ሁለተኛው ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት›› ዘንድሮ በመጋቢት ወር መጨረሻ ይከናወናል፡፡ ለሀገሪቱ በጎ ሠርተዋል የሚሏቸውን ሰዎች ይጠቁሙ፡፡ ለጥቆማ የሚረዷችሁ ነጥቦች
- ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቦች መቀራረብና መደጋገፍ፣ ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣
- በበጎ አድራጎትና ሰብአዊ ተግባራት ተሠማርተው የሰው ልጅን ሕይወት የለወጡ፣
- በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጥበብና በመሳሰሉት መስኮች ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ፣ የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን ሥነ ጥበብ ወደ አንድ የላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ሥራዎች የሠሩ፣
- በግብርና፣ በቢዝነስ፣ በኢንዱስትሪና በመሳሰሉት መስኮች አዲስ፣ የራሱ ወጥነት ያለውና ያልተደፈረ የሚመስለውን ሥራ ያከናወኑ፣ ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔም ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣
- በጋዜጠኛነት መስክ ተሠማርተው ሙያውን የጠበቀ፣ ለሌሎች አርአያ የሚሆን፣ የሕዝቡን ኑሮ የሚለውጥ ሥራ ያከናወኑ፣
- በዲፕሎማሲው መስክ የሀገሪቱን ክብርና ደረጃ ያስጠበቁ፣ የሀገሪቱንም መብት ያስከበሩ፣
- በመንግሥትና በሥራ ተቋሞቻቸው የተሰጧቸውን የተለያዩ ሀገራዊ ግዳጆችን በብቃት የተወጡ፣ መሥዋዕትነት የሚጠይቁ ተልዕኮዎችን ያከናወኑ፣ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ ብቁ አመራሮችን የሰጡ፣ በአመራሮቻቸውም ድርጅታቸውንና መሥሪያ ቤቶቻቸውን የለወጡ፣
- ሀገራዊ ዕውቀቶችን በማስተማር፣ ቅርሶችንና ባህልን በማስጠበቅና በመከባከብ ለውጥ አምጭ ተግባር ያከናወኑ፣
- በጥናትና ምርምር መስክ ተሠማርተው ችግር ፈች የሆኑ ውጤቶችን ያስመዘገቡ፣
- በማስታረቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ ሀገራዊ የሽምግልና ሥራ የሠሩ፣
- በሌሎችም መስኮች የሚጠቀስ፣ ለሀገር የሚጠቅም፣ ለትውልድ አርአያነት ያለው፣ የሀገርን ክብር የሚጨምር፣ ታሪክና ማንነትን የሚያጎላ ተግባር ያከናወኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ይጠቁሙ፤
ማስተዋሻ
- የሚጠቁሟቸው ኢትዮጵያውያን በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት ያልታወቁና ይህን መሰል ዕድል ያላገኙ ቢሆኑ ይመረጣል፣
- በተቻለ መጠን ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ ቦታዎች ሰው ሳውቃቸው ለሀገራቸው አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ዜጎችን በመጠቆም ይተባበሩ፣
- ሲጠቁሙ የጠቆሙትን ሰው ስም፣ ያለበትን ቦታ፣ የሠሩትን በጎ ሥራ ዘርዘር አድርገው ይግለጹ፣ ከቻሉም ስልካቸውን ወይም ኢሜይላቸውን ይላኩልን፣
- ጥቆማውን እስከ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓም ያድርጉልን
- ከሀገር ውጭ ሆነው ሀገራዊ ሥራዎችን የሚሠሩና ሀገራቸውንንና ሕዝባቸውን የሚጠቅሙትን በጎ ዜጎች እንጠቁም
- ከጥቆማው በኋላ የተቋቋመው ኮሚቴ ሃያ አምስት ዕጩዎችን ይጠቁማል፤ በእነዚህ ዕጩዎችም ላይ ከተለያየ ሙያ፣ መስክ፣ ዕድሜ፣ እምነት፣ አካባቢ፣ የዕውቀት መስክ የተወጣጡ ነገር ግን እርስ በርሳቸው የማይተዋወቁ 100 ሰዎች ድምጽ ይሰጧቸዋል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ድምጽም የመጨረሻዎቹ አምስት ሰዎች ይመረጣሉ፣
ለመጠቆም ይህንን የኢሜይል አድራሻ ይጠቀሙ begosewshilmat@gmail.com
ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው የሠሩትን ዜጎቻችንን እናበረታታ፣ እንሸልም፣ ዕውቅና እንስጥ