Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

ጉዞ ወደ ምድር ጥግ (ሦስተኛ ክፍል)

$
0
0

አውሮፕላኑ ወደ ምድር ዝቅ እያለ መሆኑን አስተናጋጇ በመናገር ላይ ናት፡፡ የምናርፈው ባንዳር ሰሪ ባጋዋን የሚባለው የብሩናይ ዓለም ዐቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ ብሩናይ እስከ ዛሬ ስሟን እንኳን ሰምቻት የማላውቅ ትንሽ የደቡብ እስያ (ኦሺንያ) ሀገር ናት፡፡ ወደ እርሷ ለመድረስ ከዱባይ ተነሥተን የ8 ሰዓት ከ15 ደቂቃ በረራ ነው ያደረግነው፡፡ ብሩናይ ማለት ‹የሰላም ሀገር›› ማለት ነው ይላሉ ሀገሬዎቹ፡፡ ሲያቆላምጧትም ‹ብሩናይ ዳሩ ሳላም› ይሏታል – ብሩናይ ሀገረ ሰላም ለማለት፡፡

ይህች በደቡብ እስያ በቦርኒዎ (Borneo) ደሴት ላይ የምትገኘው ትንሽ ሀገር ከዋናው የእስያ መሬት በቻይና ባሕር በኩል ትለይና በሌላዋ ክፍሏ ደግሞ ከኢንዶኔዥያና ማሌዥያ ጋር ትዋሰናለች፡፡ የቦርኒዎ ደሴት የሚገርም ነው፡፡ ከብሩናይ በቀር በደሴቱ ላይ ሌላ ሉዓላዊ ሀገር የለም፡፡ ቦታውን ማሌዥያና ኢንዶኔዥያ ተካፍለውታል፡፡

ብሩናይ በንጉሣዊ አገዛዝ የምትተዳደር ሀገር ናት፡፡ ሡልጣኑ የሀገሪቱ የመጨረሻው ወሳኝ አካል ነው፡፡ የመንግሥቷ ይፋዊ እምነት እስላምና መሆኑን የአየር መንገዱ መጽሔት ይናገራል፡፡ የንጉሡ አንደኛው ተግባርም እስልምናን መጠበቅና ማስተማር መሆኑን ይገልጣል፡፡ በነዳጅ ምርቷ የምትታወቀው ይህቺ ትንሽ ደሴት ከ16ኛው መክዘ ጀምሮ ወደ አካባቢው በሄዱ የአውሮፓ አሳሾች ትታወቅ ነበር፡፡ በተለይም ደቾች ከጥንት ጀምረው የንግድ ግንኙነት መሥርተውባት ነበር፡፡ በማጅላን የ1521 እኤአ የዓለም ጉዞ ወቅት ስፔኖች ወደ አካባቢው መጥተው ያዟት፡፡ የሀገሬው ሕዝብ ግን በ1578 ስፔኖቹን ተዋጋቸው፡፡ በኋላ ደግሞ በ1888 ሀገሪቱ በእንግሊዝ ጥብቅ ቁጥጥር ሥር ሆነች፡፡ በ1959 ደግሞ የጃፓኖች የወታደር መሥፈሪያ ተደረገች፡፡

በ1984 ከእንግሊዝ ነጻነቷን ያገኘችው ብሩናይ እጅግ በጣም ሀብታም ሀገር ሆናለች፡፡ በሰብአዊ ዕድገት መለኪያ መሠረት ከደቡብ ኤስያ ሀገሮች ሁሉ ከሲንጋፖር ቀጥላ የምትጠቀስ ሀገር ነች፡፡ የአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ከሕዝቧ ጋር ሲነጻጸር ብሩናይ በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ናት፡፡ በ2011 የሀገሪቱ ብድር ዜሮ ነበር፡፡ በዚህ ትፎካከራት የነበረችው ሊቢያ ነበረች፡፡ በፎርበስ መጽሔት መሠረትም ብሩናይ በዓለም አምስተኛዋ ሀብታም ሀገር ናት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የሕዝቧ ብዛት 408 ሺ ብቻ መሆኑን አትርሱ፡፡ አሁን ሀገሪቱን የሚመራው ሥርወ መንግሥት ላለፉት 600 ዓመታት ሳይቆራረጥ ከልጅ ወደ ልጅ እየወረደ መምራቱን በኩራት ይነግሯችኋል፡፡

አሁን ወደዚህች ሀገር እየወረድን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እዚህ ቢያንስ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል እቆያለሁ፡፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ምሥራቅ ስትጓዙ ቀኑ ከእናንተ እየቀደማችሁ ይሄዳል፤ ወደ ምዕራብ ስትጓዙ ደግሞ ጨለማው እየተከተላችሁ ይሄዳል፡፡ እንዲያውም አንድ ፓይለት አንድ ጊዜ ‹‹ለመሆኑ እኛ እንዴት ነው መጾም ያለብን? ከኢትዮጵያ ወደ ምዕራብ ስንሄድ ሌሊቱ ይረዝማል፤ ወደ ምሥራቅም ስንሄድ ቀኑ ይረዝማል፤ የትኛውንስ ሰዓት ነው መጠቀም ያለብን? የተነሣንበትን ነው ወይስ የደረስንበትን?›› ሲል ጠይቆኝ ነበር፡፡ አሁንም እኔ ግራ ገብቶኛል፡፡ ለመሆኑ የሐዋርያት ጾም ተፈትቷል ወይስ እንደቀጠለ ነው?
ከአውሮፕላኑ ወርደን ወደ ዕንግዳ ማረፊያው ስንገባ ግድግዳው ሁሉ የሀገሪቱን መልክዐ ምድር፣ የንጉሣዊውን ቤተሰብ ተግባር፣ ታሪካቸውንና የወግ ዕቃዎቻቸውን በሚያሳዩ ትላልቅ ፖስተሮችና ፎቶዎች ተሞልቷል፡፡ ግን እናንተየ በኛ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የተጠና የሀገሪቱን ገጽታ በሚገባ የሚያሳይ ነገር የምናየው መቼ ነው? እዚህና እዚያ ከተለጠፉ፣ ተከታታይነትም ሆነ ተዋሕዶ ከሌላቸው ፎቶዎች ወጥተን፤ የታሰበበት፣ በባለሞያ የተዘጋጀና ሀገሪቱን ሊያሳይ የሚችል የሥዕል፣ የፎቶና የባሕል ዕቃዎችን ትርዒት አውሮፕላን ማረፊያችን ላይ መቼ ነው የምናየው? ከአውሮፕላኑ ወጥታችሁ በዋሻው በኩል ወደ ዕንግዳ ማረፊያ እስክትደርሱ ድረስ ግራ ቀኙ ሁሉ መልእክት ብቻ ነው፡፡ እንደ እኔ ያለው ተላላፊ መንገደኛ ሀገሪቱን ለመጎብኘት ባይችል እንኳን በአጭሩ ዐውቋትና ሌላ ቀን ለመመለስ ቃል ገብቶላት ይሄዳል፡፡
ዕንግዳ ማረፊያው ስትደርሱ ደግሞ ስለ ሀገሪቱ የሚገልጡ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ፖስተሮች፣ ካርታዎች እዚህም እዚያም ተቀምጠው ውሰዱኝ ውሰዱኝ ይሏችኋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሀገሬ አየር መንገድ ከሌላ ሀገር ስመለስ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ በተለይ ከአሜሪካ መልስ፤ አውሮፕላኑ ውስጥ ስትገቡ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ታይምስ መጽሔት ይሰጣችኋል፡፡ ሀገሩ ናፍቆት ለሚመጣ ሰው እነዚህ ምንድን ናቸው? ምናለ ቢያንስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ (መቼም ሌላውን እንዳልል ዕዳው ብዙ ነው ብዬ ነው) እንኳን ቢያድሉ?
ሌላ ሀገር ያላየ ሰው በሁለት ነገር ዕድለኛ ነው፡፡ በአንድ በኩል ‹‹በዓለም አንደኛ በአፍሪካ ሁለተኛ ነን›› የተባለውን በሰላም ተቀብሎ በደስታ ለመኖር ይቻለዋል፡፡ እኔ ወደ ኬንያ በኩል እስክበርር ድረስ ‹‹ለምለሟ ሀገሬ፣ ጫካ የሞላብሽ›› የሚለውን እንጉርጉሮ በደስታ እሰማው ነበር፡፡ ኋላ ተበላሸሁ፡፡ በሁለተኛ ነገር ሌላ ሀገር ያላየ ሰው አይናደድም፡፡ እነዚያ በ30ዎቹ፣ 40ዎቹና በ50ዎቹ ወደ አውሮፓ እየሄዱ ይማሩ የነበሩ ልሂቃን እዚያ ያዩትን ከሀገራቸው ጋር ያነጻትሩና ‹‹ምን ነካን›› እያሉ በብስጭት ስንት መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ እነ ከበደ ሚካኤል ‹ጃፓን እንዴት ሠለጠነች›› የሚል መጽሐፍ ሲጽፉ ዓላማቸው ከጃፓን ሥልጣኔ እንድንወርስ ነበረ፡፡ የዚያን ዘመን ሰዎች ‹‹ሥልጣኔ ምንድን ነች›› ሲሉ ሞያ ከጎረቤት እንድንማር ነበር፤ እነረ ‹አርአያ› የተጻፉት ማኅበረሰቡን ለመሞገት ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የምታክል የታሪክ፣ የእምነትና የተፈጥሮ ሀብት ሀብታም ሀገር ከእርሷ ያነሰ ታሪክና ሀብት ባላቸው ሀገሮች ተበልጣ ማየት ዋንጫ ከማጣት በላይ ጉበት ይልጣል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እነዚህ ባለ ሥልጣናት ለልምድ ልውውጥ እየተባለ ብዙ ሀገር ይዞራሉ፡፡ ለመሆኑ ምን ዓይተው ነው የሚመጡት? ምንስ ተምረው ነው የሚመለሱት? ወይስ ሌላ ውጭ ሀገር አለ እነርሱ ብቻ የሚሄዱበት፡፡ አለቆች ውጭ ሀገር ደርሰው ሲመለሱ ብዙ ጊዜ አለባበሳቸውና ስልካቸው እንጂ አመለካከታቸውና አሠራራቸው ሲለወጥ አይታይም፡፡ ቢያንስ ለመሥሪያ ቤታቸው ሰዎች ያዩትንና የሰሙትን በማካፈል እንኳን ዕውቀትና ልምድ አያሸጋግሩም፡፡ ሲመለሱ እንደዚያው እንደሄዱት ሆነው ነው፡፡ የቢሮአቸውን አሠራር እንኳን ለመቀየር አይሞክሩም፡፡
ምሁራኑስ ቢሆኑ፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ውጭ ሀገር ሄደው ሠርተው መጡ ይባላል፡፡ ከተማሩበት ዩኒቨርሲቲ አሠራር የተሻለ ነገር ይዘው የሚመጡት ግን ስንቶች ናቸው? ከተማሪዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የፈተና አወጣጣቸው፣ የማስተማር ዘዴያቸው፣ የውጤት አሰጣጣቸው ያው እንደ ድሮው ነው፡፡ ንብ እንኳን የተሻለውን አበባ ቀስማ ማር ትሠራለች፡፡ እንዴት ሀገርን በሥልጣንም በዕውቀትም የሚመራ ሰው የተሻለ አሠራር ከሌላው አይቀስምም፡፡
ከውጭ ሀገር መጥተው ሀገር ቤት ድርጅት የሚከፍቱ አብዛኞቹ ዳያስጶራዎች ገንዘባቸውን እንጂ የነበሩበትን ሀገር አሠራር ይዘው አይመጡም፡፡ መሣሪያው የውጭ፣ ቅኝቱ ግን የኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ ሆቴሉ ‹‹ኒውዮርክ ሆቴል›› መስተንግዶው ግን የአራት ኪሎ ሆኖ ቁጭ፤ ካፌው የስታር ባክስ መስተንግዶው ግን የሠፈራችን ሻሂ ቤት ይሆንባችኋል፡፡ ሌላ ውጭ ሀገር ይኖር ይሆን?
እንዲህ እያሰብኩ ቆይቼ ቀና ስል ኢትዮጵያዊ መልክ ያየሁ መሰለኝ፡፡ በማያውቁት ሀገር የሚያውቁት ሰው ማግኘት፣ በበረሃ ውስጥ የምንጭ ውኃ እንደማግኘት ነው ይባላልና ኮሽታ እንደሰማ እንሽላሊት ነቅቼ ማየት ጀመርኩ፡፡ ኧረ እንዲያውም የሐበሻ ልብስ ነገርም ያየሁ መሰለኝ፡፡
አንዲት ወጣት፣ የሐበሻ ነጠላ የመሰለ ሻርፕ ደረብ አድርጋ ወደ እኔ በመምጣት ላይ ናት፡፡ መቼም ማርስ ላይ ሰው አለ ከተባለ የሚገኘው አበሻ መሆን አለበት፡፡
ብሩናይ- ዳሩ ሰላም

Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>