Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

ሚድያና መዘዙ: ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብር ኤል

$
0
0

ከዚህ ቀደም ያልሆነ ወይንም ያልበረ ሆኖ ሳይሆን እንደው በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ የሚገኘው የዓለማችን ገጽታ ሳያሳስቦት አይቀርም። እውነት ነው የቴሌቪዥን መስኮት በከፈቱ ቁጥር ነውጥና ሁከት እንጅ ሰላምና ልማት የማይታሰቡ ሆነዋል። ሕዝብ በሕዝብ፣ ሕዝብ በመንግሥት፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ የሚያምጽበትና የሚነሱበት አስደንጋጭ ክስተቶችም የመገናኛ ብዙሐን ሁለመና ቀስፈው ወደ ሰፊው ውቅያኖስ ይዘው ከመውረዳቸው በተጨማሪ የሰው ልጅ እልቂትና ደም መፋሰስ ሰበር ዜና ሆኖ ሰሚ ጆሮ ማጨናነቅ ተጣጥፎ ቀጥለዋል። ይሁንና በዚህ ሁሉ ሁከት፣ ትርምስና ብጥብጥ የዓለም ማህበረሰብ ልብ በመስለብ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው የሚድያ ድርሻ ልብ ብለው አስተውሎዋል?

በኢንተርኔት አገልግሎት ብቸኛ ተጠቃሚና ደስተኛ የሆነው ሰፊው ሕዝብ ብቻ ለመሆኑ ስንቶቻችን እንደምንስማማ እርግጠኛ ባልሆንም የኢንተርኔት አገልግሎት ለሰፊው ሕዝብ ጉልበት ሲሆን ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የዓለማችን ግዛት በፖለቲካ ወንበር የተቀመጡ ባለ ስልጣናት ደግሞ የእግር አሳት ሆኖ የሚይዙት የሚጨብጡት ሲያሳጣቸው እየተመለከትን ነው። የኢንተርኔት አገልግሎት ሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ያክል ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ከኤሽያ እስከ አፍሪካ የሚገኙ ዲሞክራቱም አምባገነኑም እኩል እያርበደበደ፣ እያንጰረጰረ፣ ጉልበት እየፈታና አዳራሻሾቻቸውም እያናወጠ ይገኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ተራርቆና ተቆራርጦ የነበረው የዓለም ማሕበረሰብ፤ የአንዲት አገር ሕዝቦች ከኢንተርነት አገልግሎት የተነሳ እርስ በእርስ መነጋገር ወደሚችልበት ደረጃ ቢመጣም መንግስታት ደግሞ በፊናቸው ይህን መነጋገር ተከትሎ የሚመጣ አንድነትንና ሕዝብረት ለመስበር ብሎም ለመበጣጠስ “ሚድያ” በመባል የሚታወቀው ጉልበታም መሳሪያ በመጠቀም የሚመሩት ሕዝብ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የሚዘውሩበትና የሚፈልጉትን ብቻ የሚመግቡበትን አስተማማኝ ጡንቻ ከመጠቀም የባዘኑበት ደቀቃ የለም። የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ጠንካራ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁ አሜሪካዊ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ “Propaganda is to a democracy what violence is to a dictatorship.” ሲሉ እንደገለጹት።

አሁን ባለው ነባራዊ የዓላማችን ሁኔታ “ሚድያ” ጸረ ሕዝብ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ሚድያ መንግስታት የሚመሩትን ሕዝብ የሚገርፉበት ጅራፍና አልፎ ተርፎም ጦርነት አብሳሪ፣ ኃያላኑ የሰው ሀገር ለመውረር ሲነሱም “ሚድያ” እንደ ጠቋሚ ኮምፓስና የጦርነት ፊት አውራሪ ሆኖ ሲያገለግል ያየነውና እያየነው ያለ የባለ ስልጣናት አፍ ነው ቢባል ያንሰዋል። ስለሆነም “ሚድያ ንብረትነቱ የሕዝብ ነው!” የሚለው የነቀዘ አባባል ከእውነት የራቀ አባባልና ከመፎክር አልፎም እውነትነት የሌለው ሕጋዊ ውሸት ነው። ሚድያ (መንግስትም ሊሆን ይችላል ላይሆንም ይችላል) ብቻ ግን ኃያላን/ባላሀብቶች በሕግ የሚዋሹበት መሳሪያ ነው።  ለነገሩ “Mainstream Media” ተብሎ መጠራቱ ቀርቶ “Mass Murdering Media” ከተባለ ዓመታት አስቆጥሮ የለ።

ወደ ወቅታዊው ሁኔታ ስንመለስ ባሳነፍነው ሳምንት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር ዴቭድ ካመሮን ጋር አርባ ደቂቃዎች የፈጀ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና በደማስቆ የኬሚካል የጦር መሳሪያ (Biological Weapon) ጥቃት ሰለባ የሆኑ አንድ ሺህ አራት መቶ የሚደርሱ የዶማስቆ አከባቢ ነዋሪዎች የስሪያ መንግሥት በሻር አል አሳድ ኃላፊነቱን ይወስዳል በሚል መተማመናቸው፤  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሐላፊ የሆኑት ጆን ኬሪ የስሪያ መንግሥት ባዮሎጂካል ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል ሲሉ ደጋግመም መግለጫ መስጠታቸው፤ የእንግሊዝ ፓርላመትን እንግሊዝ በስሪያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ማድረጉ፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ የራሽያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ አለኝ የምትለውን ማስረጃ በተባበሩት መንግሥታት ለጸጥታ ምክር ቤት ማስረጃዋን እንድታቀርብ መጠያቀቸው፤ አጀንስ ፍራንስ ፕረስ ስማቸው ያልተገለጸ አንድ የስሪያ የመንግስት የደህንነት ባለሥልጣን ጠቅሶ እንደገለጸው ስሪያ በማንኛውም ቅጽበት ለሚሰነዘርባት ማንኛውም ዓይነት ጥቃት አጸፌታ ምላሽ ለመስጠት/ራስዋንም ለመከላከል በተጠንቀቅ እንደምትገኝ የተገለጸበት ሁኔታ እንዲሁም ረፋዱ ከብዙ ግርግር በኋላ ፕሬዝዳን ባራክ ኦባማ የኮንግረሳቸው ፍቃድ እንደሚሹ ማሳወቃቸውን ሁኔታው እያጋጋለውና እያወሳሰበው ይገኛል።

ጥያቄው እውነት የስሪያ መንግሥት በገዛ ሕዝቡ ኬሚካላዊ የጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ለመመለስ ምዕራባውያን መንግሥታት በማዕከላይ ምስራቅ የሚከተሉትን ፖሊሲና የተያያዙት የፖለቲካ አካሄድ በጥሞና ከማየትና ከማጥናት አልፎ ስሪያ ምድር ድረስ በመሄድ ነገሩን ማጣራት የሚጠይቅ ነው ብዬ አላምንም። ይህ ደግሞ በግሌ ያመጣሁት መገለጥ ሳይሆን በሞያው የተካኑ የፖለቲካ ተንታኞች የሚሉትንና የሚስማሙበት እውነታ ነው። “ሚድያ” በስሪያ ጉዳይ ላይ እየተጫወተው ያለው ከፍተኛ ሚናና መጠነጠ ሰፊ ዘመቻ ከማየታችን በፊት ግን እየሆነ ስላለው ሀገራትና መንግስታት የማውደም ዘመቻ በአግባቡ ለመረዳት ያክል ቀደም ብለው የምዕራባውያን መንግስታት ሰለባ የሆኑ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች (በነዳጅ) ሀገረ ሳዳም ሁሴን ኢራቅ ጨምሮ በአፍጋኒስታንና በሊብያ የሆነውን ከብዙ በጥቂቱ ማየቱ መልካም ይመስለኛል።

በፖለቲካ ሊቃውንት ዘንድ በአህጽሮተ ቃል PRS/N-PRS በማለት የሚታወቀው (Problem-Reaction-Solution/ NoProblem-Reaction-Solution) ጥቅምን የማግበስበስ ስልት በምዕራባውያን ዘንድ በተለይ በአሜሪካና በእንግሊዝ መንግስታት በሚገባ ተግባራዊ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ይህ ማለት መስከረም  11/2001 በአሜሪካ በኒውዮርክ ከተማ ግዙፉ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል በደረሰ ጥቃት የአሜሪካ መንግሥት ቀደም ብሎ በአፍጋኒስታን ጸረ ሶቬት ሕብረት ያሰለጠነው፣ ያስታጠቀውና ወልዶ ያሳደገው በኦሳማን ቢንላደን የሚመራ አልቃይዳ ነው በማለት በይፋ ሲያሳውቅ ድርጊቱም በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ በመቀስቀሱ የአሜሪካ መንግሥት ይህን የሕዝብ ቁጣና ከፍተኛ ድምጽ በመጠቀም (የሚፈለገውም ይህ ነበርና) አልቃይዳ ፍለጋ ተብሎ አፍጋኒስታን እንዳልነበረች አድርጓታል። (የመስከረም 11 ክስተት የአሜሪካ መንግሥት የልቡን ለማድረስ ራሱ የፈጸመው ድርጊት ነው አላልኩም።)

እንደ ጀስ ቨንቱራ (ከ 1999 – 2003 እ.አ.አ የሚንሶታ አገረ ገዢ ነበር ፖለቲከኛና ጸሐፊ) እምነትና ትንተና አሜሪካ አፍጋኒስታን የወረረችበት ምክንያት ለCNN በሰጠው ቃለ ምልልስ እንዲህ ይላል “we are in Afghanistan because there is a Trillion dollars worth of Lithium there.” አክሎም ንጥረ ነገሩ የሚሰጠውን ጥቅም እንደሚከተለው ያብራራዋል “Now, what is lithium used for? Every cell phone, every computer, and soon to be electric cars.”

ወደ ኢራቅ ልሻገር። ከ2003 እ.አ.አ ጥቃት በኋላ ምድሪቱ የቀረላት ነገር አለ ተብሎ መናገር የሚቻል አይመስለኝም። ወድማለች! ተብሎ በአራት ነጥብ ብንዘጋው የሚያግባባን ይመስለኛል። ግን ለምን? ማለቱ ግን ተገቢ ይመለኛል። እስቲ አሜሪካዊው ባለ አራት ኮከብ ጄነራል ዌስሊ ክላርክ በ2003 እ.አ.አ “Winning Modern Wars” በሚል ርዕስ ለህትመት ባበቁት መጽሐፋቸው በግልጽ ያሰፈሩትን እንመልከት።

“As I went back through the Pentagon in November 2001, one of the senior military staff officers had time for a chat. Yes, we were still on track for going against Iraq, he said. But there was more. This was being discussed as part of a five-year campaign plan, he said, and there were a total of seven countries, beginning with Iraq, then Syria, Lebanon, Libya, Iran, Somalia and Sudan.” ”Winning Modern Wars” (ገጽ 130)

ክላርክ በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት የዋሽንግተን/የፔንታጎን ባለ ሥልጣናት ሶማሊያን ጨምሮ ሁለት በሰሜኑ ክፍል የሚገኙ የአፍሪካ አገራት፤ አራት የማዕከላይ ምስራቅ መንግስታት በአጠቃላይ በአምስት ዓመት ውስጥ ሰባት መንግስታት የማውደም/የመውረር ዕቅድ እንዳላቸው አስፍረዋል። ይህን ዕቅድ ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፕላንም ቀድሞ ያለቀ ነው። እዚህ ላይ N-PRS (No Problem-Reaction-Solution) በኢራቅ ላይ እንዴት እንደሰራና የሚድያ ድርሻም  ምን እንደ ነበር እንደመልከት።

ኢራቅን ለመውረር ሌላ ፍንዳታ አላስፈለገም። ፔንታጎን “የሳዳም መንግስት የጅምላ ጨራሽ አውዳሚ መሳሪያ ባለ ቤት ነው! ይህ ደግሞ ለዓለማችን ሰላም ጠንቅ በመሆኑ የዓለም ማህበረሰብ ዋል እደር በሌለበት ድርጊቱን ያወግዘው ዘንድ ይገባል። አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል!” ሲል በሚድያ የሚያሰጨው ፕሮፖጋንዳ ብቻ የዓለም ማህበረሰብ ቀልብ በመሳብና በጭንቀት በመወጠር ሕዝብ ደግሞ በፊናው ከሰማው አስደንጋጭ ዜና የተነሳ “ምን ነው የዓለም መንግስታት ተባብረው ይህን ሰው (ሳዳምን) ባጠፉልን” ሲል በሰጠው ምላሽ ይሁንታ ያገኙ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታት አገሪቱ እንዳልነበረች የፍርስራሽ ክምር አድርጓታል። የዶላር ከረንሲ በተመለከተ የጠነሰሰው ጥንስስ ብቻም ሳይሆን ድሮም ሰውዬም ለምዕራባውያን አጀንዳ የሚመች ሰው አልነበረምና በሕግ ገመድና አንገቱን አገናኝተው በአደባባይ አሰናብተዉታል። ታድያ ከዚህ ሁሉ ግርግርና ትርምስ በኋላ ሰውዬው የተባለው ጅምላ ጨራሽ አውዳሚ መሳሪያ ተገኘበት ሆይ? ለሚለው ጥያቄ አይደለም ጅምላ ጨራሽ አውዳሚ መሳሪያ ይቅርና መርፌም አልተገኘበትም። እና? እናማ እርስዎ ያልሰሙ እንደሆነ አላውቅም እንጅ በአንድ ወቅት አሜሪካዊ አቦይ ስብሃይ ዲክ ቼነይ “እና ምን ይጠበስ ነው!” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

እስቲ ወደ ሊብያ ደግሞ እንለፍ። ሚድያም አለ “በዛሬው ዕለት የሊብያ ታጠቂ ኃይሎች ባልታጠቁ ዜጎች በከፈቱት ተኩስ … የሚያህሉ ጹሐን ዜጎች መቁሰላቸውን የዓይን ምስክሮች አረጋገጡ” ሙቀቱ ጨመር አደረጉትና (ሚድያዎቹ ማለቴ ነው) በሚቀጥለው ቀን ደግሞ “አንባገነኑ የሊብያ ገዢ ጋዳፊ … የሚያህሉ ንጹሐን ዜጎች ገደሉ” ሙቀቱ እንደ ጨመረ ነው “ኧረ የሰው ያለህ! ጋዳፊ ንጹሐን ዜጎች ጨረሱ ኡ ኡ ኡ … ምን ነው የዓለም መንግሥታት ዝም ያሉ?” ወደ ማለት ተደረሰ። የትኛው ዓለም አቀፍ ሕግ ይህን ያደርጉ ዘንድ እንደሚፈቅድ ለጊዜው ለማወቅ ባይቻልም በአሜሪካ የታገዘ የNATO ጦር ሊብያን እስክታስነጥስ ድረስ አጨሳት። ነፍስ ይማር! ጋዳፊም ሸሽተው መሸሽ አልተቻላቸውም ተይዘው መሬት ለመሬት እየተጎተቱ ክፉኛ ተደብድበው ተገደሉ። ተልዕኮ ተሳካ!

“ኧረ ጋዳፊ ንጹሐን ዜጎች ጨረሱ ኡ ኡ ኡ የትድግና ያለህ!” የሚለው የሚድያ ጭኸት አይደል ጋዳፊና መንግሥታቸው ጠራርቆ የወሰደ። ቁምነገሩ በሚድያ እንደተነገረን ጋዳፊን የቀሰቀሰ፣ የተነኮሰና ያነሳሳ “የዓረብ ስፕሪንግ” በመባል የሚታወቀው ሕዝባዊ ዓመጽ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆኑ በእውነቱ ነገር “ሚድያ” በእርስዎ ላይም ስራውን ሰርተዋል ማለት ነው። “ይሄው ጋዳፊ ንጹሐን ዜጎች እየገደለ ነው!” ተብሎ ለክስም ሆነ ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲያመች ጋዳፊን ዕንቅልፍ ለመንሳትንና ዕረፍት ለማሳጣት ቀደም ብሎ እንደተገለጸ “ይሄው” ለማለት እንዲያመች ጋዳፊን በተጨባጭ የሚያሳስት ተኩሶ የሚያስተኩስ ገድሎ የሚያስገድል ልዩ ኃይልማ ተሰማርተዋል! ብለው ከጠራጠሩ ግን ነቄ ኖት ማለት ነው። በሊብያ የሆነው ይህ ነው ይላሉ እንግዲህ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነንና እንዴት እንደሚሰራም የሚያውቁበት ሊቃውንቱ። የእኔና የእርስዎ መንቃት ግን አይደለም ላይመለስ ያሸለበውን ጋዳፊ በቁሙ ያለውን አሳድ የሚታደግ ለመሆኑ እጠራጠራለሁ። ለማንኛውም ወደ ስሪያ እናምራ፥

መቼም ተጋብቶ የፌርማው ቀለም ሳይደርቅ መፋታት እንደ ሚድያ ያለ የሚያምርበትና የሰመረለት ማንም የለም። እስቲ አሁን ደግሞ የስሪያና የምዕራባውያን ሚድያ ጊዜያዊ ጋብቻ ምን እንደሚመስል እንመልከት። የእስራኤል የስለላ ድርጅት “ሞሳድ” ደረሰበት እየተባለ ከሚያናፈው የዘለለ ያለ አንዳች ተጨማጭ ማስረጃ/መረጃ የኦባማ አስተዳደር የጦር መርኮቦችን ሲያንቀሳቅስ ሚድያዎች በለው! ደብድበው! ድፋው! አጭሰው! ቀቅለው! ፍለጠው! ቁረጠው! በማለት ነገሩን ከማራገብ በመቆጠብ የአሜሪካ መንግሥት በማዕከላይ ምስራቅ ያለው የረጅም ጊዜ ፖለቲካዊ ዕቅድ በማውሳት ወይም በመምዘዝ በስሪያ ላይ ያንጃበበው የጥፋት ደመና ከመነሻው መንስኤው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማጣራት (ለመመርመር) ጥረት ያደረገ አንድም የ“ሚድያ” ተቋም ፈልጎ ለማግኘት አልተቻለም።

“የስሪያ መንግሥት” ቀጥሎ ደግሞ “በሻር አል አሳድ” የሰሙኑ የምዕራባውያን ሚድያ የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖዋል። በቀንም በውድቅት ሌሊትም የሚሰሙት ቃል ከተጠቀሱ ቃላቶች የወጣ አይደለም። ሁሉም (ምዕራባውያን የሚድያ ተቋሞች ለማለት ነው) በአንድ ቃል ይስማማሉ ይኸውም፥ “በሻር አል አሳድ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በመጠቀም ንጹሐን ዜጎች ፈጅተዋል” በሚል ጭብጥ ላይ ያልተመሰረተ ክስ ይስማማሉ። ሌላ እነዚህ ሁሉ የመገናኛ ብዙሐን አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይም አለ ይኸውም አንዳቸውም ለሚዘግቡት “ዜና” የሚያቀርቡት ተጨባጭ ማስረጃ የላቸው። “በሻር አል አሳድ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል ተጠቅመዋል ነው!” ከሚል ውጭ ሌላ የሚሰሙት “ዜና” የለም። እንዲህ ያለ አቀራረብ ደግሞ ዜና ሳይሆን ፕሮፖጋንዳ ነው።

በዙሪያው ሙያዊ ተመክሮአቸውና እውቀታቸው እንዲያካፍሉ የሚቀርቡ የተለያዩ ግለሰቦች ወደሚሰጡት አስተያየት ያመራን እንደሆነም “የለም ይህ ነገር አሜሪካን አይበጅም” በማለት ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙ ሙሑራን ከአስር ሁለት ቢሆኑ ነው የተቀሩት ግን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” እንዲል ያገሬ ሰው ማንም ይተኩሶው ማን ይህን የመሰለ ጥብስ የሆነ ዕድል ተገኝቶ እያለማ አል አሳድን መጥበስ ነው እንጅ የምን የተባበሩት መንግስታት ውጤት መጥበቅ ነው። ፕሬዝዳንት ጦርነት ለማወጅ ባለ ሙሉ ስልጣን ነው። የኮንግረስ ፈቃድ ወይም እውቅና የሚጠብቅበት ምንም ምክንያት የለውም። በማለት ነገሩን የሚያጋግሉ ስፍር ቁጥርም የላቸው። በዚህ ሁሉ የግለሰቦች የሚመስል አስተያየት ሚድያ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው።

ፕሬዝዳንት ኦባማ ከአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም ሆነ ብሔራዊ ደህንነት አንጻር ሲታይ በከፊልም ሆነ በምን ስሪያን የሚወርበትና ወታደራዊ ጥቃት የሚያደርስበት አንዳች ምክንያት እንደሌለው ጠንከር ያለ ተቃውሞ የሚያሰሙ ተንታኞችም አልታጡም። ተንታኞቹ አክለው እንደሚገልጹትም ኦባማ ስሪያን ለመውረር የተውተረተረበት ዋና ምክንያት ይላሉ ስሪያ ለአሜሪካ ደህንነት የምታሰጋ አገር ሆና ሳትሆን አስተዳደሩ በIRS በNSA በባንጋዚ የደረሰበትን ኪሳራና ያጣውን ተአማኝነት ለመመለስ ነው በማለት የኦባማ አስተዳደር በስሪያ ለሚወስደው እርምጃ አሜሪካ ወደከፋ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ አዘቅት የሚከት ነው ሲሉም ተሰምተዋል።

እኔምለው ግን አሜሪካ ሆነች እንግሊዝ እግር አለሁ እያለች የምትገኘው ሀገረ ፈረንሳይ የሰው ሀገር ይወሩና ያወድሙ ዘንድ የፈቀደላቸው ማን ነው? በውኑ ይህን ያደርጉ ዘንድ የሚፈቅድ ሕግ አለ? የተባበሩት መንግሥታት የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውልዋል አልዋለም የሚለውን ከማረጋገጥ ያለፈ የኬሚካል ጦር መሳሪያው ማን ተኮሰው? የሚለውን ጥያቄ የማጣራትም ሆነ ለጥያቄው መልስ የመስጠት ስልጣኑ የለውም አሉን። እውነት? የራሽያም ሆነ የቻይና ድጋፍ የሌላት አንዲት ድንጋያማ አፍሪካዊት አገር አንዲት ነገር ብታደርግ ግን የተባበሩት መንግስታ ርሃብ እንደጠለፈው ጅብ ዘሎ ማዕቀብ ለመጣልም ሆነ አንድን ነገር ለማድረግ (ውሳኔ ለማስተላለፍ) ማንም አይቀድመውም ነበር። ድግነቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዋልያ በቀር የዘይትም ሆነ የነዳጅ ባለቤት ባለመሆንዋ ከዚህ ሁሉ ወከባና ቡጢ ተርፈናል። ቢሆንም እንደ የአንዲት ሀገር ልጆች ልዩነቶቻችን በማጥበብ የተባበርንና የተስማማን እንደሆነ የማይለወጥ ታሪክ የለምና ሰርተን የሀገራችን ገጽታ የለወጥን ዕለት “ድሪማችን” ከሚያጨናግፍ ከ“ድሮን” እናመልጣለን ማለት ግን የዋህነት ነው። “ነግ በኔ” ማለት ጥሩ ነው እያልኩ ነው።

ዲን ሙሉጌታ ወልድገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

United States of America

August 31, 2013


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles