ሰሞኑን ኤፍሬም ሥዩም ያዘጋጀውን ‹ተዋነይ -ብሉይ የግእዝ ቅኔያት ፍልስፍና› የተሰኘ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ አንዳንድ ‹ጻፍን› ብለው የሚያስቡ የኔ ብጤዎች የጥንቱን ሁሉ እንደ አሮጌ በሚያዩበት ዘመን ኤፍሬምን የመሰለ አስተዋሽ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ባለማወቃችን ምክንያት የለንም ልንል ስንነሣ፣ እንዲህ የሚያስታውሱን አይጥፉ፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች ሃሳቦቻቸውን የገለጡባቸውን የግእዝ ቅኔያት በግጥም መልኩ እየተረጎመ ግራና ቀኝ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ኤፍሬም የግእዝ ቅኔያቱን የሰበሰበበት መመዘኛው ፍልስፍና ነክነት ይመስለኛል፡፡ ሊቃውንቱ ከምድር እስከ ሰማይ ያሉ ፍጡራንንና ኃያላንን የሞገቱበትንና የመረመሩበትን መንገድና ምጥቀት እናያለን፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ 83 የግእዝ ‹ቅኔዎች› ቀርበዋል፡፡ አንዳንዶቹን አንብባችሁ ስትገረሙ ልትውሉ ትችላላችሁ፡፡
ለምሳሌ እንዲህ ያለውን የአለቃ ገብረ ሐና ቅኔ ስታዩ፡-
ኮንኖ ኃጥኣን ክርስቶስ ኢይደልወከ ምንተ
አፍቅሩ ጸላዕተክሙ እስመ ትብል አንተ
አንዳንዶቹን አንብባችሁ ደግሞ ስትመሰጡ ታነጋላችሁ፤
እንዲህ የሚሉትን ስታነቡ፡-
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፣
ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ፤
አንዳንዶቹ እንደገና እንደገና እንድትመራመሩ ያደርጓችኋል፤
ባሕቲቶ ነቢረ እግዚአብሔር ፈርሀ
እም ኢሀልዎ ንዋም እስመ ዓለመ አንቀሐ
አንዳንዶቹም ብቻችሁን እያወራችሁ እንድትሄዱ ያደርጓችኋል፡-
እመ ተናገርኩ ጽድቀ ሰብአ ዛቲ ዓለም ይጸልዑኒ፣
ወከመ ኢይንብብ ሐሰተ ኩነኔ ዚአከ ያፈርሀኒ፣
እም ኩሉሰ አርምሞ ይኄይስ ወይሤኒ
በውጭው ዓለም አንድን ዕውቀት ለመረዳት ይቻል ዘንድ በየፈርጁ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የኤዞፕ ተረቶች አንድ ዓይነት ቢሆኑም በልዩ ልዩ ዘርፎች እየተዋቀሩ እንደገና እስካሁን ይቀርባሉ፡፡ ኤፍሬም ለግእዝ ቅኔያት ይህንን መንገድ አመላክቷል፡፡ ፍልስፍናውያን፣ ታሪካውያን፣ መንፈሳውያን፣ ትርጓሜያውያን፣ ዶግማውያን፣ ወዘተ እያልን በየዘርፉ ልናያቸውና በሚገባ ልናውቃቸው እንደምንችል አመላክቷል፡፡
ባይሆን ኤፍሬም ለወደፊቱ የቅኔዎቹን ታሪካዊ ዳራ በግርጌ ማስተዋሻ በኩል ጣል ቢያደርግልን የኔ ብጤዎች በሚገባ ለመረዳት በር ይከፍትልናል፡፡ በመጽሐፉ መጀመሪያ ሊቀ ኅሩያን በላይ እና ራሱ ኤፍሬም የጻፏቸው መቅድሞችም የቅኔዎቹን ያህል ተወደውና ልብ ገዝተው የሚነበቡ ናቸው፡፡
ይህንን በ190 ገጽ የተጠቃለለ፣ በ100 ብር የሚሸጥ፣ በሻማ ቡክስ የታተመ መጽሐፍ ታነቡት ዘንድ እየጋበዝኩ እስኪ ይኼን ቅኔ ፍቱ
ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ
አኮኑ ትውዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ
መልካም ንባብ፡፡