«የሃይለማሪያም ደሳለኝ ቁልቁለቶች» በሚል በተመስገን ደሳለኝ ከጻፈው የተወሰደ (ክፍል 2)
አቶ ኃይለማርያም በስድስት ወር (በጥር) ለተወካዮች ም/ቤት ማቅረብ የነበረበትን ሪፖርት በዘጠኝ ወሩ ባለፈው ሳምንት ባቀረበበት ወቅት፣ ከምርጫው በፊት የፖለቲካ ማሻሻያ መጠበቁ የዋህነት እንደሆነ የጠቆመን፣ የም/ቤቱ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የጠበበው ምህዳርን አስመልክቶ ላቀረበለት ጥያቄ ‹‹ዲሞክራሲ በአንድ ሳምንት ተበጥብጦ አይጠጣም (ፓርቲው ሥልጣን ከያዘ በቀጣዩ ወር ሃያ ሁለተኛ አመቱን መድፈኑን ልብ ይሏል)፣ ዲሞክራሲ ህልውናችን ነው፣ ቀይ ምንጣፍ አናነጥፍም…›› ጅኒ ቁልቋል በሚሉ የእብሪት ገለፃዎች ማለፉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሪፖርቱ በሀሰተኛና በማደናገሪያ ዘገባዎች የታጀለ እንደነበረ መታዘብ ተችሏል፡፡ ለማሳያነትም ያህል ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር እጠቅሳለሁ፡-
‹‹ዕድገት›› ሲባል…
የኢኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርቱ ላይ ‹‹የሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ሂደት ሲታይ ላለፉት አስር ዓመት (ከ1996-2005) በየዓመቱ በአማካይ 10.9 በመቶ በማደግ ከፍ ባለ የእድገት ጉዞ (Trajectory) ውስጥ መሆኑን አመላክቷል›› ሲል ነግሮናል፡፡ ይሁንና አስሩን ዓመት ትተን የዘንድሮውን በመሬት ላይ ያለውን እውነት እንኳ ብንመለከት የሚያሳየው ተቃራኒውን ስለመሆኑ ለራሱም ቢሆን ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በአገሪቱ ሥራ-አጥነት (በከተሞች 40 በመቶ መድረሱን ጥናቶች ይጠቁማሉ) በአስከፊ መልኩ ተንሰራፍቶ፣ ስደት ዕጣ-ፈንታ ተደርጎ ኩብለላ የዕለት ተግባር በሆነበት፣ ብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ በኑሮ ውድነት እንደ ከባድ ማዕበል ወደላይ ጎኖ፣ ቁልቁል በአናት እየተተከለ በሚንገላታበት፣ ጎዳናዎች ቀን ቀን ልመና በወጡ ምንዱባን፣ ማታ ማታ ደግሞ ነፍሳቸውን ለማቆየት የሚውተረተሩ በዕድሜም በአካልም ትናንሽ የሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች ተጥለቅልቆ… ባለበት በዚህ ዘመን ‹በየዓመቱ በአማካኝ 10 በመቶ እያደግን ነው› የሚልን አላጋጭ ሪፖርትን ሰምቶ በቸልታ ማለፉ ሰው የመሆን ጉዳይንም ፈተና ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡
በዚህ ለሶስት ወራት በዘገየው ሪፖርት የዋጋ ንረትን ከአንድ አሃዝ እንዳያልፍ እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ከየምርጫው አንድ ዓመት በፊት በመለስ ዜናዊ ይቀርቡ የነበሩ ሪፖርቶች እንዲህ አይነት የዋጋ ንረት እንደሚቀንስ የ‹‹ሚያበስሩ›› እንደነበር ይታወሳል፡፡ የኃይለማርያምም ሪፖርት፣ ፓርቲው በምርጫ ዘመቻው ወቅት ሁሌ እንደ ስልት የሚጠቀምበትን ይህንን ጉዳይ አስጩኾ ከተለመደው የግብይት ሥርዓት አፈንግጦ መጠነኛ የዋጋ ማረጋጊያ በማድረግ የእሳት ማጥፊያ ሥራ ለመስራት ከመዘጋጀት ያለፈ ትርጉም ያለው ነገር የሚያመጣ ሆኖ አይደለም፡፡
አብዮታዊ ግንባሩም ቢሆን የምርጫው ማዕበል የሚጠራርገውን ጠርጎ፣ የሚወረውረውን ወርውሮ ማለፉ ላይ እርግጠኛ እንደሆነው ሁሉ፣ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የዋጋ ንረቱ ተመልሶ የቱንም ያህል ወደላይ ቢስፈነጠር የተቆጡ ድምፆች አደባባዩን እንደማይሞሉት ጠንቅቆ ያውቀዋል።
ሌላው የሪፖርቱ አስቂኝ ክፍል የግብርናውን ዘርፍ የተመለከተው ነው፡፡ ይኸውም ካለፈው ዓመት የዘንድሮው በእጅጉ ማደጉን ገልፆ እንደምክንያት ያቀረበው ‹‹ዋናው የዕድገት መሰረት በመሬት ማስፋት ሳይሆን በምርታማነት የመጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው›› የሚል ነበር፡፡ ይሁንና እዚህ ጋ የሚነሳው ጥያቄ የዘርፉ ባለሙያ መሆንን የማይጠይቅ ቀላልና ግልፅ ነው፡- የግብርና ቴክኖሎጂ መሻሻል በሌለበት፣ የሰው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመጣበት (አማካይ የመሬት መጠን ከአንድ ሄክታር ያነሰ ሆኖ)፣ ማዳበሪያ ለፓርቲ አባላት ብቻ በሚታደልበት፣ የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቆ በሚዘራበት እና መሰል ችግሮች ባጨለሟት ኢትዮጵያችን ምርታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገ መባሉ እንዴት ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል? …መቼም በመለኮታዊ ኃይል ከሰማይ በወረደ መና ነው ሊሉን አይችሉም፡፡ ካሉ ግን ምን ማድረግ ይቻላል! ሰውየው ኃይለማርያም፣ ፓርቲውም ኢህአዴግ ነውና፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው የእነርሱ ዕድገት፣ ምርታማነት… ቅብርጥሶ የሚለው ፕሮፓጋንዳ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በምግብ እጦት መጠቃታቸውን ዓለም አቀፍ ተቋማት እየዘገቡ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደ መስከረም አደይ አበባ በየሜዳው መፍካቱን አብስረውናል፡፡ ይሁንና ሀገሪቱ እንኳን ለግዙፍ ፋብሪካዎች የሚሆን የኃይል አቅርቦት ቀርቶ፣ አነስተኛ ፍጆታ ያለውን የከተማ ነዋሪ የመብራት ፍላጎትም ማሟላት ያለመቻሏ ጉዳይ ፀሀይ የሞቀው፣ ዝናብ ያጨቀየው የአደባባይ እውነታ ነው፡፡ የግልገል ግቤ 3 ፕሮጀክትም ቢሆን፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደደሰኮረው በሚቀጥለው ዓመት ሥራ የሚጀመር አለመሆኑን ግንባታውን የሚያካሄደው ካምፓኒ አስቀድሞ ማሳወቁን ሰምተን አረጋግጠናል፡፡
ሌላው በሪፖርቱ ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ግርምት የሚያጭረው ከወራት በፊት በሳውዲ አረቢያ አሰቃቂ ጭካኔ የተፈፀመባቸውን ወንድም-እህቶችን በተመለከተ በአምስት መስመር ብቻ ተቀንብቦ የቀረበው ዘገባ ነው፡፡ የዚህን ሥርዓት ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከመራቅም በላይ፣ መበስበሱን የሚያስረግጠው እንዲያ በ21ኛ ክ/ዘመን ሊፈፀም ቀርቶ ይታሰባል ተብሎ በማይታመን ጭካኔ ደማቸው ደመ-ከልብ ሆኖ ስለቀረውና አስክሬናቸው በጎዳና ላይ ስለተጎተተው ወገኖቻችን፡- ‹‹የሳዑዲ መንግስት በተለያየ ምክንያት ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃዳቸውን ማስተካከል ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን አገር ለቀው እንዲወጡ በወሰነው መሰረት…›› በማለት በሪፖርት ተብየው አቃሎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሁለት ነገር ያመላክታል፡፡ የመጀመሪያው ሥርዓቱ ለዜጎቹ ደህንነት ደንታቢስ በመሆኑ ቢያንስ በወረቀት ላይ እንኳን ነውረኛውን የሳውዲ መንግስት ለማውገዝ እና ወደፊትም ከእንዲህ አይነቱ ዲያብሎሳዊ ተግባሩ እንዲታቀብ ለማስጠንቀቅ አለመድፈሩን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በዚህን መልኩ ከተባረሩ ስደተኞች መካከል አሁንም ወደዛው የሞት ቀጠና ተመልሰው መሄዳቸው፣ ጠ/ሚንስትሩ እንዲያ የተዘባነነበትን ‹‹ዕድገት›› ልብ-ወለድ ማድረጉን ነው፡፡