በዶር መራራ ጉዱና የሚመራዉ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፣ የወጣቶችን ሊግ ማቋቋሙ የዶር መራራ እና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ፌስቡክ ዘገበ። ሊጉ የኦሮሞዎች መብት በኢትዮጵያ እንዲከበር ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ በኦሮሚያ ዞኖች ይንቀሳቀሳል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ አበባን ጨምሮ ሃያ አንድ የኦሮሞያ ዞኖች ሲኖሩ፣ አዲስ ለተቋቋመዉ የወጣቶች ሊግ፣ ተወካዮች ከአሥራ ሁለት ዞኖች እንደመጡም ለማወቅ ተችሏል። ወጣት ተወካዮች የመጡት፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን፣ ከምእራብ ሸዋ ዞን፣ ከኢሊባቡር ዞን፣ ከቀለም ወለጋ ዞን፣ ከምስራቅ ሃረርጌ ዞን፣ ከጉጂ ዞን፣ ከምእራብ ወለጋ ዞን፣ ከምስራቅ አርሲ ዞን እና ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ሲሆን፣ ከደቡብ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ከምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ከአርሲ ዞን፣ ከባሌ ዞን፣ ከምእራብ ሃረርጌ ዞን፣ ከቦረና ዞን፣ ከጂማ ዙሪያ ዞን፣ ከጅማ ከተማ ልዩ ዞን ፣ ከቡራዩ ልዩ ዞን እና ከአዳማ/ናዝሬት ልዩ ዞን ተወካዮች አልተገኙም።
የወጣቱ ሊግ 50 ወጣቶች ያሉበት አመራር ያሉት ሲሆን፣ 11 አባላት ያሉበትም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲኖረው ተደርጓል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የመድረክ አባል ድርጅት ሲሆን ከአምስት አመታት በላይ ከአረና ትግራይ፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከመሳሰሉ ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት የፈጠረ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንካራ አቋም ያለው ድርጅት ነዉ። ሊቀመንበሩ ዶር መራራ ጉዳና፣ ኦሮሞዉ የኢትዮጵያ ግንድ እንደሆነ በመገልጽ፣ «እንዴት ግንድ ከቅርንጫፍ ይገነጠላል ?» በማለት የአንዳንድ ጽንፈኛ የኦነግ ዘረኛ የመገነጠል ፖለቲካን በይፋ ማጣጣላቸው ይታወቃል።
አንዳንድ የመድረኩ አባል ድርጅቶች፣ በመድረኩ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን ሰጥቶ በመቀበል መርህ አጣቦ ፣ ወደ ዉህደት የመምጣት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ በኦፌኮ ዘንድ ብዙ ተቀባይነት እንዳላገኝ ዉስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ከአገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት እንጂ የሚፈልጉት፣ የ«ኦሮሞ» ድርጅትነታቸውን እና ኦሮሞ ለሚሉት ብቻ የመቆም አላማቸውን ማከሰሙ እንደማይመቻቸው፣ ያከሉት የዉስጥ አዋቂዎች፣ «የኦሮሞ ስማችንን ከቀየርን ፣ ከአክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞች ጥቃት ይደርስብናል» የሚል ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።
ኦፌኮ በመድረክ ዉስጥ ዉህደትን ከመፍጠር ፣ በቅርቡ «ወደ አገር ቤት ገብቼ እታገላለሁ» የሚል አቋም የያዘው፣ በቀድሞ ነባር የኦነግ አመራር አባላት በነበሩ፣ በነአቶ ሌንጮ ለታ፣ አቶ ዲማ ነግዎ በመሳሰሉ በተቋቋመው ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ጋር ዉህደት መመስረቱን እንደሚመርጥ የሚናገሩት ዉስጥ አዋቂዎች፣ «ሁለቱም አሁን ያለውን በቋንቋ ላይ ያለው ፌደራል አወቃቀር እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ሁለቱም የሚታገሉት ለኦሮሞዉ ነዉ። ሁለቱም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው ለመታገል የሚፈልጉት። ሁለቱም በምርጫ ለመወዳደር ፍላጎት አላቸዉ» ሲሉ፣ በኦፌኮ እና በኦዴግ መካከል በፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው ሆነ በትግል ስትራቴጂዎች አኳያ ምንም ልዩነት እንደሌላቸው ያስረዳሉ።