Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

የሙሴ እናት

$
0
0
እሥራኤልን ዐርባ ዓመት በበረሃ የመራ፣ ፈርዖንን ድል የነሣ፣ የኤርትራ ባሕርንም ለሁለት እንደ ድንጋይ የከፈለ ሰው ነው ሙሴ፡፡ እርሱን በተመለከተ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ ፊልሞችን ደርሰዋል፣ ብዙዎችም በእርሱ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሕዝብን ከባርነት የማውጣት፣ ለሕዝብ ብሎ የመከራከር፣ ለሕዝብ ብሎ ራስን የመሠዋት፣ ሕዝብን ከራሱ በፊት የማስቀደም፣ ሕዝብን በትዕግሥትና በጥበብ የመምራት፣ ለሕዝብ ብሎ ተከራክሮ ድል የማድረግ ተምሳሌት ነው - ሙሴ፡፡
ሙሴ ከወገኖቹ ጋር የኖረው ከተወለደ እስከ ሦስት ወር እድሜው ብቻ ነው፡፡ ያ ጊዜም ቢሆን ወገኖቹ በግብጻውያን እጅ ከባርነት በከፋ ስቃይ ውስጥ ገብተው የሚንገበገቡበት ጊዜ ነው፡፡ እንኳን ሌላውን ዓይነት ነጻነት ቀርቶ ልጅ ወልዶ የማሳደግ መብት እንኳን አልነበራቸውም፡፡ በተለይም ልጁ ወንድ ከሆነ፡፡ በምድርም ላይ እነርሱን ሊመለከት፣ ሊታደግና ሊራዳ የሚችል አንዳችም ኃይል አልነበረም፡፡ ዓለም እንደ ወስከንቢያ በላያቸው ላይ ተደፍታባቸው ነበር፡፡
ሙሴ ለዐርባ ዓመታት ያህል የኖረው በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈርዖን ልጅ ተብሎ፣ ግብጻዊነቱ እየተነገረው ነው፡፡ የተማረው የግብጽን ጥበብ፣ የበላው የግብጽን ምግብ፣ የሚያውቀው የግብጽን ቋንቋ፣ የኖረው ከግብጻውያን መኳንንትና መሳፍንት ጋር፣ የሚያየው የግብጻውያንን አማልክት፣ የተወዳጀው ከግብጻውያን ጠንቋዮችና አስማተኞች ጋር ነበር፡፡


ሙሴ የኖረበት የኑሮ ደረጃ ወገኖቹ ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡ እርሱ በመኳንንት ወግ፣ በቤተ መንግሥት፣ ችግር የሚባል ነገር ሳይነካው፣ ግፍ የሚባል ነገር ሳይደርስበት፣ መብቱ በሚገባ ተጠብቆ፣ ከቅንጦትና ከድሎት አንዳች ሳይጎድልበት፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ እየተባለ የኖረ ሰው ነበር፡፡ በተቃራኒው ወገኖቹ ደግሞ ሰው ሊደርስበት የሚችለውን የመጨረሻ መከራ እየተቀበሉ፤ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው ነበር የሚኖሩት፡፡ ህልውናቸው በሌሎች ፈቃድ እየተወሰነ፣ ፈንግል እንደያዘው ዶሮ ሞታቸው የሰዓታት ጉዳይ እየሆነ፣ መኖር ራሱ ቅጣት ሆኖባቸው ነበር የሚንገፈገፉት፡፡
ሙሴ እንዲህ በምቾትና በቅንጦት፣ ችግርን በጆሮው እንኳን ሳይሰማት አድጎ፣ የቤተ መንግሥቱን ቅምጥል አጣጥሞ፣ በፈርዖን ዕቅፍ ተቀምጦ - በዐርባ ዓመቱ ግን የወገኖቹ ነገር ያንገበግበው፣ ግፋቸው ይሰማው፣ መከራቸው ያመው፣ ስቃያቸው ያቃዠው፣ ሕመማቸው ያንቀጠቅጠው፣ ሞታቸው ዕረፍት ይነሣው ጀመር፡፡ እርሱ በቤተ መንግሥት ቢቀመጥም ልቡ ግን ከቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ግፍ ከሚደርስባቸው ወገኖቹ ጋር ግፍ ይቀበል ጀመር፤ እርሱ ከፈርዖን ማዕድ ቢሰለፍም፣ ልቡ ግን ከወገኖቹ ጋር ይራብ ጀመር፡፡ እርሱ በሐር ልብስ ቢሞቀውም፣ ኅሊናው ግን ከወገኖቹ ጋር ተራቁቶ ይበርደው ነበር፤ እርሱ በሥልጣን ላይ ቢቀመጥም፤ ኅሊናው ግን ከወገኖቹ ጋር ለባርነት ተላልፎ ተሰጥቶ ይገረፍና ይታሠር ነበር፡፡ እርሱ ንጉሣዊ ሕይወትን ቢያጣጥምም፣ ልቡ ግን ከወገኖቹ ጋር ይሞት ነበር፡፡
ለዚህም ነበር አንድ ቀን ወደ ወገኖቹ ሲወጣ አጋዥ አልባ መሆናቸውን ያየ፣ ለግፍ ተላልፈው የተሰጡ መሆናቸውን ያጠና፣ የእነርሱ ሕይወት እንደ ጢንዚዛ ሕይወት ባለቤት የለውም ብሎ ያሰበ ግብጻዊ አንዱን ዕብራዊ ሲመታው ያየው፡፡ ለተመታው ዕብራዊ እርሱ አመመው፡፡ እርሱ የዚህ ግፍ የሚፈጸምበት ማኅበረሰብ አካል መሆኑን አመነ፡፡ ስለዚህም ታዳጊ ለሌለው ታዳጊ ለመሆን ወሰነና በራሱ ላይ ሞት ፈርዶ ያንን ግብጻዊ መታው፡፡ ልቡ ዐርባ ዓመት ከኖረበት ቤተ መንግሥት ሸፍቶ ሦስት ወር ወደኖረበት የእሥራኤላውያን የድህነት መንደር ገባ፡፡
እንዴት? ነው ጥያቄው፡፡ እንዴት?
ሙሴን ማን ነው ያስሸፈተው? ማንነቱን ሳይረሳ ዐርባ ዓመት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ያኖረው ማነው? ከድሎቱ ይልቅ የወገኖቹን ስቃይ እንዲመርጥ ያደረገው ማነው? ሰዎች ለአንድ ዓመትና ለሁለት ዓመት ከሀገርና ከወገን ርቀው ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ይረሳሉ፣ ማንነታቸውንም ይጥላሉ፡፡ እርሱ ግን ዐርባ ዓመት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ሲኖር ለምን ማንነቱን ጠብቆ ኖረ? አንዳንድ ሰዎች ምቾትና ድሎትን ካገኙ፣ ከከበሩና ከተሾሙ ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውንና ወገናቸውን አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ ናቸው፡፡ ሙሴ ግን እምቢ አለ፡፡ እነርሱ ከበሉ ሕዝባቸው የበላ፣ እነርሱ ሲሾሙ ሕዝባቸው የተሾመ፣ እነርሱ ሲያገኙ ሕዝባቸው ያገኘ የሚመስላቸው ባለ ሥልጣናት ብዙ ናቸው፡፡ ሙሴ ግን ከወገኑ ተለይቶ ያገኘው ክብርና ምቾት፣ ሥልጣንና ሀብት ቆረቆረው እንጂ አልተስማማውም፤ ከእርሱ ድሎት ይልቅ የወገኑን መከራ መረጠ፡፡
መንግሥቱ ለማ፡-
የተለመደ ነው የመጣ ከጥንት
ከተጠቂው መራቅ አጥቂን መጠጋት
እንዳሉት የሀብታም፣ የባለ ሥልጣን፣ የታዋቂ ሰው፣ የባለ ጊዜ፣ የከበረ ወገን፣ የሚፈራና የሚከበር ሕዝብ ወገን ነኝ፣ ዘመድ ነኝ፣ አባል ነኝ ማለት ከጥንትም የነበረ ነው፡፡ የአጥቂው ወገን ሆኖ ከተጠቂው ጋር መቆም፣ የጨቋኝ ወገን ሆኖ ከተጨቋኝ ወገን መቆም፣ የክቡራን ወገን ሆኖ ከተዋረዱ ጋር መሰለፍ፣ የገፊዎች ዘመድ ሆኖ ከተገፊዎች ጋር መወገን፣ የሀብታሞች አካል ሆኖ ከድኆች ጋር መሰለፍ፤ የሹመኞች ቤት ሆኖ ለተራው ሕዝብ ዘብ መቆም ግን ብዙም የማይገኝ እንደ አልማዝ ብርቅ የሆነ ነገር ነው፡፡ ታድያ ሙሴ ይህንን ከየት አገኘው?
የሙሴ እናት ሙሴን በቤቷ ለመደበቅ የቻለችው ለሦስት ወራት ብቻ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ሲወለድ ወንድ መሆኑ የታወቀ ዕብራዊ ሁሉ እንዲገደል በፈርዖን ዐዋጅ ወጥቶ ነበርና፡፡ የጨነቃት እናት መላ አታጣምና ዓባይ ወንዝ ወስዳ በሳጥን አድርጋ ጣለችው፡፡ የጣለችበት ቦታ የፈርዖን ሴት ልጅ ገላዋን የምትታጠብበት ቦታ ነበርና የፈርዖን ልጅ ሳጥኑን አየችው፡፡ ስትከፍተው የሚያምር ወንዝ ልጅ አገኘች፡፡ አምላክ የሰጠኝ ነው ብላ ወሰደችው፡፡ የሙሴ እናት ብልሃትና ጀግንነት ከዚህ ይጀምራል፡፡ እርሷ ባትኖር ኖሮ ሙሴ ከእነዚያ ሁሉ ሟች ሕጻናት ተለይቶ ባልተረፈ - በኋላም ታሪክ ባልሠራ ነበር፡፡
እናቱ ሙሴን ዓባይ ወንዝ ላይ ሰትጥለው እኅቱ መጨረሻውን እንድታይ ልካት ነበር፡፡ የፈርዖን ልጅ ሙሴን ከባሕር አውጥታ(‹ሙሴ› ማለት ከባሕር የወጣ ማለት ነው) ሞግዚት ስትፈልግ የሙሴ እኅት እናቱን ሞግዚት አድርጋ አመጣችላት፡፡ እናቱም ሞግዚት ሆና ሙሴን አሳደገችው፡፡ በፈርኦን ቤተ መንግሥት ውስጥ በእናቱ ሞግዚትነት ነበር ያደገው፡፡ ሁለተኛው ብልሃቷ ይሄ ነው፡፡ ሙሴ ሲያድግ እናቱ እውነቱን እየነገረችው ነው ያደገው፡፡ ‹‹አንተ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ብትኖርም ግብጻዊ ግን አይደለህም፤ አንተ በምቾት ብትኖርም፣ የሚሰቃዩት የእሥራኤላውያን ወገን ነህ፤ አንተ የግብጽን ቋንቋ ብታጠናም ቋንቋህ ግን ዕብራይስጥ ነው፡፡ እዚህ ያገኘኸውን ልምድና ዕውቀት፣ሥልጣንና ክብር፣ ከሞት የመትረፍ ዕድል ወገኖችህን ነጻ ለማውጣት ተጠቀምበት፡፡ ይህ የምታየው ሕዝብ እንዲህ አልነበረም፡፡ ታላቅ ሕዝብ ነበር፣ ታላቅ ሕዝብም ነው፡፡ የአሁኑን መደኽየት፣ የአሁኑን መዋረድ፣ የአሁኑን መገፋት፣ የአሁኑን መጨቆን አትይ፡፡ ነገ ታሪክ ይለወጣል፡፡ አንተ ዛሬ ይህችን ክብርና ሥልጣን፣ ምቾትና ድሎት አገኘሁ ብለህ ከወገንህ ብትርቅ ታሪክ የተለወጠ ዕለት አንተም ስትረገም፣ ስትዋረድና ስትወቀስ ትኖራለህ፡፡ አንት ባታየው ዐጽምህ ይዋረዳል፡፡ ዛሬ ግን ከተገፉትና ከተዋረዱት ወገን ሆነህ ታሪክ ሲለውጥ አብረህ ብትሠራ ስምህ በወርቅ ቀለም ይጻፋል› - እያለች አስተማረችው፡፡
ሙሴ የእናቱ ውጤት ነው፡፡ ሰውነቱን ፈርዖን ሲያሳድገው ልቡን እናቱ ናት ያሳደገችው፤ ምግቡን ፈርዖን ሲሰጠው ጥበቡን እናቱ ናት የሰጠችው፡፡ አካን ቤተ መንግሥቱ ሲቀርጸው የሀገርና የወገን ፍቅር፣ ጽናትንና ብርታትን፣ ለወገን ሲሉ መሥዋዕት መሆንን የተማረው ከእናቱ ነው፡፡ የጥንቱን ታሪክ እየነገረች ልቡ በወገኑ ፍቅር እንዲቃጠል ያደረገችው እናቱ ናት፡፡ ያንን ታሪክ የመመለስ፣ ይህንን ሕዝብም ታላቅ የማድረግ ድርሻ ያንተ ነው ያለችው እናቱ ናት፡፡ ሙሴን ነጻ አውጭ እንዲሆን አድርጋ የሠራችው እናቱ ናት፡፡ በሙሴ ውስጥ ያለችው፣ ከፈርዖን ጋር የተከራከረችው፣ ቤተ መንግሥቱን ጥሎ ለወገኑ ሲል በረሃ እንዲንከራተት ያደረገችው፣ ባሕር እንዲክፍል ያበቃችው፣ የሕዝቡን ስድብ፣ ማጉረምረም፣ ሐሜትና ዐመጽ ችሎ ሕዝቡን እንዲመራ ያደረገችው እናቱ ናት፡፡ ‹ሕዝቤ ከሚጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ› ያሰኘችው እናቱ ነች፡፡
እንዲህ ያለች እናት በሌለችበት፣ እንዲህ ያለ ሙሴ መፈለግ ጉም መዝገን ይሆናል፡፡ እኛ የምንለፋው ሙሴን ለማግኘት ነው፡፡ የሚበጀን ግን ጀግናዋን የሙሴን እናት ማግኘት ነው፡፡
የሙሴ እናት የት ነው ያለሽው?
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>