- አስተዳደሩን ይሰበስባሉ፤ ሠራተኛ ያባርራሉ፤ ቢሮ ያሽጋሉ፤ ደመወዝ ይከለክላሉ
- መምህራኑን ለዓመታት ከኖሩባቸው የኮሌጁ ቤቶች ለቀው እንዲወጡ አዝዘዋል
- እስከ ነሐሴ ፴ መኖርያ ቤቶቹን የማይለቁ መምህራን ደመወዛቸው ይታገዳል
- ‹‹ለጥያቄዎቻችን ሥር ነቀል ምላሽ አላገኘንም፤ ይብሱኑ በቀልና ተደጋጋሚ በደል እየተፈጸመብን ነው›› ያሉት መምህራኑ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አቤት ብለዋል
- በጊዜያዊ ሓላፊነት የተመደቡት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ድምፃቸውን አጥፍተዋል
ቅዱስ ሲኖዶስ በሐምሌ ወር አጋማሽ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከሥልጣናቸው እንዲገለሉ የወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ በመጋፋት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደርን በጉልበት እየመሩ መኾናቸው ተገለጸ፡፡
የዜናው ምንጮች እንደገለጹት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመጪው ዓመት ጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም በሚያካሂደው አንደኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በኮሌጁ የበላይ ሓላፊነት ከያዙት ሥልጣናቸው ተገልለው እንዲቆዩ የተወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ÷ የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ በመተላለፍ የአስተዳደር ጉባኤውን ስብሰባዎች ይመራሉ፤ ለሠራተኞች ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ፡፡ ከሥራ ገበታቸው አላግባብ ያባረሯቸውና ደመወዛቸውን የከለከሏቸው ሠራተኞች፣ ቢሯቸውን ያሸጉባቸው ሓላፊዎችም አሉ፡፡
የኮሌጁ 11 መምህራንና ሠራተኞች የተፈራረሙበትና በዛሬው ዕለት ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንዳደረሱት የተሰማው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ደግሞ፣ መምህራኑና ሠራተኞቹ ለዓመታት የኖሩባቸውንና በኮሌጁ ቅጽር የሚገኙ ቤቶችን ቁልፍ ነሐሴ ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ድረስ እንዲያስረክቡ በቁጥር 1593/05/04/05 በቀን ፱/፲፪/፳፻፭ ዓ.ም በበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ቲተርና ፊርማ በወጣ ደብዳቤ ታዝዘዋል፡፡
የኮሌጁን ቤት እስከተጠቀሰው ቀን የማያስረክቡ መምህራንና ሠራተኞች ደግሞ የነሐሴ ወር ደመወዛቸው እንዳይከፈላቸው በቁጥር 1633/05/04/05 በቀን ፳፩/፲፪/፳፻፭ ዓ.ም ለኮሌጁ ፋይናንስ ክፍል በተጻፈ ደብዳቤ አዝዘዋል፡፡ ይህም ደብዳቤ የወጣው በበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቲተርና ፊርማ ነው፡፡
አቤቱታቸውን ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ካቀረቡት 11 መምህራንና ሠራተኞች መካከል የኮሌጁን ቤቶች ቁልፍ አስረክበው ቤቶቹን እንዲለቁ የተጠየቁት ስምንቱ ሲኾኑ የተገለጸላቸውም ምክንያት ‹‹አጠቃላይ የሕንፃ ጥገና ለማከናወን በቅድሚያ የመምህራንና የሠራተኛ መኖርያ ቤት ለዕድሳት አመቺ ለማድረግ›› የሚል መኾኑ ተመልክቷል፡፡
የሕንፃዎች ጥገናና እድሳት በየጊዜው እንደሚካሄድ የገለጹ መምህራንና ሠራተኞች በበኩላቸው፣ ከመንበረ ፓትርያሪኩ በሚሰጠው ልዩ ትእዛዝና ከሥራ ጠባዕያቸው አኳያ በአስተዳደር ጉባኤው እየተፈቀደ የኮሌጁ መኖርያ ቤት የተሰጣቸው መምህራንና ሠራተኞች በጋብቻ ምክንያት ካልኾነ በቀር በእድሳትና ጥገና ወቅት ‹‹ቤት ለቃችኹ ውጡ›› የተባሉበት አጋጣሚ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ ከእነርሱም መካከል ኮሌጁ በቀድሞው ሥርዐተ መንግሥት ተዘግቶ ቆይቶ ዳግመኛ ከተከፈተበት ከ፲፱፻፹፯ ዓ.ም ጀምሮ ለ18 ዓመታት ያህል በቤቶቹ የኖሩና ኮሌጁ ሙሉ እድሳት በሚያደርግበት ወቅት እንኳ የኮሌጁን የጥገና ወጪዎች እየተጋሩ የቆዩ የኮሌጁ አንጋፋ መምህራን እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡
‹‹ከላይ ጎርፉ ከታች ዶፉ በከበደበት፣ ቤት ለማግኘትም ለመከራየትም በሚያዳግትበት ክረምት ያለአንዳች የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ልቀቁ መባላችን የግፍ ግፍ እና የቤተ ክርስቲያናችንን የርኅራኄ አስተምህሮ የሚፃረር ነው፤›› በማለት ተቃውሟቸውን ያሰሙት መምህራኑና ሠራተኞቹ ከተባለው የሕንፃዎች ዕድሳት በኋላ እንኳ ለመመለስ ይችሉ እንደኾን በደብዳቤው አለመገለጹ አሳስቧቸዋል፡፡
በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ እና በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጆች ለመምህራንና ሠራተኞች መኖርያ ቤት በማመቻቸትና ለቤት ኪራይ አበል በጀት በመመደብ ከሚከተሉት አሠራር የተለየው የአሁኑ የኮሌጁ አስተዳደር ትእዛዝ፣ የኮሌጁ ሥራ አመራር ቦርድ ከቅጽረ ግቢው ለሚለቁ ቤት ለሌላቸው መምህራን የቤት ኪራይ አበል እንዲመደብ ከዚህ ቀደም ያስተላለፈውን ውሳኔ እንኳ ያላከበረ እንደኾነ አቤት ባዮቹ አስረድተዋል፡፡
የኮሌጁ 11 መምህራንና ሠራተኞች የተባበሩበትና የተቋሙ አጠቃላይ ችግሮች የተዘረዘሩበት አቤቱታ የሊቀ ጳጳሱ የቤት ልቀቁ ውሳኔና ትእዛዝ÷ አላግባብ የተላለፈና ቅን መነሻ እንደሌለው ይከራከራል፤ በምትኩ የአሁኑ የአስተዳደሩ ርምጃ ኮሌጁ ከደቀ መዛሙርቱ አካዳሚያና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ጋራ ተያይዞ በግለሰቦች ውሳኔ ሲከፈትና ሲዘጋ በቆየባቸው ባለፉት ሰባት ወራት የኮሌጁን አስተዳደራዊ በደል፣ ስጋትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለሚመለከታቸው የበላይ አካላት በተከታታይ ሲያሳውቁ በመቆየታቸው የተፈጸመባቸው በቀል ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ቤት እንዲለቁ ከታዘዙት መምህራንና ሠራተኞች መካከል ለመንፈቅ የዘለቀውን የደቀ መዛሙርት የተቃውሞ እንቅስቃሴ አነሣስተዋል በሚል በጡረታ ለማግለል የተዛተባቸው የሐዲስ ኪዳን መምህሩ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሳ፣ ወደ ሌሎች ኮሌጆች እንዲዘዋወሩ ከታቀደባቸው መካከል የኤቲክስ መምህሩ ተሾመ ገብረ ሚካኤል ይገኙባቸዋል፡፡
በደቀ መዛሙርት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት ውዝግቡን ለማጣራት ከተቋቋመው ጥምር ኮሚቴ ጀምሮ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሚያዝያ ፪/፳፻፭ ዓ.ም፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሰኔ ፳፬/፳፻፭ ዓ.ም፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሐምሌ ፲ እና ፳፱/፳፻፭ ዓ.ም መምህራኑና ሠራተኞቹ በሰጧቸው ማብራሪያዎች÷ በዕርግናና ጤና ማጣት ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ አንጋፋውን መንፈሳዊ ኮሌጅ የመምራት አካላዊ ችሎታቸው የተዳከመው አቡነ ጢሞቴዎስ ኮሌጁን ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እየመሩት መኾኑን በተደጋጋሚ አስታውቀው ነበር፡፡
የዓመቱ ምሩቃን ከተሸኙና የተቀሩትም ፈተናቸውን ጨርሰው መውጣታቸውን ተከትሎ ከሥልጣናቸው ተገልለው እንዲቆዩ የተወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ለመምህራኑና ሠራተኞች አላግባብ ያስተላለፉት ‹የቤት ልቀቁ› ትእዛዝ እና ‹የደመወዝ እከልክላለኹ› ዛቻ ሊቀ ጳጳሱ የሚታወቁበትን እልከኝነት/ማን አኽሎኝነት ብቻ ሳይኾን የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ እንደሌሎች ውሳኔዎች ሁሉ ያለበትን ሥር የሰደደ የማስፈጸም ችግርም አመልካች ነው፡፡
እስከ ቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ከተቀሩት ሓላፊዎችና ሠራተኞች ጋራ በመተባበር ኮሌጁን በጊዜያዊ ሓላፊነት እንዲመሩ የተሠየሙት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃም እንኳ ከምረቃውና ከመንፈቅ ዓመቱ የመደበኛ መርሐ ግብር ፈተናዎች መጠናቀቅ በኋላ ዳናቸው ከቅጽረ ግቢው ጠፍቷል፡፡ ከሓላፊነቱ ተነሥቶ ከኮሌጁ እንዲወገድ፣ ስለ ሃይማኖቱ ሕጸጽም እንዲጠየቅ የተወሰነበት ዘላለም ረድኤትም መውጣትና መግባቱን አላቋረጠም፡፡
መምህራኑና ሠራተኞቹ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት ማመልከቻ፣ ረኀብን ጨምሮ ለበርካታ ጫናዎች ሳይበገሩ ውጤት ያስመዘገቡትን ጽኑዐን ደቀ መዛሙርት አቋም የሚጋራ ነው – መፍትሔው፡- ቅ/ሲኖዶሱ የሚወስደው ሥር ነቀል ርምጃ ነው!! የሥር ነቀል ርምጃው ዋነኛ ተግባር፣ አካላዊ ችሎታቸው የተዳከመውን አስተዳደራቸው የተበላሸውን ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስን ከሥልጣን ማንሣት ነው፡፡
የዚህ ሥር ነቀል ርምጃ ዋነኛ ተግባር ቁልፍ ገጽታው ደግሞ ተፈላጊውን ትውልድ በሚተካው አንጋፋ የትምህርትና ምርምር ተቋም ውስጥ ጎጠኝነትንና ሙሰኝነትን እኒህም እርስ በርስ በመመጋገብ የሚፈጥሩለትን ምቹ ኹኔታ የሚበዘብዘውን ኑፋቄን ማስወገድ ነው፡፡ መተኪያውም ‹‹ዘርን፣ ጎሳን፣ ቀለምን የማይለይ፤ ዕውቀትን፣ የመምራት ጥበብን፣ መንፈሳዊነትን፣ ርኅራኄን፣ ሥነ ምግባርንና ፍቅርን የተላበሰ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ነው፡፡›› ይገኝ ይኾን? ከዛሬ ነሐሴ ፳፪/፳፻፭ ዓ.ም ሥራውን ከሚጀምረውና እስከ ቀጣዩ ዓመት ጥቅምት/፳፻፮ ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክን፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስንና ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በተለዋጭ አባልነት ይዞ ከሚቆየው ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ብዙ ይጠበቃል፡፡
