“እኛና አብዮቱ”
የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግ ደረስ ጸጸት አልባ ትዝታዎች
ጽሁፉን በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። የፍቅረሥላሴ ትዝታዎⶭ
ከኤፍሬም የማነብርሐን
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግ ደረስ በጣም አስደናቂም አስገራሚም የሆነ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። የደርግ አባልና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለአምባ ገነኑ ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እንደቀኝ እጅ ባገለገሉበት ዘመን የሆነውን ሁሉ እሳችው ካመኑበት አቋም በመንደርደር ተርከውታል። በጣም ብዛት ያላቸው የውስጥ ሰው ብቻ ሊያውቃቸው የሚችላቸው መረጃዎችን (ፋክትስ) መጽሐፉ አካቷል። ብዙ ሰው ወደ ጀርባ ገፍቶት የነበረውን የዚያን የደም ዘመን ትዝታዎች እንደ አዲስ ይቀሰቅሳል። ደራሲው መረጃዎችን በመሰብሰብና በተቀናጀ መልክ ታሪኩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማቅረባቸው ሊደነቁ ይገባል። ታሪክም ላቀረቡት ጽሑፍ እንደባለውለታ ያያቸዋል የሚል ግምት አለኝ። የዚያ አስከፊና በኢትዮጵያ ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ያለፈው የደርግ ቡድን አባል በመሆን ከድርጅቱ የተቆራኙ ቢሆኑም፣ ጽሑፉን በማዘጋጀታቸው ለአገር፣ ለወገን በአመዛኙ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ለማቅረባቸው መጽሐፉ ቋሚ ምስክራቸው ይሆናል።
መጽሐፉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግስትና የገዢውን የፊውዳል ሥርዓት ለማንበርከክና ደርግ በሥልጣን ተፈናጦ ለመቀመጥ እንዲያስችለው እርምጃዎች በወሰደ ቁጥር ያጋጠሙትን ተቃውሞዎች፣ የብሔራዊ ዘመቻንና የሶማሌን ወራሪ ጦር ለመመከትና ወደመጣበት ለመመለስ የተደረገውን ርብርቦሽና በተለይ አኩሪ የሆነውን የታጠቅ ጦር ሠፈር ግንባታና አስተዋጽኦ፣ የገጠርና የከተማ ቤት አዋጆችን ለማውጣትና ለማሰፈጸም የተደረጉ ጥረቶችንና ቅዋሜዎችን፤ የፖለቲካ ቅራኔዎችን ለመግታት፣ ለመገደብ፣ ለማምከንና ብሎም የኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን አምባ ገነንነት ለማረጋገጥ የተደረጉ ፍልሚያዎችን በሰፊው ተንትኗል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከተፈጸሙት ብዙ ግዙፍ ስሕተቶች አንጻር ሲታይ የደራሲውን ጸጸት አልባነት፣ ይባስም ብሎ ለነዚህ ስሕተቶች መከላከያ ለማቅረብና ኃላፊነትን ለሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ለማስተላለፍ መሞከሩ የመጽሐፉ ጉልህ ደካማ ጎን ነው። መጽሐፉን ካነበብኩ በኋላ “ደርግ ሰው ገደለ እንጂ፣ ኢትዮጵያዊነትን ግን አልገደለም” እየተባለ እንደ ቀላል ወርወር የሚደረገውን አባባል ወደ ትልቅ ሥሕተት እንደሚወስድ ድምዳሜ ላይ አድርሶኛል። ኢትዮጵያዊነት አሁን ለደረሰበት አስጊ ደረጃና አገሪቱ ያለዲሞክራሲ የጉልበተኞችና የዘረኞች መፈንጫና የአንድነት ኃይሎች መደበቂያና ማፈሪያ እንድትሆን ምክንያቱ ወያኔ ብቻ እንዳልሆነና፣ ደርግም ግዙፍ ሚና በእጅ አዙር እንደተጫወተ መጽሐፉ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በርግጥም ኢትዮጵያን በቀጥታ ፈቃደኝነትም ባይሆን፣ በእጅ አዙር ለወያኔ ገጸ በረከት ያቀረቡትና ፣ ለኢትዮጵያዊነት ስሜት የዝግታ የመጥፋት ጉዞ መነሻውና፣ ምናልባትም በእኩይ ወሳኙን ሥራ የሰሩት አሰከፊው የደርግ መንግስትና፤ በተለይም የግል ሥልጣንን ለማካበት ቆርጠው ማንኛውንም ጥፋት ከማድረስ ወደኋላ ያልተመለሱት ኮለኔል መንግስቱ ለመሆናቸው መጽሐፉ ደራሲው ባላሰቡት መንገድ በቂ ግንዛቤ ይሰጣል።
መጽሐፉ በአገሪቱ ላይ በቅርብ ዘመን በማይታወስ መጠንና ስፋት የጭካኔ መረቡን ዘርግቶ በሺዎች ለሚቆጠሩ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ጥፋት ዋና ምክንያት የሆነው ደርግን የውስጥ አሰራር አቅርቦልናል። ምንም እንኳን ደራሲው መንግስቱን “ቆራጥና “ከፍተኛ “የሃገር ፍቅር” እንደነበራቸውና፣ ይወስዷቸውም የነበሩት ጨካኝ ድርጊቶች አገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሳ ለማየት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ ለማሳየት ቢሞክሩም፣ በኮለኔሉ ቀጥታ ትእዛዝና አመራር ሰጭነት አብዛኛዎች ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉት በእጅ ወድቀው እስር ቤት ከተወረወሩ በኋላና ምንም አደጋ በደርግ መንግስት ላይ ሊያደርሱ በማይችሉበት ሁኔታ ስለነበረ፤ የሻምበሉ የኮለኔሉን በከፊልም ቢሆን መልካም ገጽታ ለማቅረብ ያደረጉት ሙከራ ብዙም አልተሳካላቸውም።
ሊቀ መንበሩ ለምን ይሆን እንዲህ ቃታን በቶሎ የመሳብ ፈንጭ (ትሪገር ሃፒ) የሆኑት? ከድንቁርናና ጅልነት ይሁን? ምናልባት ከመናቅ ሳቢያ በተፈጠረባቸው ድብቅ የበታችነት ስሜትና የበቀል ጥማት ይሆን? ለምን ይሆን እንዲህ ለፍትሕና ለርሕራሔ ዕውር ያደረጋቸው? መጽሐፉን ማንበብ ስጀምር ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ በትንሹም ቢሆን አገኛለሁ የሚል ግምት ነበረኝ። ከመጽሐፉ ያገኘሁት ግን አምባ ገነኑን መንግስቱን ማድነቅን፣ ታላላቅ ወንጀሎችን አድበስብሶ ማለፍን፣ የፈረደበትን “የፊውዳል” ሥርዓትን ማውገዝን፤ ላስከፊ ግድያዎች ራሳቸው የሾሟቸውን ዕድለ ቢስ ጄነራሎችን፣ ከመንግስቱ ለየት ያለ አቋም የወሰዱትን የደርግ አባላትን፣ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የወዝ ሊግ፣ ወዘተ መሪዎችንና ጀሌዎችን ተጠያቂ ማድረግን፤ መንግስት እንደአባት ዜጎችን በርሕራሔና በፍትሕ መዳኘት ይገባው የነበረ መሆኑን ተዘናግተው ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ሟቾችንና ተበዳዮችን ተጠያቂ አድርጎ ማቅረብን፤ ወዘተ ብቻ ነው። ቢያንስ ጸጸት አልፎም ይቅርታ መጠየቅን አላየሁበትም። በመሆኑም መጽሐፉ በጣም ረብሾኛል። ጸሐፊውም እኔን በበኩሌ ቅር አሰኝተውኛል።
መኖር ደጉ ደራሲው እንኳን ይህንን ለመጻፍ በቁ
ሌላው በጣም አስገራሚው የመጽሐፉ ይዘት ደራሲው እርሳቸው ከሞት ተርፈው ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ቢበቁም፣ ይህንን ዕድል በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ያላገኙት ባብዛኛው በሳቸውና በግብረ አበሮቻቸው የጭካኔ ሥራና ውጤት መሆኑን ለጥቂት እንኳን ቆም ብለው ያላሰቡ መሆኑ ነው። እሺ ኢሕአፓና ሌሎችም ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት የደርግ ተለጣፊዎች ደርግ ባደረሰው ደረጃም ባይገመት፣ በወሰዷቸው የተሳሳቱ የፖሊሲ አቋሞች ሳቢያ ለብዙ ንጹኃን ኢትዮጽያውያን መጥፋት ምክንያት ሆነዋል። ይህ ማናችንም ልንክደው የማንችለው ሀቅ ነው። ወንጀለኛን በፍርድ ቤት የማቅረብ ሥራ በኢትዮጵያ ባሕልና ወግ አንዲሁም በፍትሐ ነገስትም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ለረጅም ሲሰራበት የነበረ መሆኑን ደራሲው የተገነዘቡ አይመስለም። ለእስር የተዳረጉት ሁሉ ለምሳሌ እንደ ልጅ ካሳ ወልደማርያም፣ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ብርሐነ መስቀል ረዳ፣ ኃይሌ ፊዳ፣ ኅልቆ መሳፍርት የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የወዝ ሊግ ወዘተ አባላት ያለ ፍርድ እየተወሰዱ መረሸንን በሚመለከት ስለተደረጉ ሥሕተቶች ደራሲው ትንፍሽ እንኳን እንዴት አይሉም? የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ በባሕሉ ከፍ ያለ የፍትሕ መለኪያ ያለው ነው።
እንዲህ እንደወንጀለኛ ደርግ የሚኮንናቸው ንጉሥ ኃይለሥላሴ እንኳን በትረ መንግሥታቸውን ከጅለው ለነበሩትና ብዙ ባለሥልጣናትን ያለፍርድ ወዲያው ለረሸኑት ለጄነራል መንግስቱ ንዋይ እኮ ትልቅ ችሎታ ያላቸውን ተከላካይ ጠበቆች እንዲቆሙላቸው የፈቀዱ ሰው ነበሩ። እንዴት ደርግ ወደተራ ሽፍትነት ወርዶ ያለሕግ አፋጣኝ የግድያ ውሳኔዎችን (ሰመሪ ኤክሴኪውሽን) ማስተላለፉንና በመሆኑም የብዙ ሺሕ ንጹኃን ዜጎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ሃያ ዓመታት እስር ቤት ከርሞ መልካሙን ከመጥፎ ለመለየት ጊዜና ቦታ ያጋጠመው ሰው የፍትሕን መስፈርት አለመሟላት መመልከት ያዳግተዋል? የሳቸውስ መንግስት በያዘው የሥልጣን መጠንና ስፋት ሳቢያ የኃይል እርምጃ አወሳሰድን ተመጣጣኝነት መንገዘብ ይገባው እንደነበርና፣ ያንንም አለማድረጉ ከመንግስትነት ይልቅ ወደተራ ወንበዴነት እንዳወረደው የጊዜና ቦታ እድል ያገኙት ደራሲ እንዴት መመልከት ተሳናቸው? ታንክና መትረየስ፣ ተዋጊ አይሮፕላንና፣ በመቶ ሺ የሚቆጠር ወታደራዊ የሰው ኃይል የነበረው የደርግ መንግስት የሚያስተዳድረውን ሕዝብ መጨፍጨፍ እንደማይገባው እንዴት ሊረዱ አልቻሉም? ምርኮኛ የውጭ ጠላት እንኳን ተገቢ እንክብካቤና ፍትሕ ሊደረግለት ይገባዋል እንኳን የራስ ወገን። ደራሲው ግን “በወቅቱ ለተሰነዘረብን የጸረ አብዮተኞች እርምጃ ተገቢውን አጸፋ ነው የወሰድነው” ብለው ሊያስረዱ ይሞክራሉ።
በርግጥ ደርግን ተከትሎ የመጣው የወያኔ መንግስት በአገሪቱ ላይ ቀላል የማይባል የታሪክ ጥፋት አድርሷል፤ በማድረስም ላይ ይገኛል። በዚህ እውነታ ሳቢያ ግን ደርግ ያደረሰውን ጥፋት ወደጎን አድርገን መተው የለብንም። ደራሲውም ከዚያ ጥፋት የተማርኩት ይህንን ነው፤ መጪው ትውልድ ይህንን ስሕተት መድገም የለበትም፤ ብለው መምከር ይገባቸው ነበር። ነገር ግን እኝህ ሰው በሕይወት የመኖር እድለኛ ሆነው በተለይ ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ ብዙ ነገር ከዕለታዊ ግርግር ወጣ ባለ ሁኔታ የቀድሞ ሥራዎቻቸውን፣ አቋማቸውንና፣ ስሕተቶቻቸውን ለመመርመርና ለማውጣት ለማውረድ ዕድል ያገኙ ቢሆንም፤ ከጸጸት አይደለም መጽሐፉን የጻፉት። ያውም እንዲህ ግልጽ ለሆነ የደርግ ጥፋት። አገሪቱን ከፍተኛ ውድቀት ላይ ጥለዋትና ለዘረኞች አጋልጠዋት ያልሄዱ ይመስል መልካም ተሰርቶ እንደነበር በጽሑፋቸው ለማቅረብ መሞከራቸው የመጽሐፉ ታላቅ ድክመት ነው። እሺ በወቅቱ የዕውቀትና የልምድ ማነስና ውዝንብር የተጠናወታቸው እነርሱ ብቻ አልነበሩም። ስንቱ የተማረውም የሃገሪቱን ሥልጣኔ፣ ባሕል፤ ታሪክ ያላገናዘቡ፣ ለአገሪቱ የማይስማሙ መጤ ርዕዮተ ዓለሞችን ለኢትዮጵያ ይስማማሉ ብሎ አንዲያውም ደርግን በሚያስንቅ አኳኃን የሚያስተምርበት ጊዜ ስለነበረ፣ አገር የዕብደት ፈረስ ጭኖ በሚጋልብበት ዘመን ከደርግ አባላት የተለየ መጠበቅ ተገቢ አይሆንም። ከሃያ ዓመታት በኋላ ግን ይህን ላልተገነዘቡ ተመሳሳይ ይቅርታ ለማድረግ ያስቸግራል።
ደራሲው የጥላቻን ፖለቲካ በንጉሡና ባለፈው ሥርዓት ላይ አሁንም እያስተጋቡ መሆኑ
ደራሲው አሁንም የዚያ የአምባ ገነንነትን ሥርዓትና ዓላማ በሚያደንቅ መልኩ፣ ደርግ እንደባሕልና ቋሚ መመርያው አድርጎ ሲከተለው የነበረውን ስሕተት ይደግሙታል። ለደራሲው አሁንም የቀድሞው “የገዥ መደብ” መጥፎ ስለነበር መደፍጠጥ ነበረበት፤ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች መመታትና መደምሰሳቸው ተገቢ እርምጃ ነበር፤ መቻቻልና ተሰባስቦ በጋራ መስራትን ሊያራምዱ ይሞክሩ የነበሩት የደርግ አባላትም ሆን ተቃዋሚ ኃይሎች ለሥልጣን የቋመጡ ብሎም መደምሰስ ይገባቸው የነበሩ ኃይሎች ናቸው፤ የሚለውን የዚያን የደርግ ዘመን ፕሮፓጋንዳ አሁንም ይደግሙታል። ይቃወሟቸው የነበሩትን ድርጅቶችና ግለሰቦች ጥላሸት የመቀባትና በጠላትነትም ፈርጆ የማጥፋትን የደርግ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ደራሲው አጥብቀው ከመተቸትና የስሕተቱን ጥልቀትና ያስከተለውን ውጤት በግምት ከማስገባት ይልቅ፣ አሁንም ስለልክነቱ አንባቢን ሊያሳምኑ ይሞክራሉ።
ገና ምዕራፍ ፩ እና ፪ ላይ በቀድሞው ሥርዓት የነበረውን የሕዝብ ኑሮም ሆነ የአገሪቱን የዕድገት ደረጃና አገሪቱም ለነበረችበት አጠቃላይ ችግር ማነው ተጠያቂ ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በደርግ ዘመን በውይይት ክበብም ሆነ በካድሬዎችና በፕሮፓጋንዳ በራሪ ወረቀቶች ያሰለቸን የነበረውን ክርክር እንደ አዲስ ሊያቀርቡልን ይሞክራሉ። ምናልባት ደራሲው አነኚህን ምዕራፎች የጻፉት በዚያው ክፉ ዘመን መሆን አለበት እንጂ ለአሁኑ ዘመን ሰው ይዋጥለታል ብለው ያደረጉት አልመሰለኝም። ለምሳሌ ገጽ 5-6 ላይ እንዲህ ብለዋል። “
በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ስናንቀላፋ ለመቆየታችን ዋነኛ ምክንያትና ተጠያቂ ሆኖ የሚቀርበው፤ በአገራችን ሕዝቡን ለመከራና ለችግር የዳረገው፤ ለዘመናት በህዝቡ ጫንቃ ላይ ተንሰራፍቶ የነበረው የዘውድ አገዛዝ ሥርዓት፣ የዘር ግንድ እየቆጠሩ በተከታታይ ሲገዙን የነበሩ ንጉሳዊ መንግሥታት እንደነበሩ ለመረዳት አያስቸግርም። እነዚህ ንጉሳዊ መንግሥታት አገሪቱን ለኋላ-ቀርነት የዳረጓት ከመሆናቸውም ባሻገር በሕዝቡ ላይ ወደር የሌለው ግፍና በደል አድርሰውበታል።
እኔ እንኳን የንጉሥን ሆነ የፊውዳልን ሥርዓት የመደገፍም ሆነ መመለስ አለበት የሚል አቋም የለኝም። ብዙ መሻሻልና ለውጥ ያስፈልግ የነበረ መሆኑ አይካድም። ነገር ግን በወቅቱ አገሪቱ ለነበረችበት ኋላ ቀርነት አስተዋጽኦ ያደረጉት በዋናነት የአገሪቱ አፍሪካዊ ጂአግራፊ፣ አስቸጋሪ የነበረ ባሕል፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ለበላይነት ያደርጉት የነበረውና አሁንም የቀጠለው የእርስ በርስ ፉክቻ፣ የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ፤ የቅኝ ግዛት አራማጆች አውሮፓውያንና ኢትዮጵያ የባሕር ወደቦቿን እንዳትጠቀም አሁን ድረስ እየታገሉ የሚገኙት የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ፣ ለሥልጣኔ አመቺ ያልነበሩ ከማንም የአገር መሪ አቅም በላይ የነበሩ የተወሳሰቡ ብዙ ምክንያቶች መሆናቸውን መካድ አይቻልም። በደራስያን ዘውዴ ረታ፤ ፋታውራሪ ተክለ ሐዋርያት፣ ወዘተ የተጻፉ መጻሕፍትን ስናነብ የምንገነዘበው ለአገር ሥልጣኔ ማምጣት ቀላል ነገር እንዳልሆነና በአብዛኛው ከተራ ተዋንያን ችሎታ ውጭ የሆኑ ለተለያዩ ሥልጣኔዎች፣ ሀሳቦች፣ የአሰራር ልምዶችና፣ ዘይቤዎች የመጋለጥ ዕድል (ኤክስፖዠር) በማግኘት የሚወሰን ጉዳይ እንደሆነ እንገነዘባለን። በስሜታዊነት በመነሳሳት የድሮውን መንቀፍ ይቻላል። ማጣፊያውን ግን ማንም በቅጡ አያውቀውም። የቀድሞ መሪዎች የግዜያቸው ሰዎች ነበሩ። በግዜያቸው ከነበረው አርቀው አለማሰባቸው ሊያስቀጣቸው የሚገባ አልነበረም። በወቅቱ ሊያደርጉ ለሚገባቸውና በሥልጣን ለመቆየት ከማሰብ ለሚወስዷቸው (ለምሳሌ ወያኔ በአሁኑ የሰለጠነ ዘመን እያካሄደ ያለውንና በሥልጣን ለመቆየት ሲል ከዓለም ሕዝቦች የመጨረሻነቱ የተረጋገጠበትን የዜጎች የመናገር፤ የመጻፍና፣ በነጻ የማሰብ መብት አፈናን የመሰለ) እርምጃዎች በእርግጥ ገዢዎች ሊጠየቁበት ይገባል። ከላይ ደራሲው የጻፉትን ለመሰለ የተስፋፋ ኃላፊነት ግን ተጠያቂ አድርጎ ማቅረብ አይገባም።
እስቲ ገምቱት ከዚያ ሁሉ የተማሪ ትግልና የደርግ ጭፍጨፋ በኋላ የደረስንበትን። ከቋንቋ ጥያቄ በቀር የአብዛኛው ዘር ቀልጦ የሚዋሐድባት (ሜልቲንግ ፖት) አገር መገንባታችን ቀርቶ አዲስና ከአድዋ በመጡ የንዑስ ብሔረሰብ አባላት አምባ ገነኖች ተገዢነት የወደቅን መሆኑን ተገንዝበው እንዴት እንዲህ ያለ የተገላቢጦሽ ውስጥ ወደቅን ብለው መጠየቅ ሲገባቸው፤ ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ጠብቆ ነጻነቷን ያስረከበውን ትውልድና አባላት ለሁሉም የአገሪቱ ኋላ ቀርነት ተጠያቂ አድርገው አቅርበውታል።
ጎበዝ አንዲት ባሕር በር እንኳን ለማግኘት ለዘመናት የነገሡት ነገሥታት ከአህመድ ግራኝ፣ ቱርክ፣ ግብጽ፤ ፈረንሳይ፤ ጣልያን፣ እንግሊዝ ወዘተ ጋር ያደረጉትን ፍልሚያና ትግል እንኳን እናስታውስ እስቲ። አሁንስ ቢሆን ከወያኔና ከሻቢያ ጋር ያለንበትን በወደብ ሳቢያ ፍጥጫ እስቲ እንመልከት። ሥልጣኔ በቀላሉ ወይም ስለተመኘነው ብቻ አይመጣም። ሥልጣኔ የብዙ ውስብስብ ጉዳዮች መቀናጀት ውጤት ነው። የአንድ መደብ አባላት የሕዝብ አባላት ናቸው። ያላቸውም የንቃት ደረጃ ካካባቢያቸው የሚለይ አይደለም። ፊውዳልም በለው ገበሬ ከአጠገቡ ራቅ ብለን ሰከን ባለ ትኩረት ብናየው ሁሉም እንደጉንዳን የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለመምራት የሚታገልና የሚሯሯጥ ፍጡር ነው።
እንዲያውም በዓለም ሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ደርሰው ዓለምን የሚያንቀሳቅሱትና ለኛና ለብዙ የዓለም ስደተኞች መጠለያ እየሰጡ ያሉት አገሮች እንደኛ በስሜታዊነትና ጥላቻ ተነሳስተው የነበራቸውን ሁሉ ደምስሰው አሁንም ባለመቻቻል መርሆ የሚመሩት አገሮች ሳይሆኑ፣ ባህላቸውን፣ እያንዳንዱን ሃብታምም ሆነ ድኃ የአገራቸውን ዜጋ መብቱንና ደኅንነቱን በመጠበቅ የጥላቻ መርዝ በአገራቸው ባልነሰነሱት አገሮች አንደ አሜሪካና ምዕራብ አውⶂፓ በመሰሉ አገሮች ነው። በአረቡም አገር እንደ ሊቢያ፤ኢራቅ፤ ሶሪያ ወዘተ በመሰሉ “የባአዝ ፓርቲ አብዮት” ባካሄዱት ሳይሆን እንደ ሞሮኮ፣ዮርድኖስ፣ ሳውዲና፣ አረብ ኤሚሬቶች ባሉ አገሮች ነው። አፍሪቃ ውስጥም ቢሆን ደቡብ አፍሪቃን፤ ቦትስዋናንና፣ ጎረቤታችን ኬንያንም እንመልከት። የደቡብ አፍሪቃው ማንዴላ የጥላቻን መርዝ ከመነስነስ ይልቅ በባርነትና በእሥራት ይዘውት የነበሩትን ነጮች በመቻቻል አብሮ መኖር ይሻላል ብሎ አይደል እንዴ ያስተማረውና የኛን ሰዎች ጨምሮ ለብዙ የአፍሪካ አምባ ገነኖች ተበዳይ ለሆኑ ሰዎች ደቡብ አፍሪቃ ለመጠለያነት ደረጃ የደረሰችው? ኬንያስ ብትሆን ለብዙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ተቀባይ የሆነችው የኛን የመሰለ “አብዮት” ያላካሄደች በመሆኑ አይደለም? ቦትስዋናስ። ወያኔ የሚያራምደውን የጥላቻ ፖለቲካ ግን አውሮፕላን አብራሪው ካፒቴን ጭምር ከነአይሮፕላኑ የሚሸሽባት አገር ሆናለች።
የመጽሐፋቸው መጨረሻ ገደማ ደራሲው ትንሽ አይናችው ተከፈተ መሰል ገጽ 411 ላይ እንዲህ ብለዋል፡፡
ከእኛ በፊት የነበሩት መንግስታት የአገሪቱን ነጻነትና የህዝቧን አንድነት ለማስጠበቅ በየአቅጣጫው የሚከፈትባቸውን ጦርነት ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ተግባር ላይ ተሰማርተው ስለነበር የተስፋፋ የልማት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጊዜውም ሁኔታውም የማይፈቅድላቸው በመሆኑ በሰለጠኑ አገሮች የሚታየውን ዓይነት የኢኮኖሚ ልማት አልተውልንም።
ደራሲው ይህንን ሐቅ ለመጻፍ ለምን 410 ገጽ እንደወሰደባቸው ባይገባኝም ይህች የመጨረሻዋ ጥቅስ የደራሲውን መጽሐፍ መሠረትም ሆነ የደርግ መንግስትን የሃያ ዓመት ርዕዮት ዓለም ዋጋ ቢስነት ታመላክታለች። ምክንያቱም ደርግም ሃያ ዓመታት ያሳለፈው ይህንኑ ሥራ በመሥራት ነበር። ከዓረቦች፤ ከሶማሌ፤ ኢትዮጵያን ያለባሕር በር ካስቀሯት ከወያኔና ከሻቢያ ወዘተ ጋር የተደረጉት ያላቋረጡ ፍልሚያዎችን ደራሲውም በሰፊውና ምናልባትም የመጽሐፋቸው ጠንካራው ጎን በሆነ ዝርዝር በምዕራፍ 17 ላይ በጥሩ አስቀምጠውታል። ከቀድሞዎቹ መንግስታት የሚለዩበት ግን የጥፋታቸው ዒላማዎች የውጭ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያ ቅን የሚያስቡ ነገር ግን ከመንግስቱ ኃይለማርያም የተለየ አመለካከት የነበራችው ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጭምር መሆኑ ነበር። የደርግ መንግስት በዚህ ባሕርዩ ከሌሎቹ የቀድሞ መንግስታት ይለያል።
ሻምበል ፍቅረሥላሴና ደርግ የሚኩራሩባቸው የመሬት ይዞታ አዋጅ፤ የከተማ ቤትና መሬት አዋጅ፣ የሰራተኛ አዋጅ፣ ወዘተ ሁሉ ከውጤታቸው አንጻር ሲመረመሩ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። መሠረታዊ ለውጥ ይሻላል እያልን የረጋ ለውጥን እንደምርጫ መገምገም ባለመቻላችን ሳቢያ፣ የስህተቶቻችንን መራራ ጽዋ አሁን በውስጥም ሆነ በውጭ በስደትና በውርደት እየተጎነጨናት እንገኛለን። ያኔስ ተሳስተን አላወቅንም። አሁንም ግን ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ያንን የሚያንገሸግሽ ክርክር ሊደግሙልን ይሞክራሉ። ስለሰራተኛው ኑሮ እንዲህ ይላሉ።
የካፒታሊስት የምርት ግንኙነት በፈጠረው አነስተኛ የሰራተኛው መደብ ላይ ፊውዳሉና ካፒታሊስቱ በጥምረት ሲፈጽሙት የነበረው ግፍና በደል በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት በእንግሊዝ ሰራተኛ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም ከነበረው በማይተናነስ ደረጃ አስከፊና አሰቃቂ ነበር።
አሁን ይህን የመሰለ አጻጻፍ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ምስጢሩን በቅጡ ያልተረዳውን ከማወናበድ በቀር። ያንድ መንግስት ሥራ መሆን ያለበት በሃብት በገንዘባቸው ሥራን መፍጠር የሚችሉትን መርዳትና ማበረታታት መሆን ሲገባው፣ ሥራ በሌለበት አገር አሰሪውን ስናስርና ስንገድል ከረምን። እስቲ በሉ የእንግሊዝ ሰራተኛን አሁን እዚህ ውስጥ ምን ዶለው? ከዚያስ በላይ ይኽው የእንግሊዝ ሰራተኛ ከሃብታሙ ጋር ሆኖ የሰራው ትንግርትስ አይደል እንዴ ለዓለም ሥልጣኔ በር ከፋችም ሆነ መንገድ ቀዳጅ ሆኖ እንግሊዝን “በግዛቴ ጸሐይ አትጠልቅም” እንድትልስ ያበቃት? አሁንስ የዓለምን ሀብት ከአጥናፍ አጥናፍ የሚያሽከረክሩት እነሱና የነሱው ውልዶች አይደሉ እንዴ?
እሺ ያኔስ ይሁን ስሕተታችንን አልተረዳንም ነበር። ዘመኑም ይኸን ሁሉ አዙሮ ለማየት አያስችልም ይባል። በውጭ የመማር ዕድል የነበራቸው የተለያዩ ድርጅቶች መሪዎች የመቻቻልንና የዲሞክራሲን ትምህርት ሳይሆን ይዘውልን መጥተው የነበረው፣ የአጥፋው ደምስሰውን ቲዎሪ ነበር። በዚህ ደርግን በጣም አናማውም። አሁንም ግን ያንኑ መልሰን መላልሰን ለሕዝብ መጋት ግን አይገባንም ደራሲው እያደረጉ እንዳሉት። በአንድ ወገን አገሪቱ በጣም ወደኋላ የቀረች ነበረች፣ በፍጥነት ማደግም ያስፈልጋት ነበር ካልን በኋላ፣ በሌላ ወገን ገንዘቡን የመጠቀም፤ ኪሳራን የመቀበል ልምዱ (ሪስክ ቴኪንግ) ዕውቀቱና፤ አድርግ አድርግ ባይነቱ (ኢኒሼቲቭ) ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል ገና ከንⶽጩ እንዲመታ በጥላቻ የተመረዘ ፕሮፓጋንዳ ይነዛና ከዚያ አገሪቱ ወደኋላ ቀረች እያልን ደግሞ ያንኑ የተደመሰሰውን የህብረተ ሰብ ክፍል በኃላፊነት እንፈርጃለን። “ጥረህ ግረህ ብላ” ብሎ እግዜር የፈረደበትን ሰው ለምን ነግደህ፣ አርሰህ አተረፍክ ብሎ ለረሸነ መንግስት፣ በአሁኑ ሰዓት ጸጸትን እንጂ “አብዮቱ” ተቀዳጅቷቸው ስለነበሩ ደሎች መሆን አይገባውም።
የደራሲው አምባ ገነንነትን የማድንቅ አባዜ
ደራሲው የዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ በፍጹም የማይዋጥላቸው መሆኑን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በግልጽ ያስቀምጣሉ። በተለይ ለአምባ ገነኑ መንግስቱ ያላቸውን ክብርና አገር የመምራት ችሎታ ደጋግመው በማድነቅ ጽፈዋል። ደራሲው “አንድ ሕዝብ . . . የነቁ ወይም የተማሩ ግለሰቦች የተሰባሰቡበት የፖለቲካ ቡድን ወይም ድርጅት ያስፈልገዋል። . . . ሕዝብ መሪ ያስፈልገዋል። . . . ‘ሰፊው ህዝብ ታሪክ ሰሪ ነው’ የሚለው አባባል . . . ብልጣ ብልጦች የሚሰነዝሩት መፈክር ከመሆን ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም” ይሉናል። ይህ አባባል የአምባ ገነንነት ሥርዓት ናፋቂነትን ያንጸባርቃል። የዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሚያስተምረን ተቃራኒውን ነው። በእርግጥም የዲሞችራሲ መብቱን ያልተነጠቀ ሕዝብ ታሪክ ይሰራል። ባፍሪቃ ደረጃ እንኳን ሩቅ ሳንሄድ ቦትስዋና የዲሞክራሲ ሥርዓትን መሠረታዊ መርሆ የምትከተል አገር ይኸው በሁሉ አቅጣጫ በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ በመጓዝ ላይ ትገኛለች። በተለይ የጋዜጣ፤ የጽሑፍና የሀሳብ ነጻነት በሰፊው የሚንሸራሸርባት አገር ሆናለች። ችግር የለም ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ቦትስዋና ችግሯን ለመፍታት በተሻለ የፖለቲካ ጉዞ ላይ ትገኛለች። ሌሎችም አንደ ኬኒያና ደቡብ አፍሪቃ ዓይነት አገሮች በሥልጣኔ ጎዳና ወደፊት እየተጓዙ ይገኛሉ። የእኛዎቹና ሌላው የነሱ መሰል ኤርትራ የኢትዮጵያ ወጣቶች የግራ ዘመም ፖለቲካ ውጤቶች ናቸው።
ደርግ በአገሪቱ ላይ ከመጨካከንና መጠፋፋት ሥርዓት ይልቅ የመቻቻልና የተለያዩ ሃሳቦች ሊንሸራሽሩ የሚችሉበትን ሥርዕት በመጠኑም ቢሆን ለመምረጥ ዕድሉን አግኝቶ አንደነበረ እሳቸው ባይነግሩንም ብዛት ካላቸው ከደራሲው ገለጻዎች ልንረዳ እንችላለን። ከስልሳዎቹ ከተገደሉት መሃል የደርግ አባል የነበሩት፤ ሰባቱ የደርግ አባላትም ሆነ ምክትል ሊቀ መንበር አጥናፉ ከመንግስቱ የተሻለ አብሮ በውይይት የመስራት እንጂ፣ቃታ የመሳብ ፍቅር ያልነበራቸው ይመስላሉ። ነገር ግን ደራሲው የመንግስቱን ከግድያ መትረፍ አሰመልክቶ የጻፉትን ስናይ፣ በመትረፋቸው እፎይ ያሉ ይመስላል። መቼም አንድ መሪን መግደል ትልቅ ሥሕተት ነው። የሚከተለውንም መገመት አይቻልም። ነገር ግን ወደኋላ በማያ መነጽር (ሃይንድ ሳይት) ስናየው በመንግስቱ ያኔ መትረፍ የተከተለው ዘመን ብይኖሩ ሊከተል ይችል ከነበረው አስከፊ ዘመን የባሰ መጥፎ ይሆን ነበር ለማለት በሙሉ ልብ ለመናገር ያስቸግራል። ያው አስከፊው መተላለቅ፤ የአገሪቱ ብርቅዬ ወጣትና ምሁራን፤ ቅን አሳቢና የሃገር ፍቅር የሚያቃጥላቸው ዜጋዎች በአምባ ገነኑ ነፍሰ ገዳዮች ከየእስርቤቱ እየተመዘዙ ተጨፍጭፈዋል። ብሎም ዘረኛውን ወያኔን ሊቋቋሙ ይችሉ የነበሩ አውራ መሪዎች በማለቃቸው፤ ኢትዮጵያን ለአገር አስገንጣዮች አውላላ ሜዳ ላይ አጋልጠዋታል። ደራሲው ግን እንዲህ ብለዋል።
ሊቀ መንበሩ ተገድለው ቢሆን ኖሮ መሠረታዊ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ ይከተል እንደነበረ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ሊቀመንበር መንግስቱ የደርግ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸው አሌ የማይባል ኃቅ ነው። የመናገር፡ የማስማማት፡ የማግባባትና የማሳመን ችሎታቸው ከፍተኛ ስለነበር አብዛኛውን የደርግ አባላት ከጎናቸው ለማሰለፍ ወይም የሚፈልጉትን ውሳኔ እንዲተላለፍ ለማድረግ እምብዛም አይቸገሩም ነበር። (ገጽ 263)
ይህ ጥቅስ በኔ ግምት በአንድ ወገን በመንግስቱ መትረፍ በወቅቱ እፎይ ያሉ ሲያስመስላቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመጽሐፋቸው ደጋግመው ከነማስረጃ ያቀረቡትን ትረካ በጣም ይቃረናል። መንግስቱ ኃይለማርያም ከሀሳባቸው “በተጻራሪነት የቆመን ግለሰብ ወይም ድርጅት አምርረው ይጠላሉ” (ገጽ 263) ። የኋለኛው አብባላቸው ትክክለኛው ይመስለኛል። ኮለኔሉ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ከሚል የሥልጣን ጥማት የተነሳ፣ እንኳን ሰውን ሊያስማሙና ሊያግባቡ ቀርቶ፣ ሁሉን ፈጅተው ነው የጨረሱት።
ምንም እንኳን ደራሲው የኮለኔል መንግስቱን “ችሎታ” በማድነቅ፣ ለራሳቸው ለደራሲውም ባብዛኛው መድህን እንደነበሩ አድርገው ያቀረቧቸው ቢሆንም፤ ኮለኔል መንግስቱና የደርግ አባላት የወሰዷቸው የግፍ እርምጃዎች በሙሉ በኃይለሥላሴና በባለሥልጣኖቻቸው፣ በነአማን አንዶምና ተፈሪ በንቲ፤ አንዲሁም በኢትዮጵያ ታሪክና ባህልም ሊፈጸሙ ቀርቶ ሊታሰቡ እንኳን የማይችሉ አረመኔያዊ እርምጃዎች ነበሩ። ሕዝቡ ለዚህ ደረጃ ጭካኔ የተላመደ አልነበረም። ለዚህም ነው ቃታ በቶሎ የመሳብ ፈንጪ የሆኑት ኮለኔልና አባሪዎቻቸው የደርግ አባላት የተሳካላቸው። የኝህም የጨካኝ መሪ ዘመን በባሕሏ፣ በጠላት ላይ ባደረስችው ድሏ፤ በመልካምና ደግ ሕዝቦቿ፣ ወዘተ ትኮራ የነበረችውን ኢትዮጵያን ድሮስ ከአፍሪቃውያን ምን ይጠበቃል ከአረመኔነት ሌላ ብለው የጥቁርን ሕዝብ ለመስደብ ላኮበኮቡ ጠላቶች በምሳሌነት እንድትፈረጅ አድርጓታል። ዜጎቿም አንገታችንን በዓለም ዙርያ እንድንደፋ አስገድዶናል።
የስልሳዎቹ የቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ
ደራሲው የፍትሕንና የሰው ልጆችን መብት መከበር በሚመለከት ትልቅ ድክመትን አለያም የዋህነትን አሳይተዋል። ለምሳሌ “በስድሳዎቹ ላይ የተላለፈው አሳዛኝ ውሳኔ “(ገጽ 149-53) በማለት የሰየሙት ንዑስ ክፍል ኃላፊነትን ከመውሰድ አንጻር መባል የነበረበት “በስድሳዎቹ ላይ የፈጸምነው አሳፋሪ የሞት ቅጣት” ነበር። ኃላፊነቱንም በጋራ ብቻ ሳይሆን በግልም መቀበልና ጸጸት ሊያሳዩ ይገባቸው ነበር። ጄነራል አማን አንዶምን የመግደል ጥንስስ ሲያጫውቱን (ገጽ 149) “እነኚህ ቂጣቸውን ካልጠረጉ ውርጋጦች ጋር ከእንግዲህ ወዲያ መሥራት አልችለም” ብለው አማን አንዶም ከጄነራል ግዛቸው ጋር በስልክ ያደረጉትንና በሁለት ጓደኛሞች መሀል የተደረገን ጭውውት በድብቅ በቴፕ ተቀድቶ የደርግ ጀሌ አባላትን ቅጽበታው መንፈስ (ፓሽን) በማነሳሳት አንዲሰሙትና ጀኔራሉን ለማስገደል ስሜት መቀስቀሻነት ኮለኔሉ እንደተጠቀሙበት ነግረውናል። የዚህን ሰይጣናዊ ዘዴ ከሃያ ዓመታት በኋላ ከማውገዝ ይልቅ፣ ይባስ ብለው ምክንያት በማድረግ “በጀኔራል አማን ዕብሪትና ንቀት፣ ራስ ወዳድነትና የማይረካ የሥልጣን ጥማት የተነሳ ባከበራቸውና በሾማቸው ደርግ ላይ አምጸው መነሳታቸው ለ59 ሰዎች መገደል ምክንያት ሆነ” (ገጽ 153) በማለት ለአንባቢ ሊነግሩና ኃላፊነቱን በሟቹ ጄኔራል አማን አንዶም ላይ ሊደፈድፉ ይሞክራሉ። ነገር ግን ትንሽ ቀደም ብለው የ59ኙ ባለሥልጣናት የሞት ፍርድ “ኮለኔል ዳንኤል በዝግታ ወደ አዳራሹ” ገብቶ (ገጽ 152) የጄነራሉን መገደል ከመናገሩ በፊት በደርጎች ተወስኖ እንደነበር ቀደም ባለው ፓራግራፍ ላይ አጫውተውን ነበር።
ለጄነራሉ መገደልም አስተማማኝ የሆነ ምንም ማስረጃ አላቀረቡም። እንዲያውም አማን አንዶም ከኤርትራዊነታቸው ይልቅ ኢትዮጵያዊነታቸው ያመዘነባቸውና “ሕዝብ ሆ ብሎ ከሥልጣን ያወረድናቸውን የኃይለሥላሴ መንግስት ባለሥልጣናትን ከስር ቤት በማስወጣት መልሰው በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ እቅድ እንዳላቸው በመረጃ ደርሰንበታል” ብለው ኮለኔሉ ለስብሰባው እንደተናገሩ አጫውተውናል (ገጽ 149)። እስከ ዛሬ ይመስለን የነበረው አማን አንዶም ኤርትራን ለማንስገንጠል ይዶልቱ እንደነበር ነበር። በዚህ ወያኔ ባመጣብን የዘር ክፍፍል ሳቢያ በጎሪጥ ለምንተያይ ሰዎች ኢትዮጵያ ከተለያዩ ብሔረሰቦች በመጡ ፍጹም ፍቅር በነበራቸው ሰዎች ትመራ እንደነበርና በዘር ያበዱት የዘመኑ መሪዎች ኢትዮጵያዊነት ላይ የጀመሩት ዘመቻ ሕዝቡ በፍላጎቱ ሳይሆን፣ በጉልበት እንደሆነ አንድ ማስረጃ ነው። ደራሲው ይህንን በማውጣቸው ይመሰገናሉ።
የሚያሳዝነው ግን እንደ ቀላል ነገር ለረጅም ጊዜ የአገሪቱ መሪ ስለነበሩትና፤ ኢትዮጵያን በምንመኘው ደረጃም ባይሆን ለሰለጠነው ዓለም ስላስተዋወቋትና የአፍሪካ አንድነት አባት ስለሆኑት ቀዳማዊ ኅይለሥላሴ እንዴት ባለ ዘዴ እንዳወረዷቸው በሰፊው በሚዘረዝረው መጽሐፋቸው ውስጥ፣ ስለአስተሳሰራቸው ሆነ አሟሟታቸው ይነግሩናል ብዬ ስጠብቅ ምንም ትንፍሽ አላሉም። ያሳዝናል። መቼም ረስተውት ሳይሆን አውቀው ተኝተውበት ነው። ይልቁንም ደራሲው ተቃዋሚዎች “ፋሺስት” አሉን ብለው ከፋሺዝም እንዴት ደርግ እንደሚለይ ለማስረዳት (ገጽ 245-47) ጊዜያቸውን ይፈጃሉ። ዒላማውን የሳተው ክርክራቸው “የተወሰኑ ሰዎች በመንግስት ላይ ተነሳስተው ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ከፍርድ ቤት ውጭ በተሰጠ ውሳኔ ቢገደሉ በፋሽስትነት የሚያስፈርጅ መለኪያ ተሟልቷል ማለት ይቻላል ወይ?” ብለው እንደ ደህና ንጹሕ ሰው ካንባቢ ጋር ክርክር ሊገጥሙ ይዳዳሉ። የፋሽዝምን ቲዎሪ ከሳቸው ጋር የመከራከር ማንም ፍላጎት አንባቢ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም። ከሳቸው ጋር መነጋገር የሚፈልገው የሚመስለኝ የነርሱ ድርጊት ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ ከፈጸመችው ወንጀል ይበልጥ አይበልጥ የሚለው ላይ መሆኑ ምነው በገባቸው።
የደርግ አባላትንና የወዝ ሊግ አባላትን ግድያ በሚመለከት ደራሲው ያቀረቡት
ከሁሉም የሚያሳዝኑት ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ናቸው። ወንድምና እህት፣ አባትና ልጅ የተለያየ አቋም ይዘው በፖለቲካ በማይስማሙበት ዘመን ጄኔራል ተፈሪ በንቲን በሚመለከት “ከውጭ አገር ተመልሶ በኢሕአፓ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ በመያዝ ሲንቀሳቀስ በነበረው ልጃቸው በዓይን እሸት ተፈሪ ግፊት ጀኔራል ተፈሪ በንቲ የኢሕአፓ ደጋፊ ከመሆናቸውም በላይ የድርጅቱን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ የታገሉ የደርጉ ሊቀመንበር ናቸው” (ገጽ 302)፤ እንዲሁም “መለሰ ማሩ የጄኔራል ተፈሪ ልዩ ጸሐፊ በመሆኑ ከልጃቸው በተጨማሪ ጄኔራሉ ለኢሕአፓ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት እንዲያገለግሉ ግፊት ያደረገባቸው እሱ እንደሆነ ታምኗል” (ገጽ 330) በማለት ተፈሪ በንቲን በኢሕአፓነት ለመፈረጅ የሚያቀርቡት ማስረጃ ይህን ከመሰለ አሉባልታ ያላለፈ እንዳልነበር ያሳየናል። ሌሎቹንም የደርግ አባላት የኢህሕአፓ አባላት ነበሩ ይሉናል። ቢያንስ ያ፲ አለቃ ኃይሉ በላይን አውቀዋለሁ። የኢሕአፓ አባል አልነበረም። ተፈሪ በንቲንም ሆነ ሌሎችን የደርግ አባላት ኢሕአፓዎች ነበሩ ብሉም ከክሳቸው በቀር አሳማኝ ማስረጃ አላቀረቡም።
በመቶ አለቃ ዓለማየሁና በመንግስቱ ስለተፈጠረው መቃቃር (ገጽ 314-18) እንዲህ ሲሉ ተርከዋል። መንግስቱ ሚኒስትሮችን የማሰራቸውን ትክክለኝነት ለማሳመን፤
“የተካሄደውን ዘረፋና የተፈጸመውን ውድመት ከፍተኛ ሆኖ ሳለ ሰምተው እንዳልሰማ፤ አይተው እንዳላየ በመሆን በምንቸገረኝነት አልፈውታል። ይህ ድርጊታቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያረጋግጥ ሆኖ በማግኘቴ እንዲታሰሩ አድርጌአለሁ” ብለው ገለጻቸውን እንዳበቁ የመቶ አለቃ ዓለማየሁ ለመናገር ከሊቀመንበሩ ፈቃድ እንኳን ሳይጠይቅ “ሚኒስትሮች ያንተ አሽከር ወይም ገረድ አይደሉም እንደፈለግክ የምታስራቸው” ብሎ … ከፍ ዝቅ አድርጎ ሌ/ኮሎኔል መንግስቱን ዘለፋቸው። . . . የዓለማየሁ ዘለፋ አልበቃ ይመስል ሞገስም በተመሳሳይ ሁኔታ በሚኒስትሮቹ መታሰር የተሰማውን ቅሬታ ገለጸ።
ያስገረመኝ ነገር መቶ አለቃ ዓለማየሁና ሻለቃ ሞገስ ከሰላሳ ዓመታት በፊት ቁልጭ ብሎ የገባቸውን የሰውን መብት መረገጥና የመንግስቱ ኃይለማርያምን ትልቅ ወንጀል ደራሲው እስካሁን የገባቸው አለመምሰሉ ነው። መቶ አለቃ ዓለማየሁ በሚኒስትሮቹ መብት መነካትና የፍትሕ መጓደል ሳቢያ ያሳየው ቁጣና አቋም ትክክል የነበረ ቢሆንም ደራሲው ይህንን አሁንም ያዩት አይመስልም። አሁንም ስለመንግስቱ መደፈር የሚንገበገቡና አለማየሁ ንግግራቸውን አቋረጣቸው፤ “አንተ” እያለ አናናቃቸው፤ “ከፍ ዝቅ አድርጎ … ዘለፋቸው”፣ ብለው የሚቆጩ ነው የሚመስለው። ይህንን በጣም ወሳኝና የማናውቀውን ዜና ማቅረባቸውን ባመሰግንም፣ የደራሲውን የፍትሐዊ ዳኝነት ደረጃ ዝቅጠትም አሳይቶኛል።
በተለይ መንግስቱ ከተገቢው የደርግ የውስጥ ደንብ አሰራር ውጭ በአምባ ገነንነትና ድርጅታዊ አሰራር ንቀት የሰከሩ ስለነበሩ ከሳቸው በጣም ይሻሉ የነበሩትን እነ መቶ አለቃ ዓለማየሁን ያጠፉበትን ዘዴ እስከ ዛሬ ኮለኔል መንግስቱ “ኢሕአፓዎችን አጠፋሁ፣ ለምሳ ሲያዘጋጁን ለቁርስ አደረስናቸው” እያሉ ቱልቱላ የነፉበትን ተልካሻ ማስተባበያ በሰባቱ የደርግ አባላት ላይ ያስወሩት ውሸት እንደነበረና፤ ኮለኔሉ የፈጸሙት ወንጀል ስይቀድሙኝ በሚል ሳይሆን ከንጹሕ ሥልጣን ጥማትና ለደርግ የውስጥ ደንብ ብሎም ለሕግ መገዛት እንቢተኝነት ሳቢያ መሆኑ ያልጠበቅኩት ዜና ነው። ደራሲው ግን ከ20 ዓመታት በኋላ እንኳን ይህ መሰረታዊ የደርግን የውስጥ ደንብ ጥሰት ሊያዩ አልቻሉም።
ሌላው አሳዛኝ ታሪክ የወዝ ሊግ አባላትን መታሰር ታሪክና አሟሟት የተረኩት ነው። የወዝ ሊግ አባልነታቸውን በሙሉ ስይሰርዙ የሰደድ አባል መሆናቸው ሲታወቅ ይቅርታ ቢጠይቁም ተይዘው ለእስር በኋላም ለሞት የተዳረጉትን በሚመለከት፣ ደራሲው ኮለኔሉ በጉዳዩ በጣም መናደዳችውን እንደትክክል በማቅረብ፣ አሳችውም የተናደዱ አንደነበርና በማንኛውም አገር የፓርቲ አሠራር ታሪክ የአንድ ፓርቲ አባል በሌላ ድርጅት ውስጥ በምስጢር አባል የሚሆነው ለስለላ ወይም በምስጢር የተያዙ መረጃዎችን ለመስብሰብ ነው በማለት ለኮለኔሉ አንደተናገሩ ይገልጻሉ። የሚያሳዝነው ግን የወዝ ሊግ አባላቱ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት ሁለቱ ደርጅቶች በቅርብ ይዋሃዳሉ ብለው ጠብቀው አብዛኛውን ጊዜያቸውን ይውሉ የነበረውም ለሰደድ ሥራ እንደነበረ ለተናገሩት፣ ደራሲው “ክስተቱ ድርጅታችን ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በአብዮታችን ላይ ከባድ አደጋ [በመጋረጡ ሰዎቹ እንደታሰሩና] ከዓመት በኋላም ብዙዎቹ እንደተገደሉ ተሰማ” ብለው ታሪኩን ገለጹልን። የሳቸው ቀጥተኛ እጅ ለሰዎቹ እስራት ምክንያት እንደነበር አልካዱም። ሚናቸውን ደፍረው በመናገራቸው አደንቃቸዋለሁ ምንም እንኳን ትረካውን ሳነብ ቀዝቃዛ ውኃ በጀርባዬ ላይ ሲሄድ ቢሰማኝም። ከ20 ዓመታት በኋላ እንኳን ምናለ “የወዝ ሊግ አባላት የሰጡት ማብራሪያ በቂ ነበር እኛ ግን በወቅቱ ይህንን ማየት ተስኖን ነበር” ቢሉን? ይባስ ብለው የወዝ ሊግ አባላት የታሰሩት ራሳቸው ሥራቸውን ስላመኑ ነው ከሚሉን?
ለማጠቃለል፣ ደራሲው ለጻፉት መጽሐፍና አዳዲስ የማናውቃቸውን መረጃዎች ላቀረቡልን ውለታ በጥልቅ ከልብ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ሌላም ካላቸው ከማቅረብ እንዳይቆጠቡ እንማጸናቸዋለን። ነገር ግን ለዚያች አንጀቷን በገመድ አስራ፣ እየተራበች፣ ለልጆቿ ትምህርት ቅድሚያ ሰጥታ፣ አሳድጋ፣ ትልቅ ደረጃ ይደርሱልኛል ብላ ስትጠብቅ፣ ከእስር ቤት እየተመዘዙ ከተረሸኑ በኋላ በጠራራ ፀሐይ ሬሳቸው በየመንገዱ ተወርውሮ ሬሳቸውን ለመውሰድ የጥይት ክፈይ እየተባለች ለተገፈተረችውና በሰደፍ ለተደበደበችው እናትና፤ ምሁር አልባ ለተደረገችው ኢትዮጵያ ደራሲውን ትንሽ ጸጸት እንኳን አሳዩ ብሎ መጠየቅ ብዙ መጠየቅ አይሆንም። ምናልባት በሚቀጥሉት ጽሁፎቻቸው ይህንን እድል ይጠቀሙበት ይሆናል ብዬ በተስፋ እጠብቃለሁ።