- በዓሉን የአካባቢው ተጨማሪ የቱሪስት መስሕብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው
- መንፈሳዊ ይዘቱ እንዲጠፋ የሚሹ ግለሰቦች በበዓል ኮሚቴ መካተታቸው ቅር አሰኝቷል
- በበዓሉ አጋጣሚ ለቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳደራዊ ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል
የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ፍጻሜ ተከትሎ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል ከነገ ጀምሮ የዓለም አቀፍ ብርቅዬ ቅርስ ማእከልና የውብ ባህል መድረክ በኾነው ላሊበላ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ ደብርን ጨምሮ የወረዳ ቤተ ክህነቱን በበላይነት በሚመራው የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳደር ካህናት የሚሳተፉበት ያሬዳዊ ዝማሬና ቅኔ የበዓል ዝግጅቱ አካል ሲኾን የበዓሉ መክፈቻ ሥነ ሥርዐት በሚካሄድበት ነሐሴ ፲፮ ቀን ምሽት የላስታ – ላልይበላ ሕዝባዊ ባህል የኾነው የአሸንድዬ ልዩ ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም ይቀርቡበታል፡፡
በዓሉን መሠረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሞያዎች ቀርበው የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ለበዓሉ አከባበር ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከነሐሴ ፲፭ – ፲፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በሚቆየው ክብረ በዓል ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 200 ያህል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡
ከዓመት ወደ ዓመት ለበዓሉ አከባበርና ክብረ በዓሉ ለሚያስገኘው ፋይዳ የሚሰጠው ትኩረት የሚመሰገን ነው ያሉ አስተያየት ሰጭዎች ውስጥ በዓሉን ከሃይማኖታዊ መሠረቱ አሰናብቶ ዓለማዊ ገጽታ ብቻ ለማላበስ በማሤር የሚታወቁ በእምነታቸው ልዩ የኾኑ አንዳንድ ግለሰቦች በበዓል አከባበር ኮሚቴ ውስጥ መካተታቸው ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸዋል፡፡ በዓሉ ባህላዊና መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ ተጨማሪ የቱሪስት መስሕብ እንዲኾንና የባህል ገጽታ ግንባታን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በከተማው አስተዳደርና በክልሉ መንግሥት ትኩረት በተሰጠበት ኹኔታ በእንዲህ ዐይነቱ ተንኮል የተለከፉ ግለሰቦች ሊነቃባቸውና ሊጋለጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አስተያየት ሰጭዎቹ አክለውም በሁሉም ገጽታው ጠንካራ ሃይማኖታዊ መሠረት ባለው የአሸንድዬ ክብረ በዓል አጋጣሚ የዞኑ አስተዳደር የልማት ጉብኝቶችንና ሌሎች አገራዊ አጀንዳዎችን ማካተቱ በራሱ ባይነቀፍም፣ በከፍተኛ የቱሪስት መስሕብነቱና በእምነት ማእከልነቱ ለከተማው ህልውናና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሚና ለሚጫወተው የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳደር መቃናትም ትኩረት እንዲሰጠው አመልክተዋል፡፡
የደብሩ አብያተ መቅደስ የሕዝብ ሀብትና የዓለም ቅርስ መኾናቸውን በማስታወስ የሚገኙበት ኹኔታ አሳሳቢና ጊዜ የሚሰጠው እንዳልኾነ ያስረዱት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ የክብረ በዓሉ አጋጣሚ የደብሩ አስተዳደር ከሙሰኛና ዐምባገነን አሠራር ነጻነቱን አግኝቶ በሕግ እንዲመራ፣ ቅርሱ እንዲጠበቅና በገቢው መጠን የበለጠ እንዲለማ የሚያስችል ተጨባጭ ርምጃ እንዲወሰድ ግፊት የሚደረግበት እንዲኾን ጠይቀዋል፡፡
ላለፉት ስምንት ዓመታት የደብሩንና የወረዳ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር ደርበው የያዙት መ/ር ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን ሐሰተኛ ሰነድ በመፍጠርና ኾን ብሎ ቅርስን በማፍረስ ወንጀል ተጠርጥረው የተጠርጣሪነት ቃላቸውን እንዲሰጡ የሚፈለጉ ቢኾንም በፈቃድ ዕረፍት ሰበብ በአዲስ አበባ ተቀምጠው እንደለመዱት አንዳንድ ድሉል የፍትሕ አካላትን ለማማሰን እየማሰኑ መኾናቸው ተጠቁሟል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ማለትም በትግራይ፣ ዋግና ላስታ ከሚከናወኑ በርካታ ሃይማኖታዊ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል እንደ እሽውላሌ፣ ጊጤ፣ ገና ጨዋታ፣ አሸንድዬ፣ ሙሻሙሾ እና ሆያ ሆዬ የመሳሰሉት በዐበይትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በነሐሴ ወር አጋማሽ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዐለ ዕርገት/ፍልሰታ/ ጾም ፍች ጋራ ተያይዞ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል ማራኪና ልዩ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡
በቀድሞዋ ሮሃ በኋላ ላሊበላ የሚከበረው በዓሉ÷ በላስታ አሸንድዬ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በዋግ ሻደይ፣ በራያ ቆቦ ስለል በይ በመባል ተቀራራቢነት ባላቸው ስያሜዎች ይጠራል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት ልጃገረዶች ከወገባቸው ላይ ሣር መሰል ቅጠል በማሰር ከቤት ቤት በመዘዋወር የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት የሚጫወቱት ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ዘንድሮም ከላሊበላ በተጨማሪ በላስታ እና በመቐለ በደማቅ ኹኔታ ይከበራል፡፡
በላሊበላና አካባቢው የቱሪስት ፍሰቱ ከፍተኛ የሚኾነው በታኅሣሥና ጥር ወር ሲኾን ይህም በአብያተ መቅደሱ (በቋሚ ቅርሱ) የሚከበሩ በዓላትን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርስ የኾነው የአሸንድዬ በዓል በአግባቡ ታቅዶና ተደራጅቶ ለቱሪስቶች ቢተዋወቅ ደግሞ በነሐሴና በመስከረም ወር የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመርና የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የቱሪስቶችን ቆይታ ያራዝማል፡፡ ይህም እንደ ቻይና የውኃ በዓል፣ እንደ ስፔን የበሬ ውጊ፣ እንደ ብራዚልና አርጀንቲና የጎዳና በዓል ለመልካም ገጽታ ግንባታ ሊውል፣ ኢንቨስትመንትን ሊያስፋፋና የሥራ ዕድል ሊጨምር ይችላል፡፡
* * *
የፍልሰታ ጾምና በዓል ከአሸንድዬ ላስታ – ላልይበላ ባህላዊ ክንዋኔ ጋራ ያለው መስተጋብር
በኢትዮጵያ ከፍ ብሎ የሚታየው በብዛት ልጆች ተሳትፎ የሚያደርጉበት የፍልሰታ ጾምና በዓል ነው፡፡ ፍልሰታ የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ ኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረተ ቃሉ÷ ‹‹ተነሥአ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትኽ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስኽ ታቦት፡፡›› /መዝ.፻፴፩÷፰/፡፡ ‹‹ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኮኵሕ ቅሩበ ጥቅም፤ አቅራቢያዬ መልካማ ርግቤ ተነሽ ነዪ በግንብ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው ጥላ፡፡›› /መኃ. ፪÷ ፲ – ፲፬/ የሚለው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ጽሑፍ ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፤ በወርቀ ዘቦ ልብስ ተሸልማለች፤ በኋላዋም ለንጉሡ ደናግልን ይወስዳሉ፤ ባልንጀሮችዋንም ይወስዱልሃል፡፡ በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በዕቅፋቸው፣ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ያመጡልሻል፤›› ተብሎ በተነገረው የነብያት ቃል መሠረት ልጆችም፣ ወላጆችም በመተባበር የእመቤታችንን የፍልሰታ ጾምና በዓል ሲጠብቁ ይኖራሉ፡፡
ከቀደሙት ሰዎች ታሪክ ከእስራኤል መሳፍንት አንዱ ለኾነው የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ በዓል ሲያከብሩ እንደ ነበረ ተናግሯል፡፡ /መጽ. መሳ.፲፩÷፵/፡፡ እንዲህ ከኾነ ዘንድ ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ሕፃናት፣ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች የእናታችንን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ በየዓመቱ ሲያከብሩ የበለጠ ነገር ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡
የጾመ ፍልሰታን መታሰቢያ ለመፈጸም ልጆችም ወላጆችም ይተባበራሉ፤ ጾሙ በፍትሐ ነገሥት በአንቀጽ ፲፭ ከተዘረዘሩት አጽዋም አንዱ ነው፡፡ ጾሙ ከፍቅር ጋራ የሚፈጸም ስለኾነ ልጆችም ወላጆችም የሚጾሙት በጉጉት ነው፡፡ ወላጆች ከባድ ምክንያት ካላጋጠማቸው በስተቀር ከአልጋ ወርደው፣ ከመሬት ላይ ተኝተው ወይም ከቤታቸው በቤተ እግዚአብሔር ዙሪያ ማረፊያ አሰናድተው ከነሐሴ ፩ – ፲፭ ድረስ ጥሬ በመብላት፣ ውኃ በመጠጣት፣ ሌሊት በሰዓታት፣ ቀን በጸሎት ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም በመስማት፣ በምጽዋት፣ ቅዳሴ በማስቀደስ በከፍተኛ ሥነ ሥርዐት ይጾሙታል፡፡
ልጆችም በረኀብ ሳይሰማቸው፣ ውኃ ጥም ሳያሸንፋቸው ከ፯ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ሕፃናት እየጾሙ ይቆርባሉ፡፡ በመጨረሻ ነሐሴ ፲፮ ቀን ወላጆች በዓሉን በሥነ ሥርዐት ሲያከብሩ ልጆችም በልዩ ሥነ ሥርዐት ያከብሩታል፡፡
የረጅም ዘመን ታሪክ ባለጸጋ በኾነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ የሚከበሩ በዓላት ጥንታዊነቷን፣ ታሪካዊነቷን፣ የነባር ሥልጣኔ ባለቤትነቷን ከሚገልጹ ቅርሶቿ መካከል ይመደባሉ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ኢትዮጵያ በውስጧ አቅፋ ከያዘቻቸው የሃይማኖት፣ የታሪክና የመካነ ቅርስ ማእከላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹መላእክት በልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርደው በላሊበላ ይዘምራሉ›› ከተባለለት የቤዛ ኲሉ ክብረ በዓል ጀምሮ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ሞቅና ደመቅ ብለው ይከበሩበታል፡፡ ዘመናትን አቆራርጦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ከጊዜያችን የደረሰውና በፍልሰታ ለማርያም ጾም ፍጻሜ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል አንዱ ነው፡፡
* * *
የአሸንድዬ ባህላዊ ጨዋታ መገለጫ የኾነው አሸንዳ እንደ ቄጤማ ረጅምና እንደ ቅጠል ሰፋ ያለ ነው፡፡ ቁመቱ ከ80 – 90 ሣ.ሜ ይኾናል፡፡ ለምለም ነው፡፡ በወገብ እንደ ሽብሽቦ ኾኖ ይታሰርና ከግጥሙና ከዜማው ጋራ ተዋሕዶ በዳሌያቸው ላይ ይዞራል፤ ይሽከረከራል፡፡ በተለይ፡-
እቴ አይዞርም ወገብሽ
ባቄላን ነው ቀለብሽ
እያለች የበለጠ ወገባቸው እንዲዞር በግጥምና በዜማ አውጭዋ ስታዜም ተቀባዮቹ ደግሞ አባባሉን ለማስተባበል በኃይልና በዘዴ ወገባቸውን ሲያዞሩ ቅጠሉ ርግፍ እያለ ከወገባቸው ጋራ ይሽከረከራል፡፡
አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
እሽርግፍ እንደወለባ
ሲሉና ሲዞሩም አብሮ በኃይል ይዞራል፤ ከወገባቸው ላይ ርግፍ ይልና ዞሮ ተመልሶ ያርፋል፡፡ አሸንድዬ በተለያዩ የሰውነት አካላት (በአንገት፣ በትክሻ፣ በወገብ፣ በእጅ፣ በእግር ወዘተ) እንቅስቃሴ ይከወናል፡፡![Ashenda Shadey02]()
አንዳንድ ምሁራን አሸንድዬ ገና ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የክረምቱን (ጨለማው፣ ጭቃው፣ ጎርፉ፣ ዶፉ፣ ብርዱ) መውጣትና የበጋውን (ብርሃኑ፣ ፀሐዩ፣ የወንዙ ጥራት፣ የአዝዕርቱ ማሸት፣ የአበባው ማበብ) መግባት ምክንያት በማድረግ ደናግል (አዋልድ) ቅድመ ዕንቊጣጣሽ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ አዲሱን ዘመን በደስታና በሐሤት ለመቀበል በብሩህ ተስፋ ውስጥ ኾነው ይጫወቱት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ እውነትም፡-
አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
እሽርግፍ እንደወለባ
አደይ አበባ አደይ አበባ
ነሽ ውባ ውባ
አደይቱ፣ መስከረሚቱ
መውደድ እንደሌሊቱ
እያሉ አበባንና መስከረምን ሲያነሡና ሲያወድሱ፣ የታጠቁትንም ቅጠል ሲያወሱ እውነትም ከአዲሱ ዘመንና ከዕንቊጣጣሽ በዓል ጋራ ግንኙነት እንደነበረው ያሳያል፡፡
አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋራ ያይዙታል፡፡ ከሕግ ባለቤት ከልዑል እግዚአብሔር ሕግን ተቀብሎ ያስተላለፈው ሙሴ እስራኤላውያን በግብጽ በባርነት በነበሩበት ጊዜ ዕብራዊት እናቱ በዚያ ስለወለደችውና ማንኛውም ወንድ ዕብራዊ ሲወለድ እንዲገደል በግብጽ ዐዋጅ መውጣቱ እናቱ እግዚአብሔር እንዳደረገ ያድርገው ብላ ከዐባይ ወንዝ ዳርቻ በቄጤማ ውስጥ አስቀምጣዋለች፡፡ ኋላ የፈርዖን ልጅ ገላዋን ልትታጠብ ወደ ወንዝ (ዐባይ) ስትሄድ ደንገጡሯን ልካ አውጥታ በእናቱ ሞግዚትነት አሳድጋው እስራኤልን ከተገዙበት የ430 ዓመት ባርነት ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡
ይህን መሠረት በማድረግ፡-
አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ
ፍስስ በይ በቀሚሴ
የሚለው ባህላዊ ጨዋታ መነሻው ልጃገረዶች በጀርባቸው አሰውረው ከሚወዘውዙት ቄጤማ መሰል ሣር ስያሜ የመጣ ሲኾን ይህ ሣር(ቅጠል) ሙሴ የተጣለበትን ቄጤማ ስያሜ ወስዶ አሸንዳ ሙሴ ተብሎ ይጠራል፤ አበ ሙሴ፣ ወርቃበ ሙሴ እያሉ ደጋግመው ማንሣታቸው ለዚህ ማስረጃ ነው ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል የአሸንድዬን ባህላዊ ጨዋታ ከመጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድያዳ ልጅ ዘፈን (የሄሮድስ ልደት ዕለት) ምክንያት አንገት መቆረጥና ከአዲስ ዓመት ብሥራት ጋራ ያያይዙታል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ በዓሉም መስከረም ፩ እና ፪ በየዓመቱ ይከበራል፡፡ መስከረም ፪ ምትረተ ርእሱ ተብሎ በቅዱስ ላሊበላ በቤተ ማርያም በጋለ ስሜት በማሕሌት በውዳሴና በቅዳሴ ይከበራል፡፡
ከዚሁ ጋራ በተያያዘ የአሸንድዬ ቅጠል ሔዋን ዕፀ በለስን በልታ ራቁቷን በኾነች ጊዜ ያገለደመችውን ቅጠል ሲያስታውስ፣ አረንጓዴ (ሐምራዊ) መኾኑም የድንግል ማርያምን ልብስ ያስታውሳል፤ በየሥዕለ ማርያሙ እንደምንመለከተው ልብሰ ቅድስት ድንግል ማርያም ሐምራዊ መልክ አለውና፡፡ አንድም ቅጠሉ ለምለም ነው፡፡ የዐዲሱ ዓመት በልምላሜ መምጣት የሚበሠርበት ነው፡፡
አሸንድዬው የሚታሰረውና የሚያርፈው በጀርባቸው እንጅ በፊታቸው አይደለም፤ ጀርባቸውን እንጂ የፊታቸውን አካል አይሸፍንም፡፡ የሰው ልጅ ጸጋው በበደል ቢገፈፍም መሐሪው እግዚአብሔር ፈጽሞ ሳይተወው ኋላ ከድንግል ተወልዶ የተገፈፈውን ጸጋ ልብስ እንደሚመልስላቸው ተስፋ የገባላቸው መኾኑን ያዘክራል፡፡
ይኹን እንጂ አሁን እየጎላ የመጣውና ዋና በዓል የኾነው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰት ጋራ እየተያያዘ የመጣው የአከባበር ሥነ ሥርዐት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ይከበሩ የነበሩ በዓላትና ሥርዐታት በሐዲስ ኪዳን ዘመን ሥርዐታቸውና ትርጉማቸው ተጣጥሞ መዘዋወራቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የአሸንድዬ ቅጠል ለጨዋታ የሚታሰረው በጒንጒን ታስሮ ተጠላልፎ ነው፡፡ ይህም መላእክት እመቤታችንን ክንፍ ለክንፍ ገጥመው ተያይዘው ማሳረጋቸውን ያጠይቃል፡፡![Ashenda Shadey01]()
ይኸውም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ‹‹አሸንዳ›› የሚባለው ሣር ዐይነት ቅጠል ኹኔታው ቀጭን ቢኾንም ቁመቱ ረዘም ያለ ኾኖ ቅርጹ ፊላ ዐይነት ነው፤ ሲነቅሉት ሥሩ ነጭ ነው፤ ዛጎል ይመስላል፡፡ ልጃገረዶች በልዩ አሠራር ሠርተው በቀሚሳቸው ላይ ይታጠቁታል፤ እንደ ዘርፍ ኾኖ ወደታች ይወርዳል፤ በሚጫወቱበትና በሚዘፍኑበት ጊዜ ዙሪያውን ሲነሣ ክንፍ ይመስላል፡፡ በዚህ ዐይነት ሥርዐት በዓሉን ሲያከብሩ ይውላሉ፤ በተለይ በገጠር ላሉ ሴቶች ሕፃናት ቆነጃጅት ልዩ በዓላቸው ነው፡፡
አሸንዳ ከሚባለው ሣር ዐይነት ቅጠል በልዩ ዐይነት አሠራር ሠርተው የሚታጠቁትና ሲጫወቱ፣ ሲዘፍኑ ዙሪያውን የመነሣቱ ኹኔታም መላእክት እመቤታችን ክንፍ ለክንፍ ገጥመው እያመሰገኑ ማሳረጋቸውን ያሳስባል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕራፍ ፮ ላይ ባየው ራእይ ሱራፊ መልአክ በሁለት ክንፍ ፊቱን፣ በሁለት ክንፍ እግሩን ሲሸፍን፣ ሁለት ክንፉን በግራ በቀኝ ዘርግቶ ረብቦ ይታያል የሚለውን ያመለክታል፡፡ በዓሉንም የአሸንድዬ በዓል ይሉታል፡፡
በእውነት፣ ‹‹ደናግልን ለንጉሥ በኋላዋ ይወስዳሉ፤›› ሲል በቅዱስ ዳዊት የተነገረው ቃል ልጆች በእመቤታችን ፍቅር እየተኮተኮቱ አድገው ለእግዚአብሔር ቤተሰብ መኾናቸውን ያሳያል፡፡ በዚህ ሥርዐት ያደጉ ልጆችን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ከእመቤታችን ፍቅር የሚለያቸው የለም፡፡
* * *
የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት
የአሸንድዬ ባህላዊ ጨዋታ ወቅት ክረምቱ አልፎ በጋው የሚደርስበት ነው፡፡ ‹‹ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ ብሩህ ሰማይ ሊታይ፣ አበባ በምድር ሊገለጥ፣ ፀሐይ ብርሃንዋን ልትሰጥ፣ ከዋክብት እንደፈርጥ ሊንቦገቦጉ፣ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዳለው ክረምቱ ሊያልፍ፣ የቁርየው ቃል በምድራችን ሊሰማ፣ በለሱ ሊጎመራ፣ ወይኖች ሊያብቡ፣ መዓዛቸውንም ሊሰጡ የሚቃረብበት ወቅት ነውና በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በተለይም በልጃገረዶች ደስታን ያጭራል፡፡
ቅድመ ዝግጅቱ የሚጀመረውም የፍልሰታ ጾም ሲገባ ጀምሮ ነው፡፡ ነጫጭ ልብሱን ለብሶ ከማስቀደሱና ከመቁረቡ በተጨማሪ በዚሁ ሰሞን ለአሸንድዬ በዓል አከባበር የሚኾኑ ባህላዊ አልባሳት ማለት ትፍትፍና ጥልፍ ቀሚስ፣ መቀነት፣ ልዩ ልዩ ጌጣ ጌጥ ለምሳሌ፡- ያንገት መስቀል፣ የጆሮ ጉትቻ፣ የእጅ ድኮት፣ የእግር አልቦ፣ ድሪ ካሎስ (ማተብ) አምባር፣ ጉርሽጥ (እንሶስላ) ማሰባሰብና ማዘጋጀት፣ ልብስ ማጠብ፣ ፀጉር መሠራት. . .ወዘተ ከቅድመ ዝግጅት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በዓሉ ሲደርስ አለቃ ይመርጣሉ፤ አለቃዋ በመልካም ባሕርይዋ የተመሰገነች፣ የመምራትና የማስተባበር ችሎታ ያላት፣ በአካልና በዕድሜ ላቅ ያለች፣ የታወቀችና ልምድንም ያካበተች መኾን ይኖርባታል፡፡ ገንዘብ ያዥም ይመርጣሉ፤ የታመነች፣ ገንዘቡን በጥንቃቄ ይዛ ለተፈለገው የምታውል መኾን ይጠበቅባታል፡፡ አውጭም ታስፈልጋለች፤ እንደ አቀንቃኝ ማለት ናት፡፡ ምንም እንኳ የድምፅና የግጥም ተሰጥዖ ያላቸው በብዛት ሊኖሩና አንዷ ሲደክማት ሌላዋ እየተተካች ማስኬዱን ቢያውቁበትም የበለጠ ችሎታ ያላቸው ይመደባሉ፡፡
በበዓሉ ዋዜማ ነሐሴ ፲፭ ወደ ዱር በመሄድ ከወንዝ ዳር የሚበቅለውንና አሸንድዬ የተባለውን ለባህላዊ ጨዋታው አመች የኾነውን ረጅም ቄጤማ መሰል ለምለም ሣር (ቅጠል) ቆርጠው ያመጣሉ፡፡ በዕለተ በዓሉ (ነሐሴ ፲፮) ማለድ ብለው ተነሥተው ይተጣጠባሉ፤ ይወላወላሉ፡፡ አምረው ተውበው፣ ለብሰው አጊጠው፣ በነጫጭ ባህላዊ ልብሳቸው ላይ አሸንድያቸውን በጀርባቸው ታጥቀው ብቅ ይላሉ፡፡ አጊያጊያጣችንንና አዋዋባችንን፣ አለባበሳችንንና አጨዋወታችንን በጠቅላላው የአኩሪ ባህል ባለቤትነታችንን ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡
ነሐሴ ፲፮ ልጃገረዶች በየአጥቢያቸው በቡድን ይሰባሰቡና በመጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ እየዞሩ በመዘመር እዚህ ላደረሳቸው አምላክም ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ ዝማሬያቸውም እንደሚሄዱበት ቤተ ክርስቲያን ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ መድኃኔዓለም ከኾነ፡-
እስከ በስመ አብ ብዬ ልጀምር ሰላምታ
ለመድኃኔዓለም ለአዳኙ ጌታ
ዐይነት ሊኾን ይችላል፡፡ የብልባላ ጊዮርጊስ አሸንድዬ ባዮች ጥንታዊውን ውቅር ቤተ መቅደስ እየዞሩ፡-
ቤተ ክርስቲያኑን ሁሉ ዐየነው በሰፊው
ብልባላ ጊዮርጊስ በልክ የተሠራው
በድንጋይ ላይ ድንጋይ ከዚያም በላይ ቤት
ብልባላ ጊዮርጊስ ትልቁ ታቦት
ይላሉ፡፡ በላሊበላ አሁንም፡-
አሸበረቀች ጨረቃ ተወረወረች ኮከብ
በጊዮርጊስ ጫንቃ በዐማኑኤል ክበብ
በሚካኤል ጫንቃ በገብርኤል ክበብ
በእመብርሃን ጫንቃ በሊባኖስ ክበብ
እያሉ ይዘምራሉ፡፡ በጣም የሚወዱትንና የበዓሉና የደስታቸው መግለጫ ከኾነው አሸንዳም በየቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ላይ ያስራሉ፤ ይጥላሉ፤ ይጎዘጉዛሉ፡፡
ከቤተ ክርስቲያን መልስም በቆየው ዘመን መጀመሪያ ታላላቅ ከሚባሉና ከሹመኞች ቤት በመሄድ የደስታ መግለጫቸውን ያሰማሉ፡፡ ከዚያ ወደ ሌላው ሰው ቤት ያመራሉ፡፡ ሁሉንም በስድስቱ ቀናት ውስጥ ያደርሳሉ፤ እስከ ዕንቊጣጣሽ ድረስም የሚቆዩ አሉ፡፡ ሀብታም ነው፤ ድኻ ነው ብለው የሚተዉት ሰው አይኖርም፡፡ የመንገድ (የጉዞ) ዜማም አላቸው፤ አጀባዬ ይባላል፡፡
አጀባ ኾኗል ጅብጀባ አጀባ ኾኗል ፈረሱ
በየት ልንገባ ወዴት ነው እሱ
እያሉ በመቀባበል ካዜሙና ዜማውን ተከትለው ርግፍ ርግፍ እያሉ ወደላይም እየዘለሉ ከጨፈሩ በኋላ ካባወራው ወይም እማወራውጋ ሲደርሱ ከግቢው ውጭ ኾነው፡-
አስገባኝ በረኛ
አስገባኝ ከልካይ
እመቤቴን ላይ
ጌታው አሉ ወይ አሉ ወይ
አሉ እንጂ ግቡ ይላሉ እንጂ
አሉ እንጂ፣ ተዘንብሏል ጠጂ
እያሉ በጨዋ መልክ አወድሰውና አስፈቅደው በር ካስከፈቱ በኋላ ወደ ግቢው ይገባሉ፡፡ ከዚያም በጥዑም ዜማ በሠናይ ቃና ይጫወታሉ፡፡ የጨዋታቸው ስንኞች ፍቅርን፣ ጀግንነትን፣ የሥራ ክቡርነትን፣ ሞያን፣ ውበትን. . .ወዘተ የሚያወድሱበት፣ በተለያየ ጣዕመ ዝማሬ የሚያሸበሽቡበት ነው፡፡ ባለቤቱ ሞቅ ያለ ስጦታ እንዲያበረክትላቸው ሲገፋፉትም፡-
ጌታው ስም ይሻል፤ ስም ይሻል
አንድ ብር እንኳ ጠፍቶ ያመሻል
በሬ ከጋጡ ሞቶ ያመሻል
እያሉ አመስግነው፣ ተመስግነው፣ ተሸልመው ከቤት ይወጣሉ፤ ወደ ሌላ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ሽልማቱ ቀደም ሲል እህል፣ ዳቦ፣ ጠላ፣ እንጀራ፣ በግ፣ ፍየል፣ እርጎ ነበር፤ ይህ አሁንም በገጠሩ ይኖራል፡፡ በከተማው ግን እንየዐቅሙ በብር ነው፡፡ ምርቃቱንም ቢኾን እንደቀላል ነገር አይቆጥሩትም፡፡ እንደዚሁ እያሉ ቀኑን ያገባድዱና ወደማታው ወደ ሜዳ ይወጣሉ፡፡ በየቡድናቸው ተሰባስበው በተለይ አዲ ሻዶች ከላይ ሰባት ወይሮች ከታች ይኾኑና በግጥምና በግጥምና በዜማ ሲተቻቹ አምሽተው እንደተነፋፈቁ ቀኑ መሽቶ ጨለማው ይገላግላቸዋል፡፡ በዚህ ዐይነት ሰንብተው በዓሉ ነሐሴ ፳፩ ቀን ያበቃል፡፡ በመስቀል ከሆያ ሆዬ ባዮች ጋራ ደግሰው የሰጧቸውን ሰዎች አብልተው አጠጥተው ተጫውተው ተፍጻሚተ በዓል ይኾናል፡፡
በአጠቃላይ ዓመታዊው የአሸንድዬ ክብረ በዓል በትግራይ፣ በዋግና በላስታ በደመቀ ኹኔታ ይከበራል፡፡ የቅርብ ቤተ ዘመድና አንድ ናቸው፤ በጊዜ ብዛትና በቦታ መራራቅ የተነሣ በቋንቋና በአንዳንድ ባህላዊ ልዩነት ቢኖረውም፡፡ ዋናው ነገር ሲኒማው፣ ዘፈኑ ከባህላችንና ከኛነታችን እየራቀ በመጣበት ወቅት አሸንድዬ ሃይማኖታዊ(ባህላዊ)፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያለው አኩሪ ባህል ነውና ጠብቆና አስፋፍቶ መያዙ ነው፡፡
ወንፊቱ ሰፌዱ እያለ በጃችን
ያልተነፋ ዱቁት ምነው መብላታችን
እንዳሉት ሊቁ ለብዙ ነገር ምንጭና መነሻ የሚኾን ብዙ ርእሳነ ነገር÷ ለምሳሌ ለሥነ ጽሑፍ፣ ለሥነ ጥበብ፣ ለኪነ ጥበብ የሚኾን ጥሬ ነገር የምናገኝበት ነውና ጠብቀንና አክብረን እንያዘው፡፡ በሌላ በኩል ይህ በዓል ክርስቲያናዊ በዓል ከኾነ ለምን በአንዳንድ የሰሜን አካባቢ ብቻ ተወስኖ ቀረ? ለምን በመላው ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ዘንድ አይከበርም? በቂ መልስ ለመስጠት ጥናቱ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
* * *
ምንጭ፡- ዓለሙ ኃይሌ፣ የአሸንድዬ ባህላዊ ጨዋታ በላስታ ላሊበላ፣ ነሐሴ ፳፻፬ ዓ.ም
አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ፣ ፲፱፻፸፱ ዓ.ም
ባህላዊ የሆያ ሆየ – ቡሄ ጨዋታ በላስታ ላሊበላ
የኢትዮጵያን ጥንታዊነትና የሕዝቧን ተጠባቢነት ቁልጭ አድርገው ከሚያሳዩን ኁልቆ መሳፍርት የሌላቸው ባህሎች መካከል አንዱ ሆያ ሆዬ የሚባለው ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ባህላዊ ጨዋታ በማንኛውም ጊዜ የሚዘወተር ሳይኾን ወቅቱን ጠብቆ በየዓመቱ የሚመጣ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢ እየተረሳና እየቀዘቀዘ ብቅ ጥፍት እያለ፣ ዜማውና ግጥሙም አራምባና ቆቦ እየኾነ፣ ተራነትም እየታየበት የመጣ ይመስላል፡፡
ይህም የሚኾነው ማንኛውም ባህላዊ ኢንታንጀብል ቅርስ የመወለድ(የመፈጠር)፣ የመዳከምና የመጥፋት ባሕርይ ስላለው ወይም እንደ ታንጀብሉ ቅርስ ትኩረት ሳይሰጠው እየቀረ ሊኾን ይችላል፤ ወይም የባሕር ማዶውን ነገር ሁሉ ጠቃሚ፣ የእኛ የኾነ ነገር ኋላ ቀር እንደኾነ አድርገን በማሰብና የውጩን ስናከብርና ስንከተል የእኛን በመተዋችን፣ ከእጃችንም እያመለጠ ሲሄድ በመርሳታችን፣ ጥቅሙን ባለመገንዘባችን፣ በመንፈሳዊ ሀብት የበለጸገ የአበው ቅርስ፣ የሀገር ውርስ መኾኑን ባለማስተዋላችን ወይም በሌላም በሌላም ምክንያት ሊኾን ይችላል፡፡
ያም ኾነ ይህ የሆያ ሆዬ ሥነ ሥርዐት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይከበራል፤ በላስታ ላሊበላም አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ይከወን እንጂ እስከ አሁን ድረስ ቀጥሎ የሚገኝ ባህላዊ ጨዋታ ነው፤ በአብዛኛው በቡሄ ሰሞን፡፡ እንደሚታወቀው ቡሄ የሚከበረው የደብረ ታቦር ዕለት ነው፡፡ ደብረ ታቦር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኰቱንና ክብረ መንግሥቱን በቅዱሱ ተራራ የገለጠበት ታላቅ ዕለት ነው/ማቴ.፲፯፣ ማር.፱፣ ሉቃ.፱/፡፡ ፍጹም አምላክነቱ የተገለጠበትንና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑ በአባቱ የተመሰከረበትን ዕለት ለማዘከር ሕዝበ ክርስቲያኑ ሆያ ሆዬ በማለት፣ ችቦ በማብራት፣ ቡሄ በመጋገርና በመብላት፣ ጅራፍም በማንጓትና በመጋረፍ ያከብረዋል፡፡
ችቦው በደብረ ታቦር ተራራ የተገለጠውን ብርሃነ መለኰቱን እንዲሁም የኃጢአትን ጨለማ ሊገፍ ወደዚህ ዓለም የመጣውን፣ ብርሃናትን የፈጠረውንና እርሱም እውነተኛ የዓለም ብርሃን የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይወክላል፡፡ ቡሄው (ቡቼው) ያኔ ከብቶቻቸውን ይጠብቁ የነበሩ እረኞች በደብረ ታቦርና በአካባቢው በተገለጠው ብርሃን ጨለማ ጠፍቶላቸው ሐሤት በማድረግ ዘንግተው ስለቆዩባቸው ቤተሰቦቻቸው ለምግብ የሚኾን ዳቦ ጋግረው በሐ (ሰላም) እያሉ የወሰዱላቸውን፣ እንደ አንዳንድ ሊቃውንት አባባልም ከሰማይ የወረደውን እውነተኛ ኅብስት ኢየሱስ ክርስቶስን ለማስታወስ፣ የጅራፉ ድምፅ ከሰማይ ከእግዚአብሔር አብ የተሰማውን ‹‹ይህ የምወደው የምወልደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚለውን ነጎድጓዳማ ድምፅ ለማሰብ፣ ግርፊያው ክርስቶስ ዓለምን ሊያድን ሲመጣ በአይሁድም 6666 ጊዜ መገረፉን ለማዘከር ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በዊሕ (ቦሓ) መታየት፣ መገለጥ፣ መጉላት፣ ብሩሕ፣ ጽዱል፣ ጸዐዳ ብለው ቡሔ ከዚህ የወጣ ነው ይሉታል፡፡
በነገራችን ላይ ቅዱስ ላሊበላ ሕንጻዎቹን የሠራው በቅድስት ኢየሩሳሌም አምሳል ነውና ደብረ ሮሐም አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ትባላለችና ኢየሩሳሌም የያዘችውን ሁሉ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ላሊበላም ይዛለች፡፡ በዚህም መሠረት የደብረ ታቦር ተራራ ስሙንና ግብሩን እንደያዘች ከከተማው በስተደቡብ ከቤተ ገብርኤል በስተምዕራብ ጉብ ብላ ትታያለች፡፡ የደብረ ታቦር ዕለት ነሐሴ ፲፫ በዚያ ተራራ ወንዶች ጅራፍ በማስጮኽ ሲያስቧት፣ ሌሊቱን ደግሞ ችቦና ጧፍ ኋላም ማሾ ሲበራባት ያድር እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያስታውሳል፡፡ ማሕሌቱ ግን ከነዋዜማው በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በደመቀ ኹኔታ ተቁሞ እንደተዘመረ እንደተወረበ ይታደራል፤ ይዋላል፡፡ የቆሎ ተማሪው ዝክርና አከባበርም ልዩ ነው፤ ለደቀ መዛሙርት ምስጢረ መለኰት የተገለጠበት በዓል ነውና ለተማሪውም ምስጢር የሚገለጥበት ነው ተብሎ ይታመናልና፡፡
ሆያ ሆዬ በቅዱስ ላሊበላ የሚከበረው ግን ከመስከረም ፩ – ፲፯ ቀን ነው፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ለምሳሌ በወረዒሉ ከቡሄ ጀምሮ እስከ መስቀል ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በትግራይ በተለይም ‹‹አውርስ›› በሚል ስም ከነሐሴ ፲፮ ቀን ጀምሮ መስቀል ማጠናቀቂያው መኾኑን የሀገር ተወላጆች ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ነግረውታል፡፡ በመስከረም ላስታ ላሊበላ ዙሪያዋ ሁሉ ያምራል፤ አበባው ያብባል፤ እኽሉ ያሸታል፤ አዝመራው ይደርሳል፤ ወንዙ ይጠራል፤ ፏፏቴው ይወርዳል፡፡
በዚህ ጊዜ ዝናም ይቆማል፤ ጭቃ ይደርቃል፤ ጨለማው ይወገዳል፤ ብርሃን ይፈካል፤ ሰማይ በከዋክብት ይደምቃል፤ ምድር በአበባ ያጌጣል፤ ሜዳው በአበባ ያሸበርቃል፤ መስኩ በአደይ ይንቆጠቆጣል፤ መሬት ታሸብርቃለች፤ ፍጥረት ትሥቃለች፤ ምድር ትፈነድቃለች፡፡ የወጣቱ ልብም ይደሰታል፡፡ ፊቱ ያብባል፤ ገጹ ይፈካል፤ መንፈሱ ይረካል፤ ነፍሱ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሕይወቱ ትለመልማለች፤ መንፈሱ ትደሰታለች፡፡
ይህን ስሜቱን ከሚገልጽበት፣ ሕይወቱን ከሚያስደስትበትና ደስታውን ከሚያካፍልበት አንዱና ዋናው ሆያ ሆየ ነው፡፡ በዓሉ የሚከበረው በዓመት አንዴ በዚህ ሰሞን በመኾኑ እስከደርስለት ይቸኩላል፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ እየተተካ ዘመናትን አቆራርጦ ከሱ የደረሰውን ይህን ባህላዊ ሥርዐት እርሱም በተራው ሊያከብረው ይናፍቃል፡፡
በላስታ ላሊበላ የሆያ ሆየ በዓል ቅድመ ዝግጅት የሚጀመረው በዓሉ ከመከበሩ አንድ ቀን አስቀድሞ ነው፡፡ ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ ወጣት ወንዶች ወንዝ እየወረዱ ገላቸውን ያጸዳሉ፤ ልብሳቸውን ያጥባሉ፤ ለጭፈራው ዋና መሣርያ የሚኾናቸውን ዱላም ያዘጋጃሉ፤ ለጨዋታ የሚያስፈልጋቸውን ግጥምም ያጠናሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢ አለቃና ገንዘብ ያዥ ይመርጣሉ፡፡ የዘመን መለወጫ ዕለት ሁሉም በየቤቱ የተገኘውን ሲበላ ሲጠጣ ይውልና ወደ ማታው ጅራፍ በማጮኽ ይሰበሰባሉ፡፡ ያልወጣውን ለማስወጣት፣ ያልመጣውን ለማስመጣትም እየተቀባበሉ፤
እሆይ ሲራራ
እገሌ ሲፈራ
ከምድጃው
እናቱ ተነሺ
ያንን አብሺ
እሱ በመፍራቱ
ከኛ መለየቱ
እያሉ በረጅም ዜማ በጩኸት በየዐደባባዩ እየዞሩ ይጣራሉ፡፡ ይህን ጊዜ እኔ ወንዱ እንዴት ፈሪ እባላለሁ በማለት ዱላውን እየያዘ፣ ከየቤቱ እየተመዘዘ ወጥቶ ጀማውን (ስብስቡን) ይቀላቀላል፤ ያልተገናኘ ይገናኛል፤ የተነፋፈቀ ይሳሳማል፡፡
የጭፈራ ሰዓቱ ማታ ማታ ነው፡፡ ምናልባት አብዛኛው ገበሬና ከብት ጠባቂ ስለሚኾን ከየሥራ ስምሪቱ ውሎ ሲመለስ አመቺ ኾኖ ያገኘው ምሽቱን በመኾኑ ይኾናል፡፡ ወጣቱ በሥራ የደከመውን አካሉንና አእምሮውንም የሚያሳርፍበት፣ የሚዝናናበትና ሕይወቱን ደስ የሚያሰኝበትም ነው፡፡ ጨዋታው የበዓሉን ድባብ ሞቅ ደመቅ ያደርገዋል፡፡ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የብልጽግና እንዲኾን ብሩህ ተስፋን ይሰንቃል፡፡
ወጣቶቹ እየጨፈሩና እየፈነደቁ የሚያስተላልፉት መልእክትና የአከናወን ስልት ከቅርጽና ይዘት አኳያ በአራት ሊከፈል ይችላል፡፡ በተለይ የግጥሙ ዐይነት የጉዞ(የመንገድ)፣ የቤት፣ የምስጋና፣ የቅሬታ በመባል በአራት ይከፈላል፡፡ የሆያ ሆዬ ባህላዊ ጨዋታ በወጣት ወንዶች ብቻ የሚከናወን ነው፡፡ ወቅቱም ከዘመን መለወጫ ጀምሮ እስከ መስቀል ድረስ ብቻ ነው፡፡ መስቀል የበዓሉ ማጠናቀቂያ ወቅት ነው፡፡ ከነሐሴ 16 -21 ቀን ደግሞ የአሸንድዬ ባህላዊ ጨዋታ ይከናወናል፡፡ ሆያ ሆዬ የወጣት ወንዶች እንደኾነ ሁሉ አሸንዳየ ደግሞ የወጣት ሴቶች ብቻ ነው፡፡
ሴቶቹም ኾኑ ወንዶቹ በበዓል ሰሞን ያገኙትን ገንዘብ በአንዳንድ ከተሞች ዛሬ ዛሬ እንደሚታየው ተከፋፍለው ለግል ጥቅማቸው አያውሉትም፤ ሰቶቹ ገበያ ወጥተው አስፈላጊውን ነገር በመግዛት የሚበላና የሚጠጣ ያዘጋጁበታል፡፡ ወንዶች ድሮ እስከ ሰንጋ አሁን ሙክት ይገዙበታል፡፡ ተባብረው ይደግሱበታል፡፡ ዳስ ጥለውና ድንኳን ተክለው በጋራ ኾነው የሰጣቸውን ሁሉ ይጠሩና ያበሉበታል፤ ያጠጡበታል፡፡ ላልመጣም ተሸክመው ይወስዱለታል፡፡
ይህ ሁሉ ኾኖ ድግሱ ሲያልቅ በመጨረሻ ለመጪው ዓመት በሰላምና በጤና እንዲያደርሳቸው ተመራርቀው፡-
ከርሞ እንገናኝ ባመት
እናንተም ሳትሞቱ እኛም ሳንሞት
ተባብለው ይለያያሉ፤ በዓሉም እንደተናፈቀ በዚሁ ይጠናቀቃል፡፡ በአጠቃላይ ከነሐሴ እስከ መስከረም ፲፯ ድረስ ላስታ ላሊበላ በዓል በዓል ትሸታለች፤ ሞቅ ደመቅ ትላለች፡፡ ጧት ጧት አዕዋፍ ይዘምራሉ፤ ማታ ወጣት ወንዶች ሆያ ሆዬ ይላሉ፤ ቀን ቀን ሴቶች አሸንዳየ ይጨፍራሉ፤ ሌሊት ሌሊት ካህናት ሰዓታት ይቆማሉ፤ ስብሐተ ፍቁር ያደርሳሉ፤ ነጋ ለኪዳን ጠባ ለቁርባን ይተጋሉ፤ ቀን ቀን መዘምራን(ደባትራን) በማሕሌት ይቆማሉ፤ ይወርባሉ፤ ያሸበሽባሉ ማለት ይቻላሉ፡፡ የዜማ ዐይነት እዚህ ይሰማል፤ እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡
የሆያ ሆዬ ፋይዳ
ሆያ ሆዬ በየዓመቱ በፌስታ በደስታ ተከብሮ የሚያልፍ ባህላዊ ጨዋታ ብቻ አይደለም፡፡ የተሰባሰቡ ወጣቶች የማኅበራዊ ሕይወት ትስስር መሠረት የሚጥሉበት በዚሁ በሆያ ሆዬ ሰሞን ነው፤ በተለይ በገጠሯ ላስታ የሆያ ሆዬ ስብስብ በሂደት ወደሚዜነት ያድጋል፤ ቃል ኪዳን ይገባቡታል፤ አግብተው ሲጨርሱም ማኅበራዊ ቁርኝት የሚዳብርበት፣ የጽዋ ማኅበርም የሚጠጡበት፣ ቅዱሳንን የሚዘክሩበት፣ አብረው የሚበሉበት፣ የሚጠጡበት የሚደሰቱበት፣ በደቦና በወንፈል ተሰባስበው እያንዳንዳቸውን ሥራ እየተረዳዱ የሚተገብሩበት(በቤት ሥራ)፣ በግብርና (በእርሻ፣ በአረም፣ በአጨዳ፣ በውቂያ)፣ በኀዘን በደስታ የሚገናኙበት(የሚካፈሉበት) እስከ መጨረሻይቱ ሕቅታም የሚጓዙበት ይህም ሂደት ከእነርሱ ሕይወት ጋራ የሚያከትምበት ሳይኾን በልጆቻቸውም የሚቀጥልበት ነው፡፡
ሆያ ሆዬ የማኅበራዊ አገልግሎት ሚና በልጅነት ሙከራ የሚደረግበት ማለት መሪ ለመኾን የሚችል አለቃ፣ ታማኝ ገንዘብ ያዥ፣ ድምፃዊ፣ አቀንቃኝ፣ ያነጋገር ለዛ ያለው ውሕደቱን አድማቂ፣ ጨዋታ አሟቂ ኾኖ አቅምን በማሳየት በወደፊቱ ለአንድ ቁም ነገር የሚታጭበት ነው፡፡ ይህም እየተኮተኮተ ያድጋል፡፡ በጨዋታዎቹ በግጥም ሞያ የሚወደስበት፣ ፍርሃት፣ ስንፍና፣ ደግነት፣ ሞያ ቢስነት፣ ሥራ ፈትነት፣ ጊዜውን አልባሌ ሥፍራና ቦታ ማሳለፍ የሚነቀፍበት ወዘተ ነው፡፡ በጠቅላላው የኋላው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለዘላቂው ኑሮ መሠረት የሚጥልበት፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ጥቅምና እርባና የሚገኝበት በመኾኑ ባህሉ መጠበቅ መከበር ይገባዋል፡፡
ምንጭ፡- ዓለሙ ኃይሌ፣ ባህላዊ የሆያ ሆዬ ጨዋታ በላስታ ላሊበላ፣ ነሐሴ ፳፻፬ ዓ.ም