Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

የውህደቱ ቁማርተኞች – አስራት አብርሃ

$
0
0

የሀገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ወደ አንድ ጠንካራ የለውጥ አማራጭነት እንዲሰባሰብ እና ገዥውን ፓርቲ የሚገዳደር ወሳኝ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ ማስቻል የብዙ ቀናት አሳቢ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት እንደሆነ ይሰማኛል። እኔም ራሴን ይህ ዓላማ ከፍፃሜ እንዲደርስ ከሚፈልጉ ወገኖች ውስጥ እንደ አንዱ በማድረግ እቆጥረዋለሁ። ውህደት እንዲኖር መፈለግ አንድ ነገር ሆኖ፤ ማን ከማን ጋር ነው የሚወሃደው? የውህደት መስፈርቱን ምን መሆን ይኖርበታል? የሚለውንም አብሮ ማየቱ የሚገባ ይሆናል።

ከርዕዮተ ዓለም አንፃር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በዋነኝነት ሶስት ዓይነት አሰላለፍ ነው ያለው። አንደኛው “ወግ አጥባቂ” ወይም “ቀኝ አክራሪው” ኃይል እየተባለ የሚጠራው ነው። በዚህ ጎራ የሚመደቡት ኃይሎች ላይ ላዩ ሲታዩ፣ በርዕዮተ ዓለም የግለሰብ ነፃነት መሰረት የሚያደርገውን ሊበራል ዴሞክራሲ የሚከተሉ ይመስላሉ፤ በተጨባጭ ካላቸው አመለካከት፤ ከሚያራምዱት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አንጻር ሲታዩ ደግሞ፤ የተወሰነ አከባቢ ወይም የህብረተሰብ ክፍልን በማዕከልነት የሚወክሉ፤ ከዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ባሻገርም ኢህአዴግ በሚከተለው የብሄር ተኮር ፖለቲካ ምክንያት አጥተነዋል የሚሉቱን የበላይነት የማስመለስ አጀንዳ ያላቸው ናቸው።

የእነዚህ ኃይሎች አካሄድ ያለፈው ስርዓት በምንም ዓይነት መልኩ ተመልሶ እንዲመጣ ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር በተቃራኒ እንዲቆሙ ስለሚያደርጋቸው ባሉት ፖለቲካዊ አስላለፎች መካከል ውህደት እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆን ነው። ይሄ ጎራ አንዱን ጥግ ወይም ጫፍ ይዞ የሚሄድ፤ በደንብ የተደራጀ፤ ከሌሎች አሰላለፎች አንፃር ድርብ፣ ድርብርብ የሆነ ግብ እና ዓላማ ያለው በመሆኑ ጎልቶ የሚሰማና የሚታይ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ጨዋታው ሜዳ ጥቂቶች ብቻ የሚጫወቱበትና ሌላውን የዳር ተመልካች እንዲሆን የሚያደርግ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር፤ በተለያዩ ልሂቃን መካከል መተማመን እንዳይኖር በማድረግ በእኩል የድርሻውን የሚያበረከት ነው።

ሁለተኛው አሰላለፍ ከላይ በአንደኛው ከተገለፀው ጎራ በተቃራኒው ያለ እና ከርዕዮተ ዓለም አንፃር ሲታይም ግልፅ ባለ ሁኔታ ማስቀመጥ የሚያስቸግር፤ በዋነኝነት ክልላዊ ብሄርተኝነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት፤ ከፖለቲካዊ ግብ አንፃር ደግሞ የራሳቸውን አከባቢ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ከማስተዳደር ጀምሮ በፌደራል መንግስት ውስጥም ተገቢውን ውክልና እንዲኖራው የሚፈልጉ፤ እንዲሁም አሁን ካለው ፌደራል መንግስት በመገንጠል የራሳቸውን ነፃ ሀገር ለመመስረት የሚታገሉ ቡድኖች በአንድ ላይ የሚያጠቃልል ነው። በዚህ ጎራ የተሰለፉ ኃይሎች በሚያራምዱት ፖለቲካዊ አመለካከት ምክንያት “የተነሱት ኢትዮጵያን ሊበታትኑ ነው” የሚለውን የሌላኛው ወገን ውንጀላ ስለሚያጋልጣቸው እና ስለሚያስጠረጥራቸው አብሮ መስራትና በጋራ መታገል እንዳይቻል ምክንያት መሆናቸው አልቀረም።

እውነትም የአንዳንዶቹ እንቅስቃሴ ሲታይ ኢትዮጵያን ሊበታተን የሚችል አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ለመረዳት ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ ኃይሎች ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ የሆነ ኃይል ለማምጣት እና ከሌላው ጋር ማዋሃድ በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶቹ “ከሌላው ጋር ከተዋሃድን በሌሎች እንዋጣለን” ይላሉ፤ የዚህ ዓይነት ስጋት ካላቸው ፓርቲዎች ውስጥ የአንዳንዶቹ ስጋት ውሀ የሚቋጥር አይደለም። ለምሳሌ የኦሮሞ ፓርቲዎች “በሌሎች እንዋጣለን” ሲሉ በእውነቱ ልብ ለሚል ሰው ራሳቸውን በራሳቸዉ የሚሰድቡ ነው የሚመስሉት፤ ወይም ደግሞ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ አይወክሉም ማለት ነው። የተወሰኑ ደግሞ “ከሌሎች ጋር ከተዋሃድን የተመሰረትንበትን የብሄር ወይም የክልል ዓላማችንን ማስፈፀም አንችልም” የሚል ምክንያት የሚያቀርቡ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ከሌሎች ጋር ጥምረት ወይም ግንባር በመፍጠር የፌደራሉን መንግስት መመስረት የሚፈልጉ፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግስትም ሆነ አስተዳደራዊ አከላለል ላይ ብዙም ቅሬታ የሌላቸው፤ ብዙውን ጊዜ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላቸው ልዩነት የአፈፃፀምና የአተገባበር የሆነ፤ ወይም በኢህአዴግ የተሰጠው “የብሄር መብት በቂ አይደለም” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ጥቂት ይሁን እንጂ በዚህ አሰላለፋቸው እንዲገፉበት የሚያደርግ ከውጭም፣ ከሀገር ውስጥም ፅንፈኛ የሆኑ ደጋፊዎች ያላቸው ናቸው።

እነዚህ ከላይ ያሉትን ፍፁም ተፃራሪ የሚመስሉትን ሁለት ጎራዎች ለማዋሀድ ማሰብ ከባድ ነው። ነገር ግን ፍፅም የሚቻል አይደለም ለማለት የሚስችል መሰረታዊ የሆነ ምክንያት አለ ብዬ አላስብም። እኔ በበኩሌ እነዚህን ኃይሎች በጋራ ሊስማሙበት የሚችል ፖለቲካዊ አጀንዳ በመቅረፅ፣ እርስ በእርሳቸው መተማመን የሚችሉበትን ሁኔታ በመፍጠር አንድ ላይ ተዋህደው አስተማማኝ የሆነ የፖለቲካ አማራጭ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ይህን አቋሜንም በተገኘ አጋጣሚ ሆሉ ከማንፀባረቅ ተቆጥቤ አላውቅም። በዚህ አቋሜ ደስተኛ ያለሆነ አንዱ አፍቃሬ ህወሀት “አይጥና ድመት የሚተባበሩበት አጋጣሚዎች አሉ” በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ አሰላለፎች ለማዋሀድ ማሰብን ድመትን ከአይጥ ጋር የማስማማት ያህል ፈፅሞ የማይቻል አድርጎ አቅርቦታል።

እንደ እኔ እምነት ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገቢ የሆነ የተሳካ ውህደት ማድረግ ያልቻሉበት ስረ ምክንያት በፓርቲዎቹ መካከል ባለው ያለመተማመን፤ የስልጣን ጥመኝነት እና የተወሰነ አካባቢን ብቻ የሚወክል ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ መኖር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ራዕይ ማጣት ነው። ከማንኛውም ተፅዕኖ ውጪ ሆነ ለሚያየው ሰው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ አንድ ኃይል ተሰባስበው እንዳይታገሉ የሚያድርግ መሰረታዊ የሆነ ችግር የለም። በዋነኛነት ውህደት ይቻላል ሲባል ከዚሁ መሰረታዊ እምነት በመነሳት ነው።

በአንድ ላይ ለመስራትና በአንድ ላይ ለመኖር ሰው በመሆናችን ብቻ በራሱ በቂ ምከንያት ነው። ለምሳሌ የአሜሪካ የጥቁሮች የነፃነት አባት የሚባለው ማርቲን ሉተር ኪንግ “I have Dream” በሚለው ታሪካዊ ንግግሩ “አንድ ቀን ጥቁሮችና ነጮች ሁለቱም እኩልነት በአንድ ላይ በአንድ ሀገር እንደ አንድ ህዝብ ሆነው የሚኖርበት ቀን እንደሚመጣ ህልም አለኝ” ያለው ከዚሁ የሰው ልጆች ሰብአዊ አንድነት በመነሳት ነው። ያን ህልሙ እርሱ በህይውት ኖሮ ባያየውም፤ እኛ በዘመናችን እውነት ሆኖ ተመልክተናል። ዛሬ አሜሪካውያን ነጭ እና ጥቁር ሳይሉ ለሁሉም የምትስማማ ሀገር ለመፍጠር መሰረታዊውን ጥያቄ መልሰው ጨርሰዋል። የዛሬ ሀምሳ ዓመት ፍፁም ሊታሰብ የማይችል የነበረውን በጥቁር ፕሬዝዳንት የመመራት ጉዳይ፣ ዛሬ ጥቁሩን መሪያቸው አድርገው በመምረጥ በሰላም አብረው እየኖሩ ነው፤ ከዚህ አንጻር ለሌላውም ጥሩ ምሳሌ ሆነዋል።

እንደዚሁም ታላቁ አፍሪካዊ የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ “ነጮች ከሀገራችን ይውጡ!” የሚለውን ፅንፍ የያዘ አቋም በማስቀረት “ጥቁሮችም ሆነ ነጮች በሰላምና በፍቅር አብረን መኖር እንችላለን፤ ደብብ አፍሪካ ለሁላችንም ትበቃናለች።” የሚለውን ሀሳብ በማቀንቀን ድል አድርጓል። ለሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ጮራ፣ ሰላምና ነፃነት አስገኝቷል። በዚህም ተደናቂነትን፣ እንዲሁም ምሳሌ የመሆንን ክብር ተጎናጽፎበታል። በዚህ እምነቱም ምክንያት በክብር ኖሮ በክብር አልፏል። ይህ ትልቅ የነፃነት ሰው፤ በሰው ልጆችን መሀል መሰረታዊ የሚባል ልዩነት እንደሌለ በመገንዘብ “ሰው ሁሉ አንድ ነው፤ ማንኛውም ሰው እኩል በሰውነቱ ታውቆ፣ በአንድ ላይ በፍቅር፣ በመከባበር እና በመቻቻል ሊኖር ይችላል” ከሚል ትክክለኛ ፍልስፍና ስለተነሳ ስኬቱ ታላቅ ሆኗል።

በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ሰው ከመሆን ባሻገር፤ ከሌላው ሀገር ህዝብ የሚለየን ብዙ ነገር አለ፤ ይብዛም ይነስም በአንድ ሀገር ለረጅም ጊዜ አብረን የኖርን፣ የጋራ የሆኑ ብዙ ነገሮች ያሉን፣ ክፉ እና ደጉን አብረን ያሳለፍን፣ የተዋለድንና የጋራ በሆነ ማንነት ያደግን ህዝቦች ነን። ይህ ሁሉ ታሳቢ ሲደረግ ኢትዮጵያውያን ከቋንቋ እና ከዘር በላይ ከፍ ባለ ሀገራዊ ማንነት ለማሰብ፤ ለመዋሀድ፣ አብረን ለመስራት እና የጋራ የሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማራመድ የሚከለክለን ነገር የለም። ሌላው ቢቀር እንኳ በአንድ ላይ ለመኖር የሚያስችል፣ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩት ነጮች እና ጥቁሮች በላይ የሆነ ምክንያት አለን።

ስለዚህ በእኛ ሀገር በተለያዩ ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት የአይጥ እና የድመት ያህል መሰረታዊ እና ተፈጥሯዊ አስመስሎ ማቅረብ ትክክል አይደለም። ልዩነቱ የአይጥ እና የድመት ያህል፤ የጠፊ እና የአጥፊ ዓይነት ከሆነ አብሮ መጓዝም፣ መዋሀድም የሚታሰብ አይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም መሰረታዊ የሆነ የተፈጥሮ ልዩነት ካላቸው ልዩነቱን ማስታረቅ የማይቻል ይሆናል። አይጥ እና ድመት በምንም ተአምር ተስማመተው፤ አብረው ሊኖሩ የሚችሉ ነገር አይደሉም። እኔ እስከማውቀው ድረስ አይጥና ድመት ተቃቅፈው አንድ ላይ በፍቅር መኖር እንደሚችሉ ተስለው ያየሁት በጀሆባ ምስክሮች (Jehovah’s Witness) መፅሔት ላይ ነው።

በእኔ እምነት በሀገራችን ህዝቦች መሀል መሰረታዊ የሆነ ልዩነት የለም። በሀገራችን ያለው መሰረታዊ ችግር በልሂቃኑ መካከል ያለውን ያለመተማመን፣ የስልጣን ጥመኝነት፣ ጠባብነት፣ ጥላቻ እና ቂም በቀል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ዛሬ ላይ ለሚታው ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን የፊውዳሊዝም እና የባለአባታዊ ስርዓተ ማህበር የፈጠረው የአስተሳሰብ ሰንካላነት ውጤት ነው።

ሶስተኛው ፖለቲካዊ አሰላፍ ከላይ ያሉትን ሁለቱንም ጫፎች በማስቀረት ወይም በማስታረቅ ለዘብተኛ የሆነ አቋም የሚያራምዱ የተካተቱበት ነው። የእድል ጉዳይ ሆኖ በዚህ ጎራ የሚመደቡ ኃይሎች አንድም በአግባቡ የተደራጁ አይደሉም፤ አንድም የተደራጁትም ነጥረው ለመውጣት አልቻሉም። ለዚህ እንደምክንያት ሊሆን የሚችለው ከላይ በተገለፁት ሁለት ፅንፍ አሰላለፎች በእኩል ስለሚመቱ ነው። በእኔ እይታ መካከለኛ አቋም ከሚያራምዱት ፓርቲዎች መካከል አንድነት ፓርቲ አንዱ ይመስለኛል። ነገር ግን አንድነት በዚህ መስመር ለመጓዝ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል። በወግ አጥባቂዎቹ በእኩል ለዘብተኛ እና ሁሉንም አቃፊ የሆነ ፕሮግራም ያለው በመሆኑ፤ እንዲሁም ብሄር (ክልል) ተኮር ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመስራቱ ምክንያት በማድረግ ወደዚያኛው ጥግ፣ ወደ ግራ ዘምም ጎራ እንደተቀላቀለ አድርገው ዘመቻ ያካሄዱበታል። በሌላ በእኩል ደግሞ በብሄር የተደራጁ ኃይሎች የአማራ ብሄር ወይም የከተሜ ድርጅት አድርገው በመሳል ሁለቱን ጫፎች ለማቀራረብ በሚያደርገው ሙከራ ላይ ውሀ ይቸልሱበታል።

በእውነቱ፣ በዚህ ሰዓት የሚፈለገው የእነዚህን ሁለት ጫፍ የሆኑ ኃይሎችን ልዩነቶችና ስጋቶች የሚያስወግድ መካከለኛ የሆነ መንገድ የያዘ፤ ሁሉም ኃይሎች ሊያሰባስብ የሚችል አስታራቂ አቋም ያለው ፖለቲካዊ ኃይል ነው። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መድረክ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ተዋህደው ወደዚህ ደረጃ ይሸጋገራሉ የሚል ተስፋ ነበር። ነገር ግን በመሪነት ደረጃ ባሉ ልሂቃን ምክንያት ሊሳካ አልቻለም። ይሄ በቀላሉ እንደማይሳካ ግልፅ እየሆነ ሲመጣ በመድረክ አባል ፓርቲዎች መካከል የተጀመረውን ውህደት በማጠናከር ዓረና ከአንድነት እና ከደቡብ ህብረት ጋር እንዲዋሀድ ስራ ተጀምሯል። ይሄ ነው እንግዲህ ድመትን ከአይጥ ጋር እንደማዋሃድ ተደርጎ በህወሀት ሰዎች ዘንድ እየተተቸ ያለው። የአረና እና የአንድነት ውህደት መድረክ ከተመሰረተ ጀምሮ ሲታሰብ የነበረ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሊሳካ አልቻለም። ከአንድነት ጋር ውህደት እንዲኖር የምፈልግበት ዋናው ምክንያት አንድነት በሀገራችን ካሉት የተቃውሞ ኃይሎች ጋር ሲነፃፀር በፕሮግራም እና በተወሰነ መልኩ በአመለካከት ደረጃ ለዘብተኛ የሚባል አቋም ያለው ፓርቲ ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው።

ነገር ግን ዓረና የውህደት ጥያቄ ባቀረበት ማግስት አንድነት ከመኢአድ ጋር አስቸኳይ የውህደት እንቅስቃሴ መጀመሩ፤ በዓረና በእኩል ደግሞ ከአንድነት ይልቅ ከደቡብ ህብረት ጋር ውህደት እንዲኖር የሚፈልጉ ወገኖች መኖር፤ በዚህ ሀገር ያለውን የእንተባበር እንቅስቃሴ የልብ እንዳልሆነ አንዱ ማሳያ ነው።

አንድነት ከመኢአድ ጋር ለመዋሀድ መፈለጉ በራሱ ችግር የለውም፤ ነገር ግን በማን ፕሮግራም ነው የሚዋሃደው? የሚለው ጉዳይ ወሳኙ ነገር። አሁን ያለው የአንድነት ፕሮግራም የግለስብና የቡድን መብቶችን ባገናዘበ ሁኔታ የተዋቀረ፤ በብዙ መልኩም ተራማጅ የሚባል ዓይነት ነው። መኢአድ በዚህ ፕሮግራም የሚዋሃድ ከሆነ ጥሩ ለውጥ ይሆናል። ቀጥሎ ከዓረናም ሆነ ከደቡብ ህብረት ጋር ሊኖር የሚችለውን ውህድት እንዲሳካ መንገድ የሚጠርግ ይሆናል። አንድነት ወደኋላ ተመልሶ በመኢአድ ፕሮግራም የሚዋሀድ ከሆነ ግን የተመደውን አሰላለፍ ከማጠናከር የዘለለ አዲስ ዓይነት የኃይል አሰላለፍ የሚያመጣ አይሆንም። መኢአድ በብሄር ወይም በክልል የተደራጁ ኃይሎች ላይ ያለው አመለካከት እጅግ የተዛባ፤ ወግ አጥባቂ እና ነባራዊውን እውነት ያላገናዘበ የሚባል ዓይነት ነው። ከዚህ አንፃር ካየነው ለአንድነት የብሄርንና የጎሳን ልዩነት በቅጡ ከማያውቅ ወይም ሊያውቅ ከማይፈልግ ፓርቲ ጋር መዋሀዱ የሚፈይድለት ነገር ያለ አይመስለኝም።

ዓረናም ቢሆን ከደቡብ ህብረት ጋር የሚያደርገው ውህደት ሀገራዊ ፓርቲ የመሆን ፍላጎቱ እውን ከማድረጉ ውጪ ያን ያህል ትርጉም ያለው ውህደት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ሰሜንና ደቡብ ላይ ቆመው እንዋሃድ ቢሉ፤ ሁለት ፍቅረኞሞች በአጥር ተንጠራርተው ለመሳሳም የሚያደርጉትን ሙከራ ያህል አስቸጋሪ ይሆናል። ምክንያቱም መሀሉን ለማገናኘት ረጅም ጊዜ እና ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>