው። (ዶር ብርሃኑ ላለፉት ስድስት አመታት ብችኛ የግንቦት ሊቀመንበር ሆነዉ ባለበት ሁኔታ፣ የአንድነት ፓርቲ ግን ሶስት ሊቀመናብርትን አፈራርቋል) በዚህ በስድስት አመታት ዉስጥ ምን ተደረገ ? ከሕዝቡ ብዙ ገንዘብ ተሰብስቦ ፣ አንድ ቀበሌ በጠመንጃ ነጻ ወጣ ወይ? ይኽዉ ዉጤቱ በሻእቢያ ቀሚስ ዉስጥ መተኛት አልሆነምን ? ይሄንን በሚገባ እያወቁ፣ በነዶር ብርሃኑ እንቅስቃሴ ላይ እንደ ጋዜጠኛ ትችት ማቅረብ አልነበረብዎትምን? የግንቦት ሰባት የስድስት አመታት ክስረትን እንዳላዩ ሆነዉስ ለምን ያልፋሉ ? ፈረንጆች እንደሚሉት Why the double standard ?

ትላንት ፓልቶክ ላይ «ፋሲል የዶር ብርሃኑ ፈረስ ነዉ …የግንቦት ሰባት አባልና ካድሬ ነዉ …በነ ዶር ብርሃኑ ታዞ ነዉ የሚጽፈው» እያሉ የሚናገሩ ነበሩ። ያንን አባባል አልጋራዉም። ለምን መረጃ የለኝምና። ግንቦት ሰባት ሚስጥራዊ በመሆኑ እርስዎ አባል ይሆኑ አይሆኑ ማወቅ አልችልም። ነገር ግን ግንቦት ሰባትን እንደ ጣኦት የማምለክ ያህል፣ አንዳች ትንፍሽ ሳይሉ፣ አንድነት ፓርቲ ላይ ይሄን ያህል መሰረት የሌለዉ ጠንካራ ትችት ማቅረብዎ፣ በብዙዎች አይምሮ ዉስጥ ጥያቄን የሚጭር ነዉ። እንግዲህ በምን መልኩ ይሄንን ጥያቄ እንደሚያስተናግዱት አላውቅም። ጉዳዩን ለርስዎና ለሕሊናዎ ትቼዋለሁ።

በድጋሜ ለጊዜዎት ምስጋና አያቀረብኩ እሰናበትዎታለሁ። ቸር ይግጠምዎት !


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>