አንዳንዱን ሰው ለምስክርነት ይፈጥረዋል፡: ደግ ሰው ጠፋ እንዳይባል፡: እርሱን የለህም እንዳንለው፣ ዓለምም ‹ጨልጦ ገርኝቶ› እንዳይጠፋ፡፡ እንዲህ ያለውም ሰው እንደ ሄሊኮሜት በዘመናት አንድ ጊዜ ብቻ ይገለጣል መሰል፡፡ መገለጡንም ብዙዎች ሳያውቁት ያልፍባቸዋል፡፡ ያወቁ ደግሞ ይጠቀማሉ፡፡
በዚህ በኛ ዘመን እንዲህ ያሉ ሰዎች ተገልጠው ነበረ ቢባል ለአብነት ከምንጠራቸው አንዷ እማሆይ ባቄላ ናቸው፡፡ ስማቸውን ማንም አያውቀውም፡፡ ግብራቸው ግን ሌላ ስም አምጥቶላቸዋል፡፡‹ እስመ ስሙ ይምርሖ ኀበ ግብሩ› ነበር የሚለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ‹እስመ ግብሩ ይመርሖ ኀበ ስሙ› እንዲል የሚያደርጉት ሰዎችም አሉ፡፡ እንደ እማሆይ ባቄላ፡፡
ትግራይ ከሰላ አካባቢ መወለዳቸው የሚነገርላቸው እማሆይ ባቄላ ደሴ ከተማ የገቡት በ1963 ዓም አካባቢ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ ያለፈ ታሪካቸውን የሚያውቅ የለም፡፡ ለእርሳቸው መልካም ሥራ እንጂ ትውልድና ዘር ትርጉም አልነበራቸውምና፡፡ የእናታቸው ስም አመተ እግዚእ፣ የአባታቸውም ስም ገብረ ትንሣኤ መሆኑ የታወቀው እንኳን በየወሩ በ29 ቀን የወላጆቻቸውን ስም በደሴ መድኃኔዓለም በጸሎት እንዲታሰብ ያደርጉ ስለነበር፣ ይህንንም ደጉ ካህን መጋቤ ብሉይ አባ ዮሴፍ ስላስታወሱት ነው፡፡
ደግሞም መሥራት እንጂ ማውራት አይችሉበትም፡፡ በአንድ ወቅት የቤተ ክህነቱ ነቅዐ ጥበብ መጽሔት ጋዜጠኛ ታሪካቸውን እንዲያወጉት ቢጠይቃቸው ‹‹እኔ ለአርአያነት የሚያበቃ ሥራ የለኝም፤ ለምነሽ እንጂ ተናግረሽ ኑሪ አልተባልኩም›› ነበር ያሉት፡፡
አባ ዮሴፍ እንደሚተርኩት እማሆይ በልጅነታቸው ለአንድ የአካባቢው ባላባት ይዳራሉ፡፡ እርሳቸው ግን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ፈጣሪን አክባሪና የእምነት ሰው ነበሩና ‹‹እኔ ወደምመራሽ ቦታ ሂጂ› የሚል ቃል ከሰማይ ይመጣላቸዋል፡፡ እማሆይም ቃሉን አክብረው እንደ ገብረ ክርስቶስ ከትውልድ ቀያቸው ይጠፋሉ፡፡ ከዚያም መቀሌ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ገብተው አገልግሎታቸውን ይጀምራሉ፡፡
እንደ ስምዖን ጫማ ሰፊው ያደርጉት እንደነበረው ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን፣ አስታማሚ ያጡትን፣ በችግር የተቆራመዱትን፣ በመንገድ የደከሙትን ለምኖ መርዳት ሆነ ሥራቸው፡፡ እነርሱን ለመርዳት ሲሉ ዞረው ይለምናሉ፤ የለመኑትንም ለራሳቸው አንዳች ሳያስቀሩ እየዞሩ በየድኾቹ ቤት ያከፋፍላሉ፡፡ አረጋውያንን ይጦራሉ፤ ሕሙማንንም ያስታምማሉ፡፡ ይህን እያገለገሉ ነበር መቀሌ ላይ የተቀመጡት፡፡
በዚህ አገልግሎት ላይ እያሉ ፊታቸውን ወደ ግሼን ማርያም እንዲያዞሩ መንፈስ አነሣሣቸው፡፡ ተነሥተውም ግሼንን ሊሳለሙ መጡ፡፡ ከዚያም በሰኔ 1963 ዓም ወደ ደሴ ገብተው ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀመጡ፡፡ ከደሴ መድኃኔዓለም የለያቸው የሥጋ ሞት ብቻ ነው፡፡
እማሆይ ደሴ ላይ የመቀሌውን በጎ ምግባር ቀጠሉበት፡፡ ችግረኞችን ይሰበስባሉ፣ መታከሚያ ያጡትን ለምነው ያሳክማሉ፤ በየቤታቸው ወድቀው ሰው አላያቸው ያሉትን ለምነው ያለብሳሉ፣ ያጎርሳሉ፤ የወደቁትን አንሥተው ለክብር ያበቃሉ፤ መንገደኞችን አሳድረው ይሸኛሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ አልፈው ደግሞ ባቄላ ቀቅለው ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም በር ላይ ቆመው ‹ስለ መድኃኔዓለም‹ እያሉ ያድላሉ፡፡ ለዚህም ነበር ሕዝቡ ‹እማሆይ ባቄላ› ያላቸው፡፡
በ1977 ዓም በተከሰተው ረሃብ ጊዜ ባቄላ ለምነው በመቀቀል፣ እህል ለምነው ጠላ በመጥመቅ አያሌ ረሃብተኞችን ታድገዋቸዋል፡፡ ያን ጊዜ እንኳን ረሃብተኞቹ ምግብ ያልጠፋባቸው ሳይቀሩ የእርሳቸውን በረከት እንካፈል እያሉ ተሰልፈው ንፍሮ ይቀበሉ ነበር ይባላል፡፡ እማሆይ እንዲህ ሀገር ያወቀውን ችግር ቀርቶ ሰው ያልደረሰለትንም ቀድመው የሚደርሱ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ከግሼን ሲመለስ ከመኪና ወድቆ አደጋ ይደርስበትና ሰውነቱ ይበላሻል፤ እዳሪውንም መቆጣጠር ያቅተዋል፡፡ ሰው ሁሉም ይጸየፈዋል፡፡ እማሆይ ግን አልተጸየፉትም፡፡ ቤታቸው ወስደው፣ ሰውነቱን እያጠቡ፣ አልጋ ላይ ሲጸዳዳ እየጠረጉ፣ ልብሱን በየቀኑ እያጠቡ፣ ሰው ለምነው አብልተው፣ አምላክን ለምነው አዳኑት፡፡ ሰውየውም ድኖ መርቋቸው ሄደ ይባላል፡፡
በሌላ ጊዘ ደግሞ አንድ ሰው ገደል ወድቆ ሰውነቱ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፤ ሆስፒታል ተኝቶ ታክሞም መዳን ይሳነዋል፡፡ የሕክምናው ወጭም ከባድ ይሆንበታል፡፡ ከሐኪም ቤት ሲወጣም መውደቂያ ያጣል፡፡ እማሆይ ይሄንን ሰው ቤታቸው ወሰዱት፡፡ እናት ለልጇ፣ ባልም ለሚስቱ ከሚያደርገው በላይ አድርገው አስታመሙት፡፡ ሰውዬው ከዐሥር ዓመት በላይ እማሆይ ቤት ተኛ፡፡ እርሳቸውም ሳይጸየፉና ሳይመረሩ አስታመሙት፡፡ በመጨረሻ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ በወግ በመዓርግ እንዲቀበር አደረጉት፡፡
አባ ዮሴፍ እማሆይ ባቄላን በተመለከተ በዓይናቸው ያዩት በጆሯቸው የሰሙት ብዙ ታሪክ አላቸው፡፡ እማሆይ ለአገልግሎት ሌትና ቀንን አይመርጡም፡፡ ሌሊት ጅቦች እንደ ሠራዊት አጅበዋቸው ሲንቀሳቀሱ አውቃለሁ ይላሉ፡፡ ይህንን ጸጋቸውን የተረዳው የደሴ ሕዝብም እጁን ያለ ማመንታት ይዘረጋላቸዋል፡፡ ‹ስለ መድኅኑ›› እያሉት እንኳን ክርስቲያኑ ሌላው አያልፋቸውም፡፡
እርሳቸው አስቦ የማይሰጠውን ደካማ ለምነው ተቀብለው ለማጽደቅ የመጡ ናቸው፡፡ ግዴታቸውን ያልተወጡትን ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድ ለማሳሰብ የተሰጡ ናቸው፡፡ ለምነው ድኻ ይረዳሉ፣ ሕሙማንን ያስታምማሉ፣ ለምነው ባቄላ ቀቅለው ያበላሉ፤ ለምነው የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ያሠራሉ፡፡ ለምነው የግሼን፣ የላሊበላና የአኩስም መንገደኛን ያስተናግዳሉ፣ ይሸኛሉ፡፡ ደላንታ ውስጥ ለተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ከ60ሺ ብር በላይ ለምነው ሰጥተዋል፡፡ ደሴ የሚገኘውን ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ከቤተልሔሙ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ የግቢ በር ያለውን ንጣፍ አስነጥፈዋል፡፡
እማሆይ ለምነው መርዳት፣ ለምነው ማልበስ፣ ለምነውም ማስታመም ጸጋቸው ነበርና ይህንን አገልግሎት ያለመታከትና ያለማጉረምረም ይፈጽሙት ነበር፡፡
አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ፡፡
አንድ የሚያውቁት ሰው መኪና እያሽከረከረ ያዩታል፡፡ ይህ ሰው ቢሰጣቸው የሚረዷቸውን ድኾች፣ የሚያስታምሟቸውን በሽተኞች፣ የሚያለብሷቸውን ዕሩቃን፣ የሚመግቧቸውን ርኁባን እያስታወሱ ወደ ሰውዬው በፍጥነት ገሠገሡ፡፡ እርሱ ግን አላያቸውም፡፡ መኪናውን ዘወር ሲያደርግ እማሆይን ገጫቸው፡፡ እማሆይ መሬት ላይ ተዘረሩ፡፡ በየትኛው ዐቅም ያንን ግጭት ይቋቋሙታል፡፡ ሕዝብ ደነገጠ፡፡ ማንም ልቡ አልቀረለትም፡፡ ወደ ልቡ የተመለሰው ይዟቸው ወደ ሆስፒታል ሮጠ፡፡
እኒያ ለማገልገል ሮጠው የማይሰለቹት እናት አልጋ ላይ ዋሉ፡፡ ‹‹የእኔ ጸሎት ጥሬና ብስል ነው›› ቢሉም ተኝተውም ለሀገራቸውና ለወገናቸው መጸለይን ለአፍታ እንኳን አላቆሙም ነበር፡፡ በዚህ ሕይወትም እያሉ ታኅሣሥ 21 ለ22 አጥቢያ በ2000 ዓም ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፡፡ ሲገንዟቸው ሰውነታቸው በመስቀል የተከበበ እንደነበር፤ በደረታቸው ላይም ትልቅ መስቀል ማግኘታቸውን አባ ዮሴፍ ይናገራሉ፡፡
ደሴም በዘመናችን ብቅ ካሉት ቅዱሳን አንዷን በልቅሶና በጸሎት ሸኘች፡፡ በየአካባቢያችን ግን ለዓይነት አይጠፉም፡፡ እርሱ ሀገርን ያለ አንድ ጻድቅ አይተዋትምና፡፡
ምንጭ
የዓይን ምስክሮችና መዘክር(ለደሴ መድኃኔዓለም 100ኛ ዓመት የተዘጋጀ) መጽሔት