- የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወደ አውስትራልያ ያመራሉ
- የሀ/ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ማ/ክፍል ሓላፊ የታገደውን አመራር ለሁከት እየገፋፋ ነው
በአመራሩ የቃለ ዐዋዲ ጥሰትና ሃይማኖታዊ ሕጸጽ ምክንያት የታሸገው የድሬዳዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት ተከፍቶ አገልግሎቱን በጊዜያዊ ሥራ አመራር ቀጠለ፡፡
ሰንበት ት/ቤቱ እንዲከፈት የተወሰነው የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ከነሐሴ ፳፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ሲኾን ይህም በቃለ ዐዋዲው ለሰበካ አስተዳደር ጉባኤ በተሰጠው ሥልጣን የተደገፈ መኾኑ ተገልጧል፡፡ ውሳኔው የሰንበት ት/ቤቱን ብዙኀን አባላት በአገልግሎት በማጽናት ከመበተን የሚያድን ወቅታዊና አስፈላጊ ውሳኔ ነው ያሉት የአስተዳደሩ ምንጮች፣ ጊዜያዊው አመራር የሰንበት ት/ቤቱን ጽ/ቤትና ቢዝነስ ሴንተር ተረክቦ፣ የሓላፊነት ድልድል አድርጎ ተግባሩውን መወጣት መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡
የታሸገው የሰንበት ት/ቤቱ ጽ/ቤት በተከፈተበት ወቅት÷ ጊዜያዊው ሥራ አመራር፣ ከሓላፊነት ታግደው ማጣራት ከሚካሄድባቸው የሥራ አመራር አባላት በካቴድራሉ ቁጥጥርና ሒሳብ ሹም አረካካቢነት ርክክብ እንዲፈጽም፣ በሥነ ሥርዐቱም የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ተወካይና የፖሊስ አባላት በታዛቢነት እንዲገኙ በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጥሪ ተደርጎ እንደነበር ተገልጧል፡፡
ይኹንና የሀ/ስብከቱ ዋ/ሥራ አስኪያጅ እና በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሕዋስነት የሚጠረጠሩት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍሉ ሓላፊ የታገደው የሰንበት ት/ቤት አመራር ከነችግሩ እንዲቀጥል ውዝግቡን በማጣራት ስም በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ ጫና ለመፍጠር ያስተላለፉት መመሪያ በሰበካ ጉባኤው ተቀባይነት ባለማግኘቱ የሀ/ስብከቱ ተወካይ እንዳይገኝ ከማድረጋቸውም በላይ በወቅቱ በታዛቢነት የተላከውን የፖሊስ ኃይል የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ከካቴድራሉ አስተዳደር ጋራ መጠነኛ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት መኾናቸው ተገልጧል፡፡
የካቴድራሉ አስተዳደር ከቃለ ዐዋዲው በመነሣት ለፖሊስ ባደረገው ገለጻ አለመግባባቱ ተፈቶ፣ የታሸገው ጽ/ቤት ተከፍቶ አገልግሎቱ የተጀመረ ቢኾንም የሀ/ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ማ/ክፍል ሓላፊ የታገዱትን የሰንበት ት/ቤት አመራሮች በመሰብሰብ የካቴድራሉን ሰላም ለማወክ እየገፋፋ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡
ውዝግቡ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩና ገለልተኞች ናቸው ከተባሉ የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ተውጣጥቶ የተቋቋመው ጊዜያዊ የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር÷ በታገደው የሰንበት ት/ቤቱ አመራርና በሰበካ ጉባኤው መካከል የተፈጠረውን ችግር የማርገብ፣ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ ተላልፎ ከሰበካ ጉባኤው ዕውቅና ውጭ በመንቀሳቀስና ከሃይማኖት ሕጸጽ ጋራ ተያይዞ በታገደው አመራር ላይ የተነሡት ጥያቄዎች በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንና ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንዲታይ የተጀመረው ማጣራት ከዳር እንዲደርስ የመጣር፣ በመጨረሻም የሰንበት ት/ቤቱን ቋሚ አመራር የማስመረጥ ሥራ እንደሚጠበቅበት ተመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ከሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅነት በራሳቸው ፈቃድ ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ የተነሡት አባ አረጋዊ ነሞምሳ፣ ወደ አውስትራልያ ሀ/ስብከት ለመጓዝ በመዘጋጀት ላይ መኾናቸው ተመልክቷል፡፡ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ በነገረ መለኰት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው አባ አረጋዊ፣ ወደ አውስትራልያ የሚጓዙበት ምክንያት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ተመድበውና በዚያውም የድኅረ ምረቃ ትምህርት ለመቀጠል ነው ተብሏል፡፡
