Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

ብዙ ውህደትና ተጨማሪ ትብብር ለኢትዮጵያ ፓርቲዎች (አንድነት እያደረገ ስላለው የዉህደት ጥረት) – ዳዊት ሰለሞን

$
0
0

የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎቻቸው እንዲወዳደሩ ወይም ስልጣን እንዲይዙ ለማድረግ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ናቸው፡፡የውክልና ዴሞክራሲ እንዲጠነክርና እንዲጎለብት ፓርቲዎች የሚጫወቱት ሚናም ቁልፍ ነው፡፡

በሰለጠነው አለም የፖለቲካው ልቀት የሚለካው በፓርቲዎች ብዛት ነው፡፡የፖለቲካ ስልጣንን ለማግኘት የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ቁጥር ሁለት ቢበዛ ሶስት ነው፡፡ለምሳሌ በአሜሪካ ኋይት ሃውስ ለመግባት የሚፎካከሩት ፓርቲዎች ሁለት ናቸው፡፡ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች፡፡ በእንግሊዝ ዋነኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሶስት ናቸው፡፡ወግ አጥባቂዎቹ (ኮንሰርቫቲቭ)የሰራተኛው(ሌበር ፓርቲ)እና ሊበራሎች፡፡

የአሜሪካና የእንግሊዝ ፓርቲዎች ጥርት ባለ የፖለቲካ አይዶሎጂ (Clear Ideologies) ላይ የተመሰረቱና ህዝቡን በፖለቲካ፣በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩች በማንቃት ምርጫው እንዲያደርጋቸው የሚታገሉ ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ጥርት ያለ አደረጃጀት ያላቸው በመሆናቸው በመሪዎቻቸው መለዋወጥ የሚለዋወጡ አይደሉም፡፡

ወደ አገራችን ስንመለስ መሬት ላይ የምናገኛቸው ፓርቲዎች ቁጥር ከ73 ይልቃል፡፡ፓርቲዎቹ በአብዛኛው በመሪዎቻቸው የፖለቲካ ቁመና የሚመዘኑ ስፖንሰሮቻቸው በማዕበል እንደተመታች መርከብ ከወዲያ ወዲህ የሚያላጓቸው ናቸው፡፡የፓርቲዎቹ ጥንካሬ የመሪዎቻቸው የፖለቲካ ቁመና ብቻ ነው፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር የፓርቲዎችን ፕሮግራም አንብቦና አማርጦ ተከታያቸው ለመሆን የሚያስችል ባለመሆኑም የየፓርቲዎቹ አመራሮች ጭምር ፓርቲያቸው ስለሚከተለው የፖለቲካ ፕሮግራም እውቀት ያላቸው ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ ለመናገር ያስቸግራል፡፡

የሊበራል የፖለቲካ ፍልስፍናን በሚያራምድ ፓርቲ ውስጥ በሶሻሊስት አይዶሎጂ የተጠመቀ መሪ ቢያገኙ መደነቅ አይኖርብዎትም፡፡ምክንያቱም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ የፕሮግራም ጉዳይ ሳይሆን የህልውና በመሆኑ ነው፡፡
የምርጫ ቦርድን መዝገብ ያጣበቡት የሚበዙት ፓርቲዎች በአይዶሎጂ የተፈበረኩ ሳይሆኑ ዘውግ ተኮር በመሆናቸውም አንደኛቸው ከሌላኛቸው የሚለዩት ‹‹የእኛ›› ‹‹የእነርሱ›› በሚለው የዘውግ አጥር ነው፡፡በእነዚህ ፓርቲዎች ሐሳብ፣ፕሮግራምና የፖለቲካ ፍልስፍና ቦታ የላቸውም፡፡ምርጫ ሲቀርቡ የዘውጌያቸው ተወላጅ የሆነ እንዲመርጣቸው ከመጠየቅ ባለፈ ከዘውጌያቸው ውጪ ያለ ሊመርጣቸው የሚችልበት መንገድ አይኖርም፡፡ስለዚህ እነዚህ ፓርቲዎች የፖለቲካ ስልጣን መዘውሩን የመጨበጥ እድላቸው በዜሮ የሚባዛ ይሆናል፡፡

ዘውግ ተኮር ፓርቲዎች የስርዓቱ ስጋት ተደርገው የሚታዩ ባለመሆናቸውም የምርጫው አድባር ኦዲት ተደረጉም አልተደረጉ አልያም ጠቅላላ ጉባኤ ባያደርጉም ይፈልጋቸዋል፡፡

ተቃዋሚዎች በቁጥር በዝተው በምርጫ ገበያው ራሳቸውን ማቅረባቸው ሁልግዜም የሚጠቅመው ስልጣን ላይ የሚገኘውን አካል ብቻ ነው፡፡የገዢውን ፓርቲ የፖለቲካ ሃይል ለመቀናቀን ፓርቲዎች ቁጥራቸውን ለመቀነስ የሚያስችላቸውን ብስለት የተሞላበት ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ያለፈው የህብረት፣የውህደት፣የትብብርና የግንባር ልምድ ጥሩ ባለመሆኑ ብቻ ውህደት ፣ቅንጅት፣ህብረትና ትብብር አያስፈለግም ማለት የገዢውን ፓርቲ እድሜ ለማራዘም ከመወሰን ተለይቶ መታየት አይኖርበትም፡፡

የከዚህ በፊቶቹ ውህደቶች፣ቅንጅቶች፣ህብረቶች ያልሰሩበትን ምክንያት በማየት የተሻለ ሆኖ ለመውጣት መስራት ይገባል እንጂ የከሸፉ ታሪኮችን በማስታወስ ማላዘን የትም አያደርስም ደግሞስ ‹‹Those who do not learn from past mistakes are doomed to repeat it››ይባል የለምን፡፡ትምህርት ቀስሞ የሚሰራ ውህደት፣ትብብር ወይም ቅንጅት ለመፍጠር መስራት ከሁሉም ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ይጠበቃል፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከመኢአድ ጋር የጀመረውን የውህደት ድርድር ከዳር በማድረሱ ሁለቱ ፓርቲዎች በቅርቡ አንድ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡አረና ከአንድነት ለመዋሐድ እያደረገ የሚገኘው ድርድርም በአስተማማኝ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ መረጃ አለኝ፡፡አንድነት ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር የጀመረው ትብብር ከፍተኛ ስኬት በማስመዝገቡ ፓርቲዎቹ በውህደት ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ለመፈራረም መብቃታቸው አይዘነጋም፡፡እናም ብዙ ውህደትና ተጨማሪ ትብብር ለኢትዮጵያ ፓርቲዎች !!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>