በዘመነ ኢህአዴግ ከታሪክ ተጠያቂነት በፍፁም ሊያመልጡ ከማይችሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ብአዴን እና ኦህዴድ በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ፡፡ ሁለቱም ‹እንወክለዋለን› በሚሉት ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ክህደት ለመፈፀማቸው፣ ደርዘን ያለፉ ድርሳናትን ማዘጋጀት እንደሚቻል እናውቃለን፡፡ አልፎ ተርፎም ህወሓትን ከመሰለ የማፍያ ቡድን ጋር ግንባር ፈጥረው ‹‹ወከልነው›› የሚሉትን የማህብረሰብ ክፍል ህልውና ማድቀቃቸው እውነት ነው፡፡ በርግጥ ምንም እንኳ የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ የጣለ ከፋፋይ ፖለቲካን ጨምሮ ሕዝብ እና ትውልድ የሚሉ ነገሮችን ቅርጫት ውስጥ የመጣል አባዜ ቢጠናወተውም፣ ህወሓት ከቅጥረኞቹ ይልቅ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ቁመና እና መሬት የወረደ አጀንዳ ይዞ የተነሳ መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው፡፡
በዚህ ቁጣ እንድናገር ያደረገኝ ሰሞነኛ ምክንያት ከአንድ የብአዴን ከፍተኛ ካድሬ ነውረኛነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ሰው የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አለምነው መኮንን ሲሆን፣ ኢህአዴግን የተቀላቀለው በተወለደበት ሰሜን ወሎ በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ ከመንግስት ለውጥ በኋላም ረዝም ላለ ጊዜ በዛው በሰሜን ወሎ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር በኢህዴን /ብአዴን/ ተጠሪነት ሰርቷል፤ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪውን ማግኘቱን ተከትሎም በክልሉ አስተዳደር ስር ባለው በምፃረ ቃል ‹‹SRAR›› ተብሎ በሚጠራው (በእርሻና መልሶ ማቋቋም ላይ በሚያተኩር) ተቋም በአንድ ክፍል ኃላፊነት አገልግሏል፡፡ በምርጫ 97 ዋዜማ ደግሞ የክልሉ የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ እንደነበር ይታወሳል፤ ቀጥሎም የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሰርቷል፤ ከ2004 ዓ.ም
መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ቢሮ ኃላፊ ነው (በነገራችን ላይ በአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሶስት ናቸው፤ ከአለምነው በተጨማሪ ብናልፍ አንዱአለም እና ዶ/ር አምባቸው የተባሉ ተሿሚዎችም አሉ) የሆነው ሆኖ ይህ ሰው ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር በተዘጋጀ አንድ ስብሰባ ላይ የተናገረውን አስነዋሪ ነገር፣ ረዥም ዕድሜ ለኢሳት ይሁንና ጭው ባለ ድንጋጤ ተውጬ አድምጬዋለሁ፤ ግና ተሳዳቢው የክልሉ አስተዳዳሪ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ የንግግሩ ይዘት ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ይጠቃለላል፡-
‹‹….የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው፣ ከሌላው ጋር መኖርን መልመድ አለበት፡፡ …የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ፣ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደድ ምክንያት ሆኖታል። ….በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው። ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም፡፡ …ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት። ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም። …ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው። ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው። ያንን ምግብ እየተመገበ ያቅራራል።››
በእውነቱ ይህንን የተናገረው ፋሽስቱ ዱቼ ሞሶሎኒ አሊያም ሶማሊያዊው መሀመድ ዜያድባሬ ቢሆን ኖሮ፣ ቅኝ-ግዛት ያማለለው የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ አድርጎ ማለፍ ይቻል ነበር፤ ግን የዚህ ልብ ሰባሪ ቃላት ባለቤት የክልሉ አስተዳደሪ አለምነው መኮንን ነው፡፡ ዳሩ እርሱስ ቢሆን ማንን እየሰማ አደገና ነው! ምክንያቱም የቀደሙት የብአዴን ሰዎች የወከሉትን ዘውግ ሲረግሙና ሲያንቋሽሹ መታዘባችን የትላንት ክስተት ነው፡፡ የታምራት ላይኔን ‹ሽርጣም ሲልህ የኖረውን ይሄን ነፍጠኛ አሁን ጊዜው ያንተ ነውና በለው› የሚለውን ሐረር ላይ የተሰማ እልቅቲ ነጋሪ አዋጅ ጨምሮ፤ የተፈራ ዋልዋ ‹አማራው በባዶ እግሩ እየሄደ፣ ስንዴ በሩ ላይ አስጥቶ በባዶ ሆዱ የሚፉልል ትምክህተኛ ነው› እስከሚለው ድረስ ያሉ በአደባባይ የተሰሙ ስድቦችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ምሳሌ ለማድረግ፣ እዚህ ሳምንት ድረስ በሬዲዮ ፋና እየተተረከ ያለ አንድ የጥላቻና ዘረኝነት አቀንቃኝ የሆነ መፅሀፍን ልጠቀስ (በነገራችን ላይ እንዲህ አይነቱን ለእርስ በእርስ ግጭት መነሾ የሚሆን፣ በክፋት፣ በተንኮል፣ በክበረ-ነክ ጭብጥ የተሞላን መፅሀፍ ርዕስ እዚህ ጋ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንምና አልፈዋለሁ)፡፡ ይህንን መፅሀፍ ደረሲው ዳንኤል ግዛው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያዘጋጀው ሲሆን፣ ወደ አማርኛ የመለሰው የብአዴን ታጋይና የበረከት ስምኦን ባለቤት ወንድም የሆነው መዝሙር ፈንቴ ነው፡፡
በርግጥ በምስጋና ገፁ ላይ እንደተጠቀሰው፣ እንዲተረጉመው ያዘዘውና መፀሀፉን የሰጠው ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ነፃነትና ክብር በዱር-በገደል ታግያለሁ የሚለን ራሱ በረከት ስሞኦን ነው፤ ውለታውንም እንዲህ ሲል ገልፆለታል፡-
‹‹…የምተረጉማቸውን እያንዳንዳቸውን ገፆች ከስር ከስር እየተከታተለ ያነባቸውና ያበረታታኝ ነበር፡፡ ያስጀመረኝ እሱ፣ ያስጨረሰኝም እሱ ነበርና ለአቶ በረከት ስምኦን ያለኝ ምስጋና እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡››
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ‹‹አስተማሪ፣ አስገራሚና መሳጭ›› ሲል በፃፈው የጀርባ ገፅ አስተያየት፤ ይህንን እንቶ ፈንቶ እና አንድ ብሔርን ለይቶ የሚያጠቃ ውጉዝ ድርሳን ከፍቅር እስከ መቃብር ጋር በአቻነት አስከማስመሰል ታብዮአል፡፡ ህላዊ ዮሴፍም ረቂቁን በማንበብና በማረም ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳደረገ ተርጓሚው ተናግሯል፤ በአናቱም መዝሙር ፈንቴ መፅሀፉን ከመተርጎሙ በፊት በ‹‹ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ›› ፋብሪካ ውጪው ተሸፍኖለት (የማሳተሚያ ዋጋውንም የቻለው ሼክ መሀመድ አላሙዲ ነው) አደረኩት በሚለው ጉዞ፣ አማራ ረግጦ፣ ቀጥቅጦ፣ ከሰው በታች ዝቅ አድርጎ፣ መሬታቸውን በመንጠቅ አሽከር አድረጎ… እንደገዛቸው የተተረከላቸው የማንጃ እና ማኛ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሚገኙበት ደቡብ ኢትዮጵያ ሄዶ ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረጉን ከነገረን አኳያ (የእንግሊዘኛውን ቅጂ ማግኘት አልቻልኩም) መፀሀፉ ቃል በቃል የተተረጎመ ነው ብሎ መቀበሉ ይቸግራል፡፡ ራሱም ቢሆን የፃሀፊው ተደራሲያኖች አሜሪካውያን መሆናቸውን ጠቅሶ ‹‹አቀራረቡን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ›› ማለቱን ስናስተውል ከተርጓሚነትም ወሰን ተሻግሮ ተጉዟል ብለን እንድናምን ከመገፋታችንም በላይ፣ እነበረከት ስምኦን በአማራው ላይ ያላቸውን ያደረ ጥላቻ ለማንፀባረቅ የተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል ብለን ለመጠርጠር እንገደዳለን፡፡
እንግዲህ ብአዴን ማለት፣ ከጉምቱ መሪዎቹ ጀምሮ የክልሉን ነዋሪ ‹‹ቀጣይ ነፃ አውጪያችሁ ነኝ›› የሚለውን ነውረኛውን አለምነው መኮንን ጨምሮ፣ ይህን መሰል በተዋረደ ስብዕና የሚበየኑ ምስኪን ፍጥረቶች የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ታዲያ፤ ለዚህ ሁሉ ሰቅጣጭ ሁኔታ፣ የክልሉ ነዋሪ የሆነው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዝምታ ምን ድረስ ይሆን? የሚለው ይመስለኛል፡፡