የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር፣ በአሜሪካ ካሉ የድጋፍ ማህበራት ጋር ወደ ሁለት ሰዓት የሚጠጋ ሰፊ ዉይይት በቴሌኮንፈራንስ አደረጉ። ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራዉ ፣ የአንድነት ፓርቲ እያደረጋቸው ስላለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ሰፋ ያለ ሃታተ የሰጡ ሲሆን፣ ከስብሰባው ተሳታፊዎች በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጠዋል።
«በዉጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ በአካል ርቆ ቢገኝም ልቡ አገር ቤት ነዉ። ኢትዮጵያን በልቡ ይዞ የሚኖር ነው» ያሉት ኢንጂነር ግዛቸው፣ በዉጭ ያለው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዲሞክራሲ ፣ ለዉጥ እንዲኖር እያበረከተ ስላለው ትልቅ አስተዋጽ አመስግነዋል። በባህር ዳር የተደረገው በሌሎች ከተሞች በተጠናከረ መንገድ ለማድረግ ፓርቲው እቅድና አላማ እንዳለው የገለጹት ኢንጂነር ግዛቸው፣ በቅርቡ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት አይነት፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ለፍትህ እና የሚሊዮኖች ድምጽ ለላንድ ሪፎርም በሚል ፣ አገር ሰፊ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ አሳዉቀዋል። ይህ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄዎች፣ በአዲስ አበባ ተጀምሮ፣ አዋንሳ፣ መቀሌን፣ ደሴን፣ ደብረ ታቦርን፣ አዳማን፣ አሶሳን፣ ቁጫን ፣ ድሬደዋን፣ ጂንካን በአጠቃላይ ወደ 12 የሚሆኑ ከተሞችን የሚያዳርስ ሊሆን እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ የእንቅስቃሴው ማጠቃለያው እንደገና በአዲስ አበባ እንደሚሆን ከኢንጂነር ግዛቸው ማብራሪ ለማወቅ ተችሏል።
በነዚህ ሁሉ ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ የገንዘብ አቀም እንደሚጠይቁ ያስረዱት የአንድነት ሊቀመንበር፣ በዉጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም አሳስበዋል። የሚሊዮኖች ንቅናቄ፣ አንድነት ፓርቲ ቢጠራዉም፣ «የሕዝብና የሚሊዮኖች ንቅናቄ» ያሉት ኢንጂነር ግዛቸው በዉጭ ያለው ማህበረሰብ ትኩረት ሰጥቶት፣ ሙሉ ድጋፉን እንዲያበረክት ፣ ያሉ የድጋፍ ድርጅቶችም ቀበቷቸውን ታጥቀዉ አክቲቭ እንዲሆኑ፣ በዉጭ ያሉ ሌሎች የሲቪክ ማህበራምት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ተማጽኖ አቅርበዋል።
በስብሰባዉ የነበሩ የድጋፍ ድርጅት መሪዎችና ደጋፊዎች፣ በተደጋጋሚ የአንድነት ፓርቲ እያደረገ ላለው እንቅስቅሴዎች ያላቸውን አድናቆት የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም በባህር ዳር የተደረገው፣ ከልብ እንዳስደሰታቸው ተናገረዋል። ተሰብሳቢዎቹ በርካታ ጥይቄዎችን በተለያዩ ጉዳዮች ያቀረቡ ሲሆን፣ ኢንጂነር ግዛቸውም ጊዜ ወስደው ሰፋ ያለ መልስ ሰጥተዉበታል።