ዛሬ ማለዳ ሜክሲኮ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡት የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ሊቀመንበር፣የብሄራዊ ምክር ቤት አባሉ ዘላለም ደበበና ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ በፖሊስ የአስራ አራት ቀን የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ፍርድ ቤቱ የአስራ አንድ ቀን ጊዜ ቀጠሮ ለፖሊስ በመፍቀድ በእስር ቤት እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል፡፡
ፖሊስ በአንድነት አባላት ላይ ባቀረበው ክስ ‹‹ለቅስቀሳ ባልተፈቀደ ቦታ ሲቀሰቅሱ አግኝቻቸዋለሁ፣የተፈቀደላቸው ለሰላማዊ ሰልፍ እንጂ ለቅስቀሳ አይደለም በማለት ዋስትና እንዲከለከሉለት ደግሞ ‹‹ካልታሰሩ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ሁከት ሊፈጥሩ የሚችሉ በመሆናቸው በእስር እንዲቆዩ ይደረግልኝ››ብሏል፡፡
ተከሳሾቹ በበኩላቸው ለፍርድ ቤት ባቀረቡት መከራከሪያ‹‹ፖሊስ ባላቸው ቦታዎች አለመቀስቀሳቸውን፣ሰልፉ እውቅና የተሰጠው በመሆኑ ሁከት መፍጠር የሚለው አያስኬድም ብለዋል፡፡ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ‹‹ሰላማዊ ሰልፉ በሸገር ሬዲዩ እየተዋወቀ ፖሊስ መቀስቀስ አትችሉም ማለቱ አስገራሚ ሆኖብኛል››ብሏል፡፡