- የአቡነ ማትያስ የመነጋገርና የመደራደር አቅም ለጉብኝቱ መሰረዝ በምክንያትነት ተጠቅሷል
- የግብፁ ፓትርያርክ በስድስት ወራት ውስጥ ሦስት ጊዜ የጉብኝት ጥያቄ አቅርበዋል
- የአቡነ ታዎድሮስ ተደጋጋሚ ውትውታ ጉዳዩ ከሕዳሴው ግድብ ጋራ መያያዙን አመላክቷል
- የጉብኝቱ መሰረዝ በአቡነ ታዎድሮስ ጥያቄ እንደኾነ መዘገቡ ከመቅለል መጥቅለል እንዲሉ ነው
- ‹‹መንግሥት የግብፆችን ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱን የዲፕሎማሲው አካል አላደረገም››
(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፵፫፤ ፳፻፮ ዓ.ም.)
የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118ኛ ፓትርያርክ ፖፕ አቡነ ታዎድሮስ ባቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከትላንት ጀምሮ በግብፅ ሊያካሒዱት የነበረው የጉብኝት መርሐ ግብር የተሰረዘው በመንግሥት ክልከላ መኾኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለፋክት መጽሔት ገለጹ፡፡
ፖፑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጋራ ሲላላኩ የቆዩት ከመስከረም ወር 2006 ዓ.ም. አንሥቶ እንደኾነ የገለጹት ምንጮቹ፣ እስከ ጥር ወር ድረስ ኹለት ጊዜ የጉብኝት ጥያቄ መቅረቡንና ይዘቱም ቅዱስነታቸው (ፖፕ አቡነ ታዎድሮስ) ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ዘንድ ይፋዊ ግብዣ ከኢትዮጵያው መንበረ ፓትርያርክ እንዲቀርብላቸው የሚጠይቅ ነበር ብለዋል፡፡
የፖፑን የጉብኝት ጥያቄ የመንግሥት አካል እንዲያውቀው ተደርጎ በመንበረ ፓትርያርኩ እየተጤነና መደረግ ስለሚገባውም ቅድመ ዝግጅት በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋራ እየተመከረበት ሳለ ፖፑ ከጥር ወር በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ መጻፋቸው ተጠቅሷል፤ በዚኽ ወቅት የቀረበው ጥያቄም ‹‹እኔ ልምጣ›› ከሚለው ይልቅ ‹‹እናንተ ኑ›› በሚል የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ግብፅን እንዲጎበኙ የቀረበ ጥሪ/ግብዣ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ኹለቱ ጥንታውያንና ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት በትምህርተ ሃይማኖት አንድነታቸውና በጠበቀ ታሪካዊ ቁርኝታቸው እኅትማማች ቢኾኑም በብሉይ – ኢየሩሳሌም – የዴር ሡልጣን – የቅድስናና የታሪክ ይዞታ በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሳቢያ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮች ሌላ ተጨማሪ የመነጋገሪያ ነጥብ እንደሚኾን ከፖፕ አቡነ ታዎድሮስ ‹‹ተደጋጋሚና የተቻኮለ›› ውትወታ ለመረዳት መቻሉ ተነግሯል፡፡
ኹለቱም ፓትርያርኮች በጉዳዩ ላይ የታወቀውን የመንግሥቶቻቸውን አቋም ጠብቀው በፍትሐዊ ክፍፍል ላይ ለተመሠረተ የአገሮቻቸው ብሔራዊ ጥቅም ከመነጋገር በቀር የተለየ አቋም ይኖራቸዋል ተብሎ እንደማይጠበቅ ምንጮቹ ገልጸው፣ በዚህ ረገድ በቂ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እንደተሠራና የፓትርያርኩ የካይሮ ጉብኝትና የኹለቱ የሃይማኖት አባቶች ንግግር የሚጨምረው ምንም ዓዲስ ነገር አይኖርም የሚል እምነት በኢትዮጵያ መንግሥት በመያዙ ሳቢያ ጉብኝቱ መሰረዙን ለፋክት ተናግረዋል፡፡
እንደምንጮቹ ገለጻ÷ የግብፅ መንግሥት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ተጠቅሞ የውጭ ዲፕሎማሲው እንቅስቃሴ አካል ለማድረጉ የፖፕ አቡነ ታዎድሮስ ውትወታ የሚያሳይ ሲኾን፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ ጥረት እንደማይታይና ደካማ መኾኑን ተችተዋል፡፡
ይህም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፓትርያርኩ የዐደባባይ ንግግር ክህሎትና መስብሕነት ደካማነት* እንዲኹም እንደ ሕዳሴው ግድብ ባሉ ስሱ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸው የመደራደርና የማሳመን አቅም አስተማማኝ አለመኾን ጋራ ተያይዞ ከሚሰነዘርባቸው የከፋ ትችት ስጋት ጋራ በቀጥታ እንደሚያያዝ አስረድተዋል፡፡
ለሕዳሴው ግድብ የቅስቀሳ ኃይል ኾኖ ተቋቁሞ ወደ ግብፅ ለማምራት ተዘጋጅቶ በነበረው የሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ቡድን ውስጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ሓላፊዎች እንደሚገኙበት ያወሱ ሌሎች አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱን በውጭ ዲፕሎማሲው ሚና ነፍጓታል የሚለውን ትችት አይቀበሉትም፡፡
ይኹንና የፓትርያርኩ የግብፅ ጉብኝት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋራ ያላትን ግንኙነት የማስፋፋትና የማጠናከር፣ የፓትርያርኩንም የውጭ ጉብኝት የመፍቀድ የመጨረሻ ሥልጣን ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነና በዚኹም መሠረት ይኸው ጉብኝት ለመንግሥት ተገልጦ በቋሚ ሲኖዶሱ በኩል ዝግጅት ሲደረግበት እንደቆየ በመጥቀስ ጉብኝቱ በመንግሥት ውሳኔ ተከልክሏል መባሉ በታሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረግ ግልጽ ጣልቃ ገብነት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
‹‹እኛም በጉብኝቱ ልናስተላልፍ የሚገባውን የራሳችንን በጣም አስበንበት ነበር፤›› ያለው ሌላ ምንጭ፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (አስቀድሞ በተመረጡት በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ምትክ) በልኡክነት ለመጓዝ ተዘጋጅተው እንደነበር አስታውቋል፡፡ የጉብኝቱ መሰረዝ ከጸጥታ ጉዳዮችና ከፓትርያርኩ ደኅንነት ጋራ በተያያዘ ምክንያት ሊኾን እንደሚችል የጠቀሰው ምንጩ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የበዓለ ትንሣኤውን መልእክት ለብዙኃን መገናኛ ከሰጡበት ቀን ማግስት (ከኀሙስ ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ) እንደሚያውቁ ጠቅሷል፡፡
ይኹንና የኹለቱ ፓትርያርኮች ግንኙነት በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የሰሞኑ የቪ.ኦ.ኤ ቃለ ምልልስ እንደተመለከተው ‹‹ኹሉም ነገር ተስተካክሎ የተጋበዙበት›› በመኾኑና ከሕዳሴው ግድብ ውጭ በሃይማኖት አንድነት የመደጋገፍና የቆየውን ግንኙነት አጠናክሮ የመቀጠል ወቅታዊ ጉዳይ ያለበት እንደመኾኑ መጠን በመንግሥት ውሳኔ ተከልክሏል መባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ነጻነትና ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው ተብሏል፡፡
በዴሞክራሲው መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት እንደኾኑ የሚነገርላቸውን ሞሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ በተነሣው ቀውስ በግብፅ ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ላይ በደረሰው መከራና ጥፋት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የግብፁን አቻቸውን በወቅቱ በስልክ ውይይት አጽናንተው እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
************************
* ‹‹ቅባት ቀንሱ፤ ተልባ ጠጡ፤ አትክልት ብሉ፤›› በሚል የስቅለት ዓርብ ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅድስት ውስጥ ተቀምጠው ኢ.ቴቪ የቀረፀውንና በበዓለ ትንሣኤ የዜናው አካል አድርጎ ያስተላለፈው ‹ምክር› በበርካታ ምእመናንና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች ዘንድ ‹‹የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ደረጃ አይመጥንም፤ ቅዱስነታቸውንም አይመለከትም›› በሚል በስፋት መነጋገርያ ኾኗል፡፡
ቃለ አቀባይ በሚል በውል በማይታወቅ መዋቅር ሓላፊነት ተይዞ የፓትርያርካዊ ጉብኝቱን በሌለ ሰበብ መሰረዝ ለማስታወቅ የተጋውና ሚዲያዊ ጉዳዮች የሚመለከተው አካል በአጠቃላይ፣ ይህንና ይህን በመሳሰሉና ሌሎችም ጉዳዮች የፓትርያርኩ አስተያየቶች፣ ንግግሮችና መግለጫዎች በተገቢው ጉዳይ ላይ ደረጃቸውንና ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲሰጡ ማድረግ አይገባውምን?
