ሌላኛው ሰሞነኛ ጉራማይሌ የፖለቲካችን ገፅ አንጋፋውን የኦሮሞ ልሂቅ ሌንጮ ለታን የተመለከተው ርዕሰ-ጉዳይ ነው፡፡ ኦነግን በመመስረትም ሆነ ፖለቲካዊ ቁመና ይዞ ህልው እንዲሆን ከዮሀንስ ለታ በላይ ማንም የለፋ እንደሌለ ይነገራል፤ ዮሀንስ ከጓዶቹ ጋር ተባብሮ ድርጅቱን ሲመሰርት ካነገበው አጀንዳ አኳያ ያለውን ተዛምዶ ገልፆ ባይነግረንም፣ ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት ይታወቅበት የነበረውን መጠሪያ ስሙን ‹ሌንጮ› በሚል ቀይሮታል፡፡
ኦነግ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የሻዕቢያ እና የህወሓትን ያህል ባይሆንም ያለፈውን ስርዓት ለመቀየር የጠመንጃ ትግል አድርጓል፡፡ ከዚህም አኳያ ይመስለኛል የመንግስቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ግብዓተ-መሬት መፈፀሙ የቀናት ጉዳይ ብቻ እንደሆነ በታመነበት ወቅት በሀገረ እንግሊዝ፣ ሰሞኑን ‹ባድመን ለኤርትራ ስጡ› እያለ በሚወተውተን ኸርማን ኮህን አርቃቂነት በተዘጋጀው የለንደኑ ኮንፍረንስ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር የተቃውሞውን ፖለቲካ ወክሎ እንዲገኝ የተደረገው፡፡ ኋላም የታመነው ደርሶ አገዛዙ ሲወድቅ ኦነግም የሽግግር መንግስቱ መስራች አባል ሆኖ የመተዳደሪያ ቻርተሩን ዋነኛ አዕምዶች (የመሬት የመንግስት ባለቤትነት፣ የመገንጠል መብት እና ቋንቋ ተኮሩን ፌደራሊዝም) ከማርቀቅ ባለፈ እስከ 1984 ዓ.ም የመጨረሻ ወራት ድረስ የሥልጣን ተቋዳሽ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ ባደረሰበት ጫናና ግፊት ሥልጣኑን ለቆ ተመልሶ ወደ በረሃ መግባቱ አይዘነጋም፡፡
ግና! ይህችን ለብዙ አስርታት በታጋዮቹ ስትማተር የነበረችውን የኦነግ የመኸር አንዲት ዓመትን ተከትሎ፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ መውረድ የጀመረው የመከራና የዕልቂት መዓት ዛሬም ድረስ አላባራም፡፡ እስከዚህች ቀንም እልፍ አእላፍ ንፁሃኖች በኦሮሞነታቸው ብቻ አስከፊውን የቃሊቲ ማጎሪያ ጨምሮ በተለያዩ ገሀነም-መሰል እስር ቤቶች የምድር ፍዳቸውን እየተቀበሉ ነው፡፡ በደርግ ዘመን የኤርትራ ነዋሪዎችን ‹‹ሻዕቢያ››! በማለት በአደባባይ ገድሎ መሄዱ ቀላል የነበረውን ያህል፣ ኢህአዴግም ሃያ ሁለቱን ዓመታት ሙሉ በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ላይ ተመሳሳዩን ታሪክ ደግሞታል፡፡ የነገይቱን ኢትዮጵያ ህልውና በሚያጠይቅ ሁኔታም በግዙፉ ቃሊቲ ‹የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው› እስኪባል ድረስ ያለ አሳማኝ ክስ እያነቀ ግቢውን እንዲያጥለቀልቁት አድርጓል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ሰበብ የእነሌንጮ ለታ ድርጅት መሆኑ አይካድም፡፡
ኦነግ ከ1980ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ለስርዓቱ አስጊ እንዳልነበር እና ይዞታውን ከባሌ ወደ አስመራ እና ሚኒሶታ ማዘዋወሩን፣ በስሙ ለተፈፀመው ዕልቂት ቀማሪና አዛዡ ህወሓትም ሆነ አስፈፃሚው ኦህዴድ ጠንቅቀው የሚያውቁት ቢሆንም፤ ‹‹በስመ-ኦነግ›› ከሚፈነዱና ከሚከሽፉ ፈንጂዎች ጋር እያያዙ የክልሉን ተወላጆች የጥቃት ኢላማ ማድረጉ መደበኛ መንግስታዊ ስራ ከሆነ ሁለት አስርታት ተቆጥረዋል፡፡ የዚህ መነሾም የህወሓት ኦሮምኛ ተናጋሪ ክንፍ ከሆነው ኦህዴድ ይልቅ፣ በኃይል የተገፋው ኦነግ በብዙሀኑ ልብ ማደሩ ያነበረው ፍርሃት አንዱ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ኦህኮ እና ኦፌዴን (ባለፈው ዓመት ‹‹ኦፌኮ›› በሚል ስያሜ መዋህዳቸው ይታወሳል) ያላቸውን ቅቡልነት መጨፍለቅን ያሰላ ይመስለኛል፡፡
በዚህ የተቀነባበረ ጥቃትም ብዙዎች ለህልፈት፣ እልፍ አእላፍቶች ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ህፃናት ያለ አሳዳጊ፣ አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀርተዋል፡፡ እርግጥ ይሄ ጉራማይሌ አይደለም፤ አያሌ ማስረጃ ሊቀርብበት የሚችል ተጨባጭ እውነታ እንጂ፡፡ በአናቱም ይብዛም ይነስ የቀድሞ የኦነግ መስራችና የአመራር አባሉ ሌንጮ ለታ፣ ለዚህ ሁሉ ስቃይና መከራ የድርሻውን ያህል የታሪክ ተወቃሽ (ተጠያቂ) መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡
የሆነው ሆኖ በሌንጮ ኦነግ ስም ለተገደሉት ገዳዮቻቸው ለፍረድ ሳይቀርቡ፣ የታሰሩት ሳይፈቱ፣ የተሰደዱት ሳይመለሱ፣ የፈረሱ ጎጆዎች ሳይቀለሱ፣ ሌላው ቀርቶ ከኢትዮጵያም አልፎ ከኬኒያ ‹ኦነግ› እያሉ አፍነው በመውሰድ ለእስር መዳረጉ (በቅርቡ በወህኒ ቤት ሕይወቱ ያለፈውን ኢንጂነር ተስፋዬ ጨመዳን እናስታውሳለን) ዛሬም ቀጥሎ እያለ ኦቦ ሌንጮ ለታ ‹‹የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር›› የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት መስርቶ፣ ለሚቀጥለው ምርጫ እያሟሟቀ ከመሆኑም በላይ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ታሪክ እንደሚሰራ የተናገረውን ማድመጣችንን ነው ለጉራማይሌ ፖለቲካ ማሳያ ያደረኩት (ሌንጮ ኦዴግን ከመሰረተ ጀምሮ ላለፉት በርካታ ወራት ‹‹ገብተን እንታገላለን›› ማለቱን ስንሰማ ከርመናል) በተያያዘም ሰውየው የኖርዌይ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ መሆኑን ስንጨምር፣ በአንድ ወቅት ራሱም ‹‹እዚህ ኖርዌይ ቁጭ ብዬ ምን እሰራለሁ?›› እንዳለው የአማካሪነቱን ከፍተኛ ደሞዝ ጭምር ትቶ ለመምጣት መወሰኑ፣ ቀጣይ ሚናው ላይ ያለውን የመተማመን ልክ ማየት እንችላለን፡፡ ርግጥ ሌንጮ ከ40 ዓመታት በፊትም የቅርብ ዘመዱ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለታሪክ ትምህርት ወደ ጀርመን ለመሄድ አዲስ አበባ ላይ በተገናኙበት ጊዜ ‹አንተ ታሪክ ተማር፤ እኛ ደግሞ ታሪክ ሰርተን እንጠብቅሀለን› ማለቱ አይዘነጋም፡፡ ዛሬም ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላቶች ስለታሪክ መጨነቁን ያመላክታሉ፡፡ ይሁንና ሌንጮ ‹ታሪክ መስራት› የሚለው የእነአባዱላ ገመዳን አይነት ወዶ-ገብት ከሆነ ሀፍረቱ ለሁላችንም መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኦሮሚያን ለመደለል ሌንጮን በዝውውር የማምጣቱ ሥራ የተጀመረው በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን ነው፤ የዊክሊክስ ዘገባም እንደጠቆመው፣ መለስ ዜናው ‹‹ሌንጮ ማድረግ ያለበት እኔን ለማግኘት መሞከር ብቻ ነው፤ ይህን ደግሞ እንዴት ማድረግ እንዳለበት ያውቃል›› ማለቱን አስነብቦናል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ባዘጋጀው፣ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕገ-መንግስታዊነት ጉዳይ ላይ በተካሄደ ኮንፈረንስ፣ የቀረበውን የሌንጮ ለታን ጥናታዊ ፁሁፍ መከራከሪያዎችን በማብራራት ተጠምዶ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ እንደነበረ ስናስታውስ፣ በሌንጮ የመምጣት ድርድር ውሳኔ ውስጥ የፕ/ሩን (የመንግስትን) የሰነበተ ሚና እንድንገምት እንገደዳለን፡፡ እርሱም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ፊንፊኔ ላይ የታየው በ2004 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ደግሞ የአሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ኖርዌይ እጅ እንዳለበት ተሰምቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር መጀመሪያ ሳምንት ሌንጮና አባዱላ ገመዳ አሜሪካን ሀገር በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፈው የነበረ መሆኑም የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡
ኢህአዴግ ስጋት ላይ ከጣሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ግለስብን ገንጥሎ ማማለልን ተክኖበታል፤ ከሶስት ዓመት በፊት መለክት ተንፍቶለት ወዶ የገባው አባቢያ አባጆቢር (ከኦነግ መስራቾቹ አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ለእንግሊዘኛው ‹‹ዘ-ሪፖርተር›› ጋዜጣ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ፣ የድርጅቱ የመጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ስለመገንጠል የሚያወራውን አንቀፅ በወቅቱ ተቃውሜ ነበር ማለቱ ይታወሳል) ዛሬ ድምፁ አይሰማም፡፡ ከኦብነግ ጋርም ተደረሰ በተባለ ስምምነት የመጡትን ግለሰቦች፣ ድርጅታቸው አሁንም አፈመዝ ካለመድፋቱ አኳያ ስናየው ጨዋታው ዕቃቃ እንደነበር ይገባናል፡፡ በዚህ ሰሞን ደግሞ ዶ/ር መራራ ጉዲና ከፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ጋር ሊወያይ ወደ ጀርመን አምርቷል፤ ሌንጮ ለታም አዳዲስ አባላትን ሊመለምል እዛው ጀርመን ይገኛል (ሁለቱ ጉምቱ የኦሮሞ ልሂቃኖች ተገናኝተው ይሆን?) በርግጥ ሌንጮ የጀርመን ቆይታውን ሲጨርስ፣ በሆላንድ ያቀደውን ተመሳሳይ መረሃ ግብር አከናውኖ በይፋ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ለጉዳዩ ከሚቀርቡ የመረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡
ይሁንና እዚህ ጋ የሚነሳው ጥያቄ ሌንጮ ወደ ሀገሩ ለምን መጣ? የሚል አይደለም፤ እነበቀለ ገርባን የመሳሰሉ ፍፁም ሰላማዊ እና እጃቸው በንፁሀን ደም ያልጨቀየ ፖለቲከኞችን መታገስ ያልቻለ ስርዓት፣ ለሌንጮ የሚሆን ይቅር ባይነትን ከወዴት አገኘ? የሚል ነው፤ ሁለት አርፍተ ነገር የተናገረ ሁሉ ተለቃቅሞ እየታሰረ ሌንጮ ምን ተማምኖ መጣ? በኦሮሚያ ላይ የነገሡት እነአፄ አባዱላና ኩማ ደመቅሳስ ቢሆኑ ከሌንጮ አዲሱ ድርጅት ተነፃፅሮ የሚነሳባቸውን የቅቡልነት መገዳደር ለመጋፈጥ እንዴት ፍቃደኛ ሆኑ? ምናልባት መተካካት የሚባለው ይህ ይሆን እንዴ? ወይስ መረራ ጉዲና ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ በቁመቱ ልክ ሥልጣን ይገባዋል!›› እንዲል፣ ሌንጮ ለታም በራሱ ቁመት የተቀነበበ ሥልጣን ቃል ተገብቶለት ይሆን? …የእነዚህና መሰል ጥያቄዎች ምላሽ ዛሬም በሙት መንፈስና በታመመ ሰው እንድትመራ በተፈረደባት ኦሮሚያ ላይ በቀጣይ ከሚኖረው ፖለቲካዊ አሰላለፍ ጋር መጋመዱ አይቀሬ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ከዚህ ባለፈ ‹‹ጀግናው›› ኢህአዴግ የሌንጮ ድርጅትን ኦፌኮን ወይም አንድነትን እንደመሳሰሉ ፓርቲዎች ነፃ ተቃዋሚ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ይፈቅድለታል ብሎ ማሰቡ እጅግ በጣም የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ኦቦ ሌንጮ ከሳምንታት በፊት ለጀርመን ድምፅ ራዲዮ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ላይ፣ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ ስለመወሰኑ ሲጠየቅ ‹‹ፖለቲካ በምርጫ በመሳተፍ ብቻ አይወሰንም፤ ሕዝቡን ማስተማርና ማንቃቱም አንዱ መንገድ ነው›› የሚል መንፈስ የያዘ መልስ ሰጥቷል፡፡ የሆነው ሆኖ ሌንጮ ለምርጫ ቅስቀሳ አሊያም ለንቃተ ህሊና ስብከት ፊቱን ወደ ኦሮሚያ ከማዞሩ አስቀድሞ የሚከተለው ጥያቄ ተጋፋጭ ተግዳሮት እንደሚሆንበት ይታሰባል፡- በሽግግር መንግስቱ ወቅት ሥልጣን ላይ የነበርክበትን ጊዜ ተከትሎ አንተን እና ኦነግን አምነው ከቤታቸው የወጡ ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንን፣ አባቶቻችንን የት ጥለሀቸው መጣህ? ሰማዕታቶቻችንንስ በማን ስም እንዘክራቸው? … Akka dhufaa jirtu barree carraa garii (sihaaqunamu)