ወደ ስድስት የሚጠጉ የፖለቲካና የየሲቪክ ማህበራት ስብስበ የሆነው የኢትዮጶያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ በዚህ ሳምንት በዳያስፖራ ለተቋቋመው የሚሊዮኖች ድምጽ ግብረ ኃይል በጻፉት ደብዳቤ ፣ ድርጅታቸው፣ በአገር ቤት ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈሉ ላሉ ታጋዮች ያላቸዉን አድናቆትና አክብሮት በመገጽል፣ አገር ቤት እየተደረገ ያለዉን የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ጎን እንደሚቆሙ አረጋገጡ።
ድርጅቶቹ በደብዳቤ ድጋፋቸውን ከመግለጽ ባሻገር ፣ በግብረ ኃይሉ የሚሳተፉ ተወካዮችን የላኩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለዉጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የኢትዮጵያዉያን መሰባሰብ አስፈላጊ እንደሆነም አስምረዉበታል።
ሸንጎም ሆነ የሽግግር ምክር ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አጀንዳዎችን በመያዝ ሕዝቡን ለትግል ለማነሳሳት ከፍተኛ
ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ፣ በተለያዩ ጊዜያትም አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ሲደግፉ የነበሩ ድርጅቶች እንደሆኑ ይታወቃል።
በዳያስፖራ የተቋቋመው የዳያስፖራ ድምጽ ንቅናቄ ከሸንጎ እና የሽግግር ምክር ቤቱ በተጨማሪ በርካታ ድርጅቶችን በማሰባሰብ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሚሊዮኖችን ድምጽ በመደገፍ አንጻር ከፍተኛ መነሳሳት እየታየ ነው። ግብረ ኃይሉ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ፣ ከማርች ፎር ፍሪደም ሲቪክ ማህበር፣ ከኢትዮጵያዊነት ሲቪክ ማህበር፣ ሎስ አንጀለስ ከሚገኝ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲኦና ሰብአዊ መብት ሲቪክ ማህበር ፣ ከቃሌ፣ ከደብተራዉ እና ከረንት አፌር ፓልቶክ ክፍልም አዎንታዊ ምላሽ እያገኘ ነው።