- ፓትርያርኩ ዛቻ ያሰሙበትን ድንገተኛ ስብሰባ ያስተባበሩት የፅልመታዊው ቡድን ቀንደኞች እነንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፡- ‹‹ቅዱስ አባታችን አይዞዎት፤ እኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ መድረክ ይፍጠሩ፤ እስከ መጨረሻው እንታገላለን›› በማለት አጋርነታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
- የቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት የፓትርያርኩ አካሔድ የምልዓተ ጉባኤውን ውሳኔ እንደሚጋፋ በመጥቀስ የተቃወማቸው ሲኾን የጠቅ/ቤተ ክህነቱ ዋ/ሥራ አስኪያጅም ለኹለት ዓመት የዘገየው የደንቡ ማሻሻያ ረቂቅ በመጪው ምልዓተ ጉባኤ ጸድቆ ማኅበሩ እንዲገለገልበት አሳስበዋል፡፡
- ፅልመታዊው ቡድን በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ፣ በማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ እና በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሕግ ረቂቆች ጉዳይ ከፓትርያርኩ ጋራ የዶለተውን ምክር÷ ሊቃነ ጳጳሳቱን በማስፈራራትና የቅዱስ ሲኖዶሱን ኁባሬ (አንድነት) ለአደጋ በሚያጋልጥ አኳኋን አቋማቸውን በመከፋፈል ጫና ለማስፈጸም ዐቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
- ‹‹ጵጵስና አሾማችኋለኹ›› በሚል ለሹመት ካሰፈሰፉ ቆሞሳት እጅ መንሻ እየተቀበለ የሚገኘው ፅልመታዊ ቡድኑ÷ አካሔዱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ሒደት ላይ የሚፈጥረውን ውጥረት በመጠቀምና ለውጥረቱ ማኅበሩንና አባላቱን ተጠያቂ በማድረግ በማኅበሩ አመራርና አባላት ላይ የታቀደውን ርምጃ ለማፋጠን መታሰቡ ተጠቁሟል፡፡
- ‹‹የሊቃነ ጳጳሳቱን ሥነ ልቡና ዐውቀዋለኹ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ የኢሕአዴግን ካድሬ ይፈራሉ፤ በራቸውን እያንኳኩ ማስፈራራት ነው፡፡›› /የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን ኹለተኛ ቢሯቸው በማድረግ ከሚኒስትሩ ጋራ ግንኙነታቸውን ያጠበቁት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ/
