በሶሪያ ላይ የአሜሪካ ዛቻና ሩሲያ
የ2005 ዋና ዋና ፖለቲካዊ ክንዉኖችjavascript:;
የ2005 ዋና ዋና ፖለቲካዊ ክንዉኖች
የግብፅ ወቅታዊ ሁኔታ
Amharic News 1800 UTC –ሴፕቴምበር 09, 2013
ESAT Radio: Sep 09
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት የለም የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች አጥፊዎች፣ከሃዲዎች ናቸው አሉ
ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትሩ ትላንትና እና ዛሬ ለሕትመት በበቃው ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንደተናገሩት “የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርግጥም ለኢትዮጽያ ሕዝብ ዴሞክራሲ፣መልካም አስተዳደር ልማትና ሠላምን ለማምጣት አጀንዳ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሊያወግዙ ይገባል ብለዋል፡፡
” በኢትዮጽያ አክራሪነትና ሽብርተኝነት የለም ብለው የሚያስቡ ከሆነ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን አያውቁም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ስራና ሕዝቡን ለመምራት የሚያስችል ትልቅ ኃላፊነትና ብቃቱ የላቸውም ማለት ነው፡፡ ብቃቱ አለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ዓለማዊውንና አገራዊ ሁኔታ በአግባቡ ገምግመው ሸብርተኛነትን እንደዚሁም አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በኢትዮጽያ እያቆጠቆጠ የመጣና ሕዝቡን በግላጭ እየጎዳ ያለ እንደሆነ ማንም
የሚያውቀውን እየካዱ የሚሄዱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው ሰላማዊ፣ሕጋዊና ለአገሪቱ የሚጠቅም የፖለቲካ ስርዓት
ውስጥ ተወዳድረው ለማሸነፍ የተዘጋጁ ኃይሎች አይደሉም ማለት ነው” ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁንም ቢሆን ከድርጊታቸው ታቅበው በሰላማዊ፣ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ እንዳለባቸው የመከሩት አቶ ኃ/ማርያም ፣ ተወዳድረው ማሸነፍ ሲያቅታቸው ከእኔ የቀረ እንደሆነ አገሩቱዋ ትቀጣጠል
ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ አጥፊዎች ናቸው ማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ባለፈው ሳምንት እሁድ በተካሄደውና በመንግስት በሚደገፈው የአደባባይ ሰልፍ ከ600ሺ በላይ ሕዝብ
መውጣቱን አስታውሰው ይህ አክራሪ ኃይሎች ከሕዝቡ መነጠላቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡ አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች ከሕዝቡ ከተነጠሉ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድ በአዲስአበባ በመስቀል አደባባይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠርተውታል የተባለው ሰልፍ በቀጥታ በመንግስት የተመራ ሲሆን የቀበሌ ሹማምንት በየቤቱ እየሄዱ ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ እንዲገኙ የግዳጅ ፊርማ ሲያስፈርሙ እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
አንድነት ፓርቲ በአዳማ/ናዝሬት የተሰካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ
ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ገዢው ፓርቲ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከማውገዝ በተጨማሪ ህዝቡ ለእውነተኛ ለውጥ እንዲነሳ ጥሪ አድርጓል።
ሰልፈኛው ሲያሰማቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል ጥያቄያችን ህገመንግስታዊ ነው፣ ውሸት ሰልችቶናል፣ ስራ መግኘት መብታችን ነው፣ ጸረ ሽብር ህጉ በራሱ አሸባሪ ነው፣ መንግስት፣ የኑሮ ድጎማ ያድርግልን፣ ድህነት በወሬ አይጠፋም፣ ርእዮት አለሙ አሸባሪ አይደለችም፣ የታሰሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች ይፈቱ የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል።
በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተሳተፉበት በዚህ ሰልፍ ላይ በቅርቡ ራሳቸውን ከአንድነት የህዝብ ግንኙነት አመራር ቦታ ያገለሉት ዶ/ር ሀይሉ አርአያን ጨምሮ ሌሎችም ንግግሮችን አድርገዋል።
የአንድነትን ሰልፍ ለማደናቀፍ የከተማዋ ባለስልጣናት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም፣ ፓርቲው ዝግጀቱን በጥሩ ሁኔታ አጠናቋል።
አንድነት ፓርቲ የጀመረው የሶስት ወር ዘመቻ መስከረም 5 በአዲስ አበባ በሚያደርገው የተቃውሞ ሰልፍ ይጠናቀቃል።
የሐምሌ ጨረቃ! ከአንዱዓለም አራጌ ዋለ (አንድነት ም/ሊቀመንበር ከቃሊቲ ማጎሪያ) – ክፍል አንድ (ሊያነቡት የሚገባ)
ከጉልበተኞች ጠመንጃ የሚወጣ ጥይት ስጋን እንጂ እምነትን ሊገድል እንደማይችለው ሁሉ፣ ከቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ተነጥሎ ቅዝቃዜ በዋጠው ጠባብ ክፍል ውስጥ መታሰርም አካልን እንጂ ምናብን (ህልምን) ሊያስር የሚችልበት ጉልበት የለውም፡፡ ከቶስ እንደምናብ ሜዳውን፣ ተራራውን፣ ቁልቁለቱን፣ ዳገቱን፣ ሸለቆውን፣ ኮረብታውን በሰከንድ ክፍልፋዮች ከብርሃን ፈጥኖ በመምዘግዘግ ያለመዛነፍ ያሰበበት የሚደርስ ምን ኃይል አለ? ከጠባቧ ክፍል ውስጥ ‹‹ድርሻህ›› ተብላ በተሰጠችኝ 90 ሴንቲ ሜትር ላይ ቀሪ ህይወቴን አሳልፍ ዘንድ በግፍ ፍርድ ብታሰርም ዕረፍት ለማያውቀው ምናቤ ገለታ ይድረሰውና ይዞኝ ይከንፋል፤ ወደ ምፈልገው አድርሶ ይመልሰኛል፡፡
አንዳንዴ ከጁፒተር ማዶ ያሉ ተንሳፋፊ ዓለማቶችን ቢያስቃኘኝም፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን በሀገሬ ሰማይ ስር በጥቅጥቅ ደመና ላይ አንሳፎ ታላላቅ ወንዞቿን፣ ሃይቆቿን፣ የተንጣለሉ መስኮቿንና ሰማይ ጥግ የሚደርሱ ተራሮቿን በመንፈስ ያስጐበኘኛል፡፡ በተራሮቿ ግርጌና በመስኮቿ እምብርት ላይ ችምችም ብለው የተሰሩ ጐጆ ቤቶችንና በውስጣቸው ለሺ ዓመታት በፍቅር የኖሩ ደሃ ኢትዮጵያውያንን እንደጓደኞቻቸው ከሚመለከቷቸው የቤት እንስሳቶቻቸው ጋ ይታዩኛል፡፡ በየከተሞቹ ከድህነትና ከአፈና ጋር ግብግብ የገጠሙ፣ ከድህነትና ከፖለቲካ አፈና ነፃ ለማውጣት በዓለም ዙሪያ የተበተኑ ወገኖቼን ሳይቀር በአይነ- ህሊና ያስጎበኘኛል፡፡ አንዳንዴ ውሸትን እንደብልህነት፣ አፈናን እንደ አገዛዝ ስልት የወሰዱ አሳሪ ወንድሞቼና እህቶቼ የህሊና ጓዳ ውስጥ ይዞኝ ዘው ይልና ያረበበውን እብሪት፣ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ እርስ በእርስ የሚላተሙ ሃሳቦቻቸውን ፍልሚያ… ያሳየኛል፡፡
እነዚህ ምን አይነት ኢትዮጵያውያን? ምን አይነትስ ወላጆች ናቸው? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ የምናብ ፈረስ ጋልቤ የምጐበኘው የዚህን ዘመን ክንዋኔ ብቻ ሳይሆን የተደራረበውን የዘመን ጉም እየጠራረጉ ያለፉ አያሌ ዘመናትን ወደ ኋላ አስጉዞ ያሳየኛል፡፡ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመናት፡- አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጐንደርን፣ ያልዘመርንለትን የገዳ ዴሞክራሲ ስርዓትንና ሌሎች የጥንት ስልጣኔዎችን በብላሽ ያስኮመኩመኛል፡፡ የኢትዮጵያን የዳር ድንበር ነፃነት ለማስከበር አባቶቻችን ያደረጓቸውን የጀግንነት ውሎዎች በተለይም የጀግንነታችን ማማና የጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን የአድዋን ጦርነት ደጋግሜ አየዋለሁ፡፡ አድዋና መሰል የጀግንነት ማማዎች ላይ ቆሜ ኢትዮጵያውያን በየቀያቸውና በየዘመኑ ሰብዓዊ ክብራቸው ተረግጦ፣ በጭቆና አዘቅት ውስጥ ወድቀው ሲዘቅጡ ይታዩኛል፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ልዕልናቸውንና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ ያደረጉትን ትግል ያሳየኝና መንፈሴን ያበረታዋል፡፡
ታሪክ እንደሚዘክረው ከኋላ ቀሩ የፊውዳል አገዛዝ ነፃ ለመውጣት (በትክክል ወዴት ያመራ እንደነበር መናገር ባይቻልም) የመጀመሪያ አብሪ ጥይት የተተኮሰችው የ1953ቱ የእነ ጄኔራል መንግስቱና ገርማሜ ንዋይን የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ በተደረገበት ዕለት ነው፤ አቤት! እርሱን ተከትሎ የተሻለ ንቃት ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ‹‹ሕዝባዊ መንግስት›› ለመመስረት ያሳየው እንቅስቃሴ! የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለዓመታት የሞቱለት፣ የተጋዙለት፣ የተደበደቡለት፣ የተሰደዱለት… ሰላማዊ ትግል እና ያነሷቸው ጥያቄዎች ጆሮዬ ላይ ደጋግመው አስተጋብተዋል፡፡ በወቅቱ የዘውዳዊ ስርዓት ገበሬዎች፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ አሰምተው፣ በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲገቡ የነበረውን ትዕግስት አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ባነፃፀርኩት ቁጥር እንደ አዲስ እደመምበታለሁ፡፡ ንጉሳዊውን ስርዓት በመቃወም ተደጋጋሚ ሰልፎች ላይ ይሳተፉ የነበሩት እና ዛሬ ለድል የበቁት የቀድሞዎቹ ተማሪዎች፣ የአሁኖቹ ገዥዎች የትምህርት ነፃነትን ከመርገጣቸውም በላይ ቅሬታ በተነሳ ቁጥር የተማሪዎች መኝታ ቤት ድረስ በመዝለቅ ደም ማፍሰሳቸውን ሳስብ፤ ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ንፁሃን ላይ ከውሃ ይልቅ ጥይት ማዝነብ የሚቀናቸውና ተቃዋሚዎቻቸውን በውሸት ድሪቶ ዘብጥያ የሚያወርዱ አምባገነኖች መሆናቸውን ሳስብ የማይፈታ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡
ዘውዳዊ ስርዓቱን የተቃወሙ ሰዎች ከነገስታቱ በላይ ከዘመን ጋር የማይዘምኑ፣ ከአፈሙዝ ጋር የተጋቡ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ የምናብ ፈረሴ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ዓለም በመጣሁበት ሰሞን ከነበረው የጭቆና አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አልመው ወደ ከፋ የአምባገነንነት ገደል የወደቁበትን የእልቂትና የዋይታ አብዮት እየደጋገመ ያስቃኘኛል፡፡ በተፋላሚዎች መካከል የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ባይኖርም አፈ-ሙዝን በአፈ-ሙዝ ለማሸነፍ የተደረገው ደም መፋሰስና ወንድም በወንድሙ አስከሬን ላይ ቆሞ የፎከረበት የእርስ በርስ ጦርነትም ሌላኛው እረፍት የሚነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ የግፍ ቋት የነበረውን ደርግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አሸንፎ በድል አድራጊነት ወደ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሲገባ ሌላ የግፍ ቋት ይሆናል ብለው ያልጠበቁ አያሌዎች ነበሩ፡፡ ረጅሙ የመከራ ሌሊት መልሶ ላይጨልም ነግቷል ብለው ለተሻለ ነገር የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ትንሽ የሚባል አልነበረም፡፡ በአሁኑ አገዛዝ ከቀደሙት ህገ-መንግስታት የተሻለ ህገ-መንግስት ቢፀድቅም ቃልና ተግባር ሳይገናኙ ይኸው 22 ዓመታት አልፈዋል፡፡
እነሆም የሌላ ዙር የአፈና ሰለባ ሆኜ ወደምማቅቅበት እስር ቤት የምናቤ ፈረስ መልሶ አደረሰኝ፡፡ ሌላ ዙር እስር፣ ሌላ ዙር አፈና፣ ሌላ ዙር የህፃናት ለቅሶ፣ ሌላ ዙር የወላጆች ሰቆቃ፣ ሌላ ዙር ውርደት፣ ሌላ ዙር የአጤዎች ቀረርቶ፣ ሌላ ዙር የህዝብ እንባ፣ ሌላ ዙር… ባለንበት መርገጥ ቀጥለናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የከበረና ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የዳር ድንበር ነፃነቱን ማስከበር ቢችልም በአገሩ ሰብዓዊ ክብሩንና ነፃነቱን ከራሱ ገዢዎች አስከብሮ መኖር የቻለበት ዘመን የለም፡፡ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለው የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግል በድቅድቁና ዝናባማው የሐምሌ ጨለማ የምትወጣውን ‹‹ጨረቃ›› ይመስላል፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌለበት የገጠሩ የሀገራችን ክፍል የልጅነቱን የመጀመሪያ ዓመታት እንደእኔ ላሳለፈና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትግል በአንክሮ ለተከታተለ ሁሉ ስርዓቱና ጨረቃዋ የአንድ አባት ልጆች ይሆኑበታል፡፡ የሐምሌ ወር ጨለማ ጥቁር ነው፡፡ እንደግድግዳ ፊት ለፊት ቆሞ ነፍስን ያስጨንቃል፡፡ ጫፉ የማይታይ የጥላሸት ቁልል ይመስላል፡፡ ከጨለማው መደቅደቅ የተነሳ በቅርብ እርቀት ያለ ቁስን እንኳን ለመለየት የሚያስችል ብርሃን የለም፡፡ ወደሰማይ ለሚያንጋጥጥም በጥቁር የደመና ከል የተጋረደ ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን ህልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት የሐምሌ ወርን እየጠበቀች እየደጋገመች የምትወጣው ጨረቃም ወቅቷን ጠብቃ መውጣቷን አላቋረጠችም፡፡ ከአንድ ጥቁር የደመና ኮረብታ ወደሌላው ስትወረወር ለቅፅበት ትንሽ ብርሃን ብትፈነጥቅም ምድሩን እንደቡልኮ የሸፈነውን ድቅድቁን ጨለማ ሰንጥቆ ለማለፍ የሚችል የብርሃን ፍንጣቂ በመልቀቅ የጨለማውን ሀይል መግፈፍ የሚችል አቅም የላትም፡፡ እንዲያውም በብርሃን ጅረት የተሞላው መላ አካሏ በጨለማው ፅልመት ጠልሽቶና ከጨለማው ጋር ተመሳስሎ ይታያል፡፡ የሐምሌ ጨረቃ ወይ ድቅድቁን አትገፋ፣ ወይም የሐምሌን ወር አትዘል በየዘመኑ፣ በየአመቱ ፍሬ አልባ ዑደቷን ቀጥላለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልም እንዲሁ፡፡ እንደ ሐምሌ ጨረቃ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገሩን የህላዌ እድሜ ያህል ከጭቆናው ሌሊት ጋር በየወቅቱ ግብግብ ይገጥማል፡፡ በተለይም ከ1953 ዓ.ም ወዲህ ያሉት 50 ዓመታት ህዝባችን ከአብራኩ ከወጡ አምባገነን ገዥዎች መዳፍ ነፃ ለመውጣት ተደጋጋሚ ትግል አድርጓል፡ ፡ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሰብዓዊ ልዕልናው ባለቤት ለመሆን የሚያስችለውን የተጠና፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የሚመራና ህዝብ የራሱ ያደረገው የፀና ሰላማዊ ትግል በማድረግ ለውጤት አልበቃም፡፡
ለምን? በረጅሙ የሀገራችን ታሪክ የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበርን የመሳሰሉ ገንቢ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ፍልስፍናዎች ማዳበር የመቻላችንን ያህል፤ በሌላ መልኩም አሉታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ፍልስፍናዎች እንዳዳበርን መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ፖለቲካዊ መስተጋብራችን የተፋለሰ እንዲሆን አስተዋፆ አድርገዋል፡፡ በተለይም ከዘመነ-መሳፍንት በኋላ ያለውና በዚያ ዘመን የፖለቲካ ብሒል የተቃኘው ፖለቲካዊ ፍልስፍናችን ከምህዋሩ የወጣ ነው፡፡ በአመዛኙ በፍርሃት፣ በአድርባይነትና በጊዜያዊ ጥቅም የተለወሰ ፍርሃት፣ የማያምኑበትን መናገር፣ በአርምሞ ማሳለፍ፣ ያልሆነውን ሁነን መታየት፣ ነገሮችን በሚስጥር መያዝ፣ ተጠራጣሪነትና በውል ባልታሸ ሁኔታ እራስን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ማራመድ የመሳሰሉትን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል፡፡ በየዘመኑ የሚነሱ አምባገነኖችና የጎበዝ አለቆች ጥላ ስር ለመጠለል መሞከር እነርሱን አይነኬ አድርጐ መቁጠር እራስን ፍፁም አቅመ-ቢስ አድርጐ መረዳት ለገዥዎች ማሸርገድና ቅዳሴ-ማህሌት መቆም አያሌ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ እንደ ፖለቲካ-ጥበብ የሚቆጥሩት አካሄድ ነው፡፡ ይህም ሁሉ በጥልቅ አስተሳሰብና ከዚያም በሚመነጭ እምነት ላይ ቢመሰረት ችግር አልነበረውም፡፡ የተሳሳተ እምነት በማንገብ የጨለማ አገዛዞችን የነፃነት ንጋት ናቸው ብለው የሚዘምሩ፤ በረሃብ ስንሞት በቁንጣን ነው ብለው ሊያሳምኑን የሚዳዳቸው፤ የአገዛዞች ዋልታና ማገር የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በየዘመኑ አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡
ከዘመናት የአፈና አገዛዝ ነፃ ልንወጣ ይገባናል ብለን የምንታገል ወገኖች እንደመኖራችን ሁሉ፤ አገዛዙ የፀሐይ መውጫ ምኩራብ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች እምነታቸውን ያራምዱ ዘንድ መብታቸው ነው፡፡ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ ጨለማው በእርግጥም ጨለማ መሆኑን አይኖቻቸውን ገልጠው እንዲያዩና እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ሞታችን ከጨለማው ጋር ነው ብለው በጨለማው አካልነታቸው መቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ ታግሎ ማሸነፍና እነርሱም ከጨለማ ነፃ እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ ከባዱ የቤት ስራና እስከአሁንም ነፃነት ከእኛ እንዲርቅ ትልቁን አስተዋፆ እያበረከተ ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ‹‹መሃል ሰፋሪው›‹› ኢትዮጵያዊ ይመስለኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር በፖለቲካ ትግል ባሳለፍኳቸው ጥቂት ዓመታት ከባዱ ፈተና የገጠመኝ ከቤተሰቤ፣ ከወዳጆቼና ከቅርብ ጓደኞቼ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እነዚህ ወገኖች ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ከአገዛዙ ጋር ግብግብ ከመግጠም ይልቅ አንገቴን ደፍቼ ልጆቼን እንዳሳድግ ምክራቸውን በተደጋጋሚ ለግሰውኛል፡ ፡ ለነገሩ ትዳር ባልያዝኩበት፣ ልጆች ባልነበሩኝ ወቅትም ‹‹አርፈህ ተቀመጥ!›› የሚለው ምክራቸው አልተለየኝም ነበር፡፡ ትግል ውስጥ እንዳልገባ የሚሰጡኝ ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ በደም መፋሰስና በሸፍጥ የተሞላ መሆኑ አንደኛው ሲሆን በተጨማሪም ከኢኮኖሚ አዋጭነት አንፃር ፖለቲካ ፈፅሞ የማይመከር መሆኑን ያስረዱኛል፡፡ በመሆኑም አንገቴን ደፍቼ፣ ገዥዎች ወደአጋዙኝ ተግዤ እንድኖር፤ ልጆቼንም እንዳሳድግ ምክራቸውን ለግሰውኝ ነበር፡፡ አሁን እንኳን በእስር ላይ እያለሁ እንደሳይቤሪያ ብርድ አጥንትን ሰብሮ የሚገባና ነፍስን የሚወጋ ምክራቸውን ይልኩልኛል፡፡ ‹‹ነግረነው አልሰማንም››፣ ‹‹ህፃናት ልጆቹን ያለአባት ትቶ እንዴት ይታሰራል?›› ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከመበሳጨታቸው የተነሳ የመጐብኘት መብቴ ቢከበር እንኳን ሊጐበኙኝ እንደማይፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ወንጀልሰርቼ እንዳልታሰርኩ፣ ለመስራትም እንደማላስብና ሰላማዊ የትግል ስልትን የሃይማኖት ያህል እንደማምንበት ወዳጆቼም ሆኑ አሳሪዎቼ እኔ የማውቀውን ያህል ያውቃሉ ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ያም ሆኖ ግን ወዳጆቼ ስርየት እንደሌለው ሃጢያት፣ የአገዛዙ ዋናዎችም የሰማይስባሪ እንደሚያክል ወንጀል የቆጠሩት የተቃውሞ ፖለቲካ ጐራ መቀላቀሌን፣ በሀገሬ አንገቴን ቀና አድርጌ በመራመዴና የማምንበትን በቀጥታ በመናገሬ ነው፡፡ አገዛዙም ይኽን አይነት በፍርሃት የተሸበበ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ይፈልጋል፤ ወዳጆቼም አገዛዙ በግፍ ስላሰረኝ የነቢይነት ደረጃቸውን በመደመምያስባሉ፤ እርስ በእርሳቸው ይመጋገባሉ፡፡ የትችት ጦራቸውን እስር ቤት ድረስ የሚወረውሩት አብዛኞቹ ጓደኞቼ በታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የተማሩና የሚያስተምሩ፣ በመደበኛ ትምህርት ልህቀታቸው በሊቀ- ጠበብትነት ጐራ የሚሰለፉና ይህች ደሀ አገር ከውስን ጥሪቷ ቆንጥራ ያስተማረቻቸው ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ ዛሬ ወዳጆቼ ያሉት ደርሶብኛል፤ ትንቢታቸው ሰምሯል፡፡ አዎ! ልጆቼ በድንገት ከቤት ወጥቶ እስከአሁን ወደቤት ስላልተመለሰው አባታቸው በህፃንነት የአእምሮ ጓዳቸው ውስጥ እያንሰላሰሉና እየተጐዱ መሆኑን በሚገባ እረዳለሁ፡፡ በተለይ ልክ የታሰርኩ እለት የትምህርት ቤትን ደጃፍ የረገጠው የልጄ የሩህ ጥያቄዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ ‹‹ማሚ፣ እኔ አባት የለኝም እንዴ?››፣ ‹‹አባባ መቼ ነው ቤት የሚመጣው?››፣ ‹‹የአንተ ስራ መቼ ነው የሚያልቀው?›› የሚሉ ናፍቆት ያንገበገባቸውን ጥያቄዎች ያነሳል፡፡
እኔ የምከፍለው ዋጋ ይቅርና ልጆቼም በውል በማይረዱት ነገር ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን በጥሞና እገነዘባለሁ፡፡ ቀድሞውንም ያልጠበኩትም አልነበረም የሆነው፡፡ ግና! በልጆቼ ሰብዕና ላይ የከፋ ስብራት እንዳይደርስ እውነተኛ ፈራጅ ወደሆነው ፈጣሪ ከመፀለይ በቀር ምን ማድረግ ይቻለኛል? ይህችን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለው በእስር ቤት ነው፤ ይኸው አሁን ደግሞ ባልጠኑ እግሮቹ፣ ክፉ ደግ ባለየ ህሊናው ከሚያፈቅረው አባቱ ተለይቶ በባዕድ ምድር የፖለቲካ ስደተኛ ሆኖ የሚንከራተተው የናፍቆት እስክንድር ነጋ ህይወት ለዚህ የበቃው አባቱ እንደኔ የወዳጆቹን የአርምሞ ጥያቄ ባለመቀበሉ ጭምር ነው፡፡ አባታቸውን ተመላልሰው መጠየቅ በማይችሉበት እርቀት ላይ የታሰረባቸው የናትናኤል መኮንን ልጆች እንባም ሰብዓዊ ፍጡርን በተለይም የወላጆችን ልብ ምንኛ እንደሚሰብር ግልፅ ነው፡፡ ከሚያስተምርበት አዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከግቢ ውጭ እንደሚፈለግ በስልክ ሲነገረው የጠመኔውን ብናኝ ከእጁ ላይ አራግፎ የወጣው የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ ‹‹የኦነግ አባልና የፌደራላዊ አገዛዙን በኃይል ማስገንጠል አሲረሀል›› በሚል ክስ ተፈርዶበት ከህፃናት ልጆቹ ተለይቶ በዝዋይ እስር ቤት የግፉን ፅዋ እየተጎነጨ ነው፡፡ በእርግጥ አቶ በቀለም እንደ እኛ አርፎ ልጆቹን እንዲያሳድግ ተነግሮት ነበር፡፡ ሌሎች አያሌ ኢትዮጵያውያንና ልጆቻቸውም ተመሳሳይ የመከራ ህይወት እየገፋ ይገኛሉ፡፡ ልጆቻችንና የትዳር አጋሮቻችን እየከፈሉ ያሉት ዋጋ እኛ በእስር ቤት ከምንከፍለው የከፋ ይመስለኛል፡፡
ለጓደኞቼና ለወዳጆቼ የማነሳላቸው ጥያቄዎች ይኖሩኛል፡፡ ነፃነት አልቦ ህይወት ምን ምን ይላል? ለመሆኑ ነፃነትን በገዥዎች ችሮታ የተጐናፀፈው የየትኛው ሀገር ህዝብ ነው? በየትኛው ክ/ዘመን ይሆን? …አባቶቻችን ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ዘመድ አዝማዶቻቸውን ከኋላቸው ጥለው ወደ አድዋ መዝመታቸው ስህተት ነበር እያላችሁን ይሆን? ቴዎድሮስ በመቅደላ፣ ዮሐንስ በመተማ ለሀገር ክብር መውደቃቸው ትርጉም የለሽ ነበር ማለት ነው? ሌሎች አባቶቻችንስ በጉራ፣ በጉንደት፣ በማይጨው እና በአያሌ የጦር አውድማዎች ለሀገር ክብር እንደወጡ ሲቀሩ የሚናፍቋቸው ሚስቶችና የሚሳሱላቸው ህፃናት ልጆች ያልነበሯቸው ይመስሏችኋል? አሉላ አባ ነጋ እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ ለሀገሩ ዳር ድንበር አጥር ሆኖ ጣሊያንና ግብፅን በማስጨነቅ ዛሬ የምንኮፈስበትን ታሪክ ማጐናፀፉ ስህተት ነበር እያላችሁ ይሆን? የእነ በላይ ዘለቀ፣ የእነ አብዲሳ አጋ፣ የእነዘርአይ ደረሰ፣ የእነ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ የእነ አቡነ ጴጥሮስና የሌሎችም ስመ-ጥር ጀግኖቻችን ውሎ በከንቱ ጀብደኝነትና ግብታዊነት የተሞላ ነበር ማለት ነው? እነዚህ ጀግኖች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ክብር ለማስጠበቅ ከቀያቸው ርቀው ሲጓዙ ሞትን ከፊት ለፊታቸው እያዩት የቆሙለት እውነት አመዝኖባቸው እንደነበር ዘንግታችሁት ይሆን? አባቶቻችን በየተራራውና ኮረብታው ስለሀገር ክብር ባይቀበሩ ኖሮ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማግኘት የምንችል ይመስላችኋል? ወይስ የዳር ድንበር ነፃነት ከተከበረ፣ ዜጐች በጭቆና ቀንበር ቢማቅቁ ምንም ክፋት የለውም እያላችሁ ነው? ወይስ ጭቆና ከአብራካችን በወጡ ሰዎች እስከሆነ ድረስ እንደክብር ይቆጠራል እያላችሁ ነው? የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የተከፈለው ዋጋ ጠጋ ብለን ስናየው የህዝብን መሰረታዊ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያነሳ ሳታችሁት? አባቶቻችን ለሀገር ነፃነት የከፈሉት ዋጋ ተገቢ አልነበረም ካላላችሁ በስተቀር ለዜጐች ሉዓላዊነትና ለዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መታገል ስህተት ሆኖ የሚገኘው በምን ቀመር ነው? በዩኒቨርስቲዎች ስለ- ሰብዓዊ ፍጡር ልዕልና የምትማሯቸውና የምታስተምሯቸው ትምህርቶች ‹ነፃነት›ን በተመለከተ ምን ነበር ያሏችሁ? ወይስ ዲሞክራሲና ነፃነት ለእኛ ሀገር አይሰራም እያላችሁ ነው? የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነውን የአድዋን ድል ያስመዘገቡ አባቶች ልጆች ሉዓላዊነታችን ከገዥዎቻችን መዳፍ ነጥቀን ማስከበር ካልቻልን ‹የእሳት ልጅ አመድ› መሆን አይመስላችሁም? ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን ቀንበር እንዲሰብሩ የረዳቻቸው የአፍሪካ አገሮች በዴሞክራሲ ጐዳና በርቀት ጥለውን ሲተሙ፤ የእኛ በጭቆና አረንቋ ውስጥ መዳከር እንዴት ቁጭት አይፈጥርባችሁም? ወይስ የእናንተ ድርሻ ትችትና ታዛቢነት ብቻ ነው? እነዚህ ከፍ ብዬ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች ለምወዳቸው ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆን ‹‹የመሃል-ሰፋሪነት›› ሚና ለመረጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ያሉ ሸንኮፎችን አስቀድመን መግረዝ ካልቻልን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እንደ ሐምሌዋ ጨረቃ አሁንም በከንቱ ብቅ ጥልቅ ከማለት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡ ፡ ምናልባት የሀሳባችሁ ማጠንጠኛ ባለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት ማሳካት ያልተቻለው እንዴት አሁን ይቻላል? የሚል ከሆነ ይኸንን ጥያቄ ማንሳት፣ ለጥያቄውም መልስ መስጠትና በመልሱም ላይ ተመስርቶ በእውነተኛ ነፃነትና ህዝባዊ ልዕልና ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መታገል እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ የተወሰኑ ጥያቄዎችን አክዬ ላንሣ፡ ፡ ሁሉም የግል ጥቅሙንና የአብራኩን ክፋዮች ብቻ በሚያስቡባት ሀገር እንዴት ህዝብ ከአገዛዝ ነፃ ሊሆን ይችላል? በየማጀቱ አገዛዙን በመርገም ነፃ መውጣት ቢቻል ኑሮ ከረጅም ዘመናት በፊት ነፃ አንወጣም ነበር ትላላችሁ? አባቶቻችን ለነፃነት መስዋዕት መሆናቸው ትክክል ነበር የምትሉ ከሆነ የስብዕና መሰረትና የነፃነቶች ሁሉ የበላይ ለሆነው የሰብዓዊ መብት መታገል ትክክል የማይሆንበት አሳማኝ ምክንያት ምንድን ነው? ከገዥዎች መዳፍ ለመውጣት አሳማኝ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ይኽን ከገዥዎች መዳፍ ለመውጣት የሚደረግን ትግል እንዳላየን አይተን ብናልፍ ለሁላችንም የማይቀረው ሞትን ተጋፍጠን ወደመቃብር ስንወርድ በምን አይነት ክብርና የህሊና እረፍት ማሸለብ እንችል ይሆን? የዘወትር ህልማችን ሰብዓዊ ልዕልናችን ተጠብቆ የምንኖርበትንና ልጆቻችን የማያፍሩበትን ሀገር ማውረስ ሆኖ ሳለ የአገዛዙን የጭቆና አርጩሜ በመፍራት ከእምነታችን ውጭ የሆኑ ተግባሮችን ስንፈፅም የምንበጀው እስከመቼ ነው? ለዘመናት እላያችን ላይ ቤት የሰራብንን የጭቆና ቀንበር መስበር በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያልተከወነ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለል የመጣ የቤት ስራ ነው፡፡ በውዝፍ ያደረ ቁምነገር ከቅርሶቻችን ሁሉ የገዘፈና የታሪካችን ፈርጥና የማንነታችንም መደምደሚያ ነው፡፡ በዚህ የሰብዓዊ ልዕልና ጉዳይ ላይ መታገል ሰው የመሆንና ያለመሆንን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ በነፃነት አለመታገል የቤት ስራውን ለልጆቻችን ወዝፎ ማሳደር በጭቆና ቀንበር ለመገዛት ህዝበ ውሳኔ የመስጠት ያህል ይቆጠራል፡፡ በሌላ በኩል ነፃ ለመውጣት እንደቀድሞ ነፃ አውጭ አበጋዞችን መጠበቅ አይገባንም፡፡ ይኽን የምናደርግ ከሆነ ሰማያችን በጭቆና ደመና እንደተሸፈነ ይቀጥላል፡፡ ጥቂቶችን አንጋጠን ስንጠብቅ በውስጣችን ያለውን ትልቅ የነፃነት ሃይል እንዳናይ ግርዶሽ ይሆንብናል፡፡
ይኽን በመሰለው የነፃነት ትግል የሚጀምረው የራስን የከረመና የተሳሳተ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተሳሰብ ከመሞገት ነው፡፡ ከዚያም ከፍ ሲል እንደ ፖለቲካ ባህልና የብልህነት ቁንጮ በመውሰድ ለህፃናት ልጆቻችን ሳይቀር በምክር መልክ የምንለግሳቸው ልዩ ልዩ ያልተሰለቀቁ አሉታዊ አስተሳሰቦችን በቅድሚያ ታግሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ስለሁሉም ፤ሁሉም ስለእያንዳንዱ ግድ በማይሰጠው ሀገር ውስጥ አምባገነኖች የሚዘውሯቸው አገዛዞች መኖራቸው የግድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ስለነፃነት ክብርነት ለማንም ማስረዳት እምብዛም አይጠበቅብንም፡፡ ነፃነት እንደ እንጉዳይ በየዛፉ ስር ያለትልቅ መስዋዕትነት በቅሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ ይኸንን የነፃነትን ውድነት ስንረዳ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር እንደዘመቱት አባቶቻችን ሁሉ ያለነፃነት ከመኖር ይልቅ ህፃናት ልጆቻችን ጥለን፣ ከሞቀ ቤታችን ወጥተን በእስር ቤት የሲሚንቶ ወለል ላይ መጣልን እንመርጣለን፡፡ በነገራችን ላይ ደጋግሜ ከምጠቅሳቸው ጀግኖች ጋር እራሴን እያወዳደርኩ አለመሆኑን አንባቢዎች ልብ እንድትሉልኝ እወዳለሁ፡፡ በታሪክ ኮረብቶች ላይ ከድንቅ የጀግንነት ውሎዎቻቸው ጋር ከፍ ብለው የሚታዩ ጀግኖች ጫፍ የሚደርስ አንዳች ስራ እንዳልሰራሁ ጥሩ አድርጌ እገነዘባለሁ፡፡ አላማዬ የዳር ድንበርን ሉዓላዊነት ከሰብዓዊ ሉዓላዊነት ጋር ማነፃፀር ነው፡፡
ሌላው የአገር ውስጥ ገዥዎችንን እንዴት ከውጭ ሀገር ወራዎች ጋር ያነፃፅራል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሁለቱም የዘመቱት በነፃነታችንና ሰብዓዊ ክብራችን ላይ ነው፡፡ የነፃነት ትርጉም ከሀገር ልጅነትም በላይ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል መንገድ ስንጓዝ ትግላችን ጨቋኝ ወንድሞቻችን ወደልባቸው እንዲመለሱና ሁላችንም በነፃነት የምንኖርባትን የጋራ ሀገር እውን እንድትሆን ከማድረግ ጋር ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ እንዲታመሙና እንዲሞቱ አይደለም ፡፡ በእኛና በልጆቻችን ላይ እያደረሱት ያለው በደል በእነርሱም ላይ እንዲደርስ ፈፅሞ የምንመኘው ነገር አይደለም፡፡ ነ ፃነትን ከውጭ ሀገር ወራሪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ጨቋኝ መጠበቅ መቼም በይደር የሚያዝ ተግባር አይደለም፡፡ ስለሁላችን ነፃነትና ሉዓላዊነት የተዘረጋ የተማፅኖ ቃል እንጂ፡፡ በሀሰት ‹‹አሸባሪ›› ተብለን ዘብጥያ ብንወርድም ትግሉን ከመቀጠል ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ነፃነትን መጠየቅና መታገል ነፃነቱን የተጠማ የነፃነት ታጋይ ሁሉ ድርሻ መሆን ይኖርበታል፤ ይሁንና የናፈቃችኋትን ነፃነት አታገኟትም ብለው ወህኒ መወርወር የአፋኞች የአፈና ተግባር ቢሆንም መንበርከክ ለከፋ መከራ፣ ለበረታ ጭቆና ከማገለጥ ውጪ ትርፍ አልባ ነው፡፡ የአሁኖቹ ገዥዎች እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የተሳሳተ የፖለቲካ ባህላችን ያበቀላቸው መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችን ካልተቀየረ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ሌሎች አምባገነኖችንም ማብቀሉን ይቀጥላል፡፡
በአምስት አመት ውስጥ ማዕከላዊ እስር ቤት ሁለት ጊዜ ስታሰር፤ ሃላፊዎች ተለዋውጠው ባገኛቸውም የሁለቱም ዋና ኃላፊዎች ቃልና ተግባር ግን ትንሽ እንኳ ልዩነት አልነበረውም፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም እንዳገኙኝ የጠየቁኝ አንድ አይነት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ወንድ ከሆንክ ለምን ጫካ አትገባም?›› የሚል፡፡ ወንድነት ማለት አፈ-ሙዝን፤ በማይናወጥ የፍቅርና የወንድማማችነት መንገድ መጋፈጥ፤ ተጋፍጦም ሳይገሉ መሞት ነው ወይንስ በራሳችን ጥላ ሳይቀር እየደነበርን ንፁሃንን መግደል? የሚገርመው እኮ ለአፈ-ሙዝ ፍልሚያ የጥሪ ካርድ የሚበትኑት ወገኖች የደሃ ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾችን ደም ለማፍሰስ እንጂ እነርሱማ ከመኪና ተደግፈው ለመውረድ ምንም የማይቀራቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ በተለይም የአገዛዙ ዋነኛ ሰዎች ይችን ሀገር ለሁላችን ወደሚበጅ ንጋት ይዘዋት ለመውጣት እድሉን ለዓመታት ቢያገኙም ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ይልቅስ እብሪት የሁለንተናቸው ማጠንጠኛ ምህዋር ሆኖአል፡፡ አንዳንዶቹን በጨረፍታ በማየት ለወንድማማችነትና የኢትዮጵያን የባጁ ችግሮች ለመፍታት በጐ አስተዋፆ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፣ ሕዝብን እንኳን ባይፈሩ ፈጣሪን ይፈሩ ይሆናል ብለን ተስፋ ብናደርግም ሁለቱንም እንደማይፈሩና የኢህአዴግ ዋና ሰዎች መለያ የሆነውን እብሪትና ሃኬት የሙጥኝ ብለው መንጐድ ቀጥለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ አገዛዞች ከዚህ የተለየ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ይኸኛው አገዛዝ ከቀድሞዎቹ ለመለየት የሚሞክረው በእውነት ላይ ያልተመሰረተ የፕሮፓጋንዳ ደመራ በማቀጣጠል ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳ ደመራው ህዝቡንም ሆነ አገዛዙን በብርሃን እንዲመላለስ አላደረገውም፡፡ ሊያደርገውም አይችልም፡፡ አገዛዙም ሆነ ህዝቡ ከፍርሃትና ከጨለማ ጉዞ ነፃ ሊወጣ የሚችለው የእውነት ችቦ ለኩሶ ከዚያም በሚገኘው ብርሃን ዙሪያ ተሰባስቦ መወያየት ሲቻል ነው፡፡ ለዜጐች ሉዓላዊነት ክብር የሚሰጥ አገዛዝ ቢኖር የፕሮፓጋንዳ ደመራ አቀጣጥሎ በዙሪያው መጨፈር ባላስፈለገ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተግባር ከቃላት በላይ ይናገራልና፡፡ የአገዛዙን አምባገነናዊ ባህሪዎችና ተግባሮች በመተንተን ከዚህ በላይ ጊዜ ልናጠፋ አይገባንም፡፡ ምንስ የማይታወቅ ነገር አለ? እንኳን የአፈናው ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ቀርቶ ዓለምም በቅጡ ተረድቶታል፡፡ አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ የሚገዛ ቢሆን ለመቃወም ከቤታችን መውጣት ባላስፈለገን ነበር፡፡
ትልቁ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ከ50 ዓመታት በላይ የአገዛዝ ስርዓትን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ለማስወገድ የተደረገው ጥረት፣ የተከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እንዴት እስካሁን ለፍሬ ሊበቃ አልቻለም? የሚለው ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ አሁን ቢያንስ ወደተሻለ ምዕራፍ ትግሉን ለማሸጋገር አልቻሉም? እስከ አሁን በተደራጁ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ ከመታገል ይልቅ በተለየና የራሳችን በሆነ መንገድ አስተዋፆ እናበረክታለን ብለን በተለያየ መስክ ተሰልፈን የምንገኝ ሰዎችም ምን ያህል አስተዋፆ አበረከትን? ብለን ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ጊዜው በተግባር የማይደገፍና የተጠጋገኑ ምክንያቶችን በመደርደር ብቻ ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የአፈናው ሰለባዎች መሆናችንን አለም በቅጡ ተረድቶታል፡፡ አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ የሚገዛ፣ የህግ የበላይነትን የሚያከበር ቢሆን ኖሮ ለመቃወም ከቤታችን መውጣት ባላስፈለገን ነበር፡፡ ትልቁ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ከ50 ዓመታት በላይ የአገዛዝ ስርዓትን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ለማስወገድ የተደረገው ጥረት፣ የተከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ዛሬም ለፍሬ ሊበቃ ያልቻለበትን ምክንያት ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ ስለምን ትግሉን ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸገር ተሳናቸው? ዛሬም ድረስ የተደራጀ የፖለቲካ ትግልን ተቀላቅሎ ከመታገል ይልቅ በተለየና የራሳችን በሆነ መንገድ አስተዋፆ እናበረክታለን ብለን በተለያየ መስክ ተሰልፈን የምንገኝ ሰዎችም አበርክቶአችን ምን ያህል እንደሆነ ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ጊዜው በተግባር የማይደገፍና የተጠጋገኑ ምክንያቶችን በመደርደር ብቻ ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አይደለም፡፡ የነፃነት ጉዳይ ‹ለነገ…› ተብሎ በይደር የሚቆይ አይደለም፡፡
ሸንጎ በአዲስ አበባ የተጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚደግፍ አስታወቀ
የሸንጎ መግለጫ፦
ሸንጎ በአዲስ አበባ የተጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ ይደግፋል
ጳጉሜ ፪፣ ፪፼፭
September 7, 2013
ህገመንግስታዊና ተፈጥሮአዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ የሚጥሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ህወሓት/ኢህአዴግ ቀንተቀን እያጠበበው ከመጣው የፖለቲካ ምህዳር ሊያስወጣቸው የሚያደርገውን ጥረት ሸንጎ እያወገዘ፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች የሚደርስባቸውን አስከፊ እንግልትና በደል ተቋቁመው ህዝባዊ እንቅስቃሴውን ማስቀጠላቸውን ያደንቃል።
ያለውን አምባገነን አገዛዝ ታግሎ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር የታጋይ ድርጅቶችን አንድ ላይ መቆም ግድ የሚል በመሆኑ በነጠላ የሚደረጉ ትግሎችን በማስተባበር ትግሉን ውጤታማ ማድረግ ወደሚቻልበት ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ ነው። አንድነት መስከረም አምስት በአዲስ አበባ የጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ ለማዘጋጀት መወሰናቸው እሰየው የሚያሰኝና ትግሉ ጥሩ አቅጣጫ ይዞ መጓዝ እንደጀመረ የሚያመላክት ነው። ይህም ትብብር ከፍወዳለ ደረጃ እንደሚደርስ ትስፋችን ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲህ ተባብረው በሚቆሙበት ወቅት ህዝቡም በነቂስ በመውጣት የተባበረ ጠንካራ ጉልበት እንዲፈጥር ሸንጎው ያሳስባል።
በተባበረ ትግል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!
የ2005 የጊዜ መሥመር
መስከረም
- § መስከረም 11/2005 የተከበሩ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ሆነው፣ የተከበሩ ደመቀ መኮንን ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ፈፀሙ፣
- § መስከረም 17 ቀን 2005 ድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በሒልተን ሆቴል አንድ ሺሕ ያህል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ጋብቻውን ፈፀመ፣
- § ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ አሜሪካን ሃገር ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የሴቶች ሚዲያ ፋውንዴሽን የ2012 ‹ፅናት በጋዜጠኝነት ሥራ› የተሰኘ ሽልማት አገኘች፣
- § የ2005 የእስልምና ምክር ቤት /መጅሊስ/ ምርጫ በየቀበሌው ተካሄደ፣
- § የጋዜጠኝነት እና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ዶ/ር መሠረት ቸኮል ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
- § ጠ/ሚኒስቴር ኃ/ማርያም ደሳለኝ አቶ ቴድሮስ አድሃኖምን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤አቶ ሙክታር ከድር እና ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በጠ/ሚኒስቴርነት ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ፣ የትራንስፖርት እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር፤ አቶ ከበደ ጫኔን የንግድ ሚኒስቴር እንዲሁም ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አድርገው ሾሙ፣
- § በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የወንጀል ችሎት በቀረበባት የሽብርተኝነት ወንጀል 14 ዓመታት እስርና 33 ሺሕ ብር ቅጣት የተጣለባት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮተ ዓለሙ፣ በይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የእስር ጊዜዋን ወደ አምስት ዓመታት በመቀነሱ ምክንያት ለሰበር ችሎት “በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል” ስትል አቤቱታ አሰምታ፤ ሠበር ሰሚ ችሎቱ በሰጠው የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፉትን የቅጣት ውሳኔ አፀና፣
- § የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፤ ከሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶበት የ18 ዓመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በአፋጣኝ ከወህኒ ቤት እንዲለቀቅ ጥያቄ አቀረቡ፣
- § አራት በፍ/ቤት እስር የተፈረደባቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የ2012 የሄልማን/ሃሜት ሽልማት መሸለማቸውን፤ ተሸላሚዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ እንዲሁም በሌለበት የተፈረደበት የቀድሞዋ የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ አዘጋጅ መስፍን ነጋሽ ሲሆኑ ጋዜጠኞቹ ሽልማቱን ያገኙት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስጠበቅ ላደረጉት ጥረት መሆኑም ተጠቅሷል፣
- § የ33ቱ ፓርቲዎች ኅብረት በሚያዚያ ወር የተካሄደውን የአዲስ አበባ መስተዳደር እና በመላው ሃገሪቱ በሚካሄደው የወረዳና የክልል ምክርቤቶች ምርጫዎች ላይ ላለመሳተፍ ውሳኔ አሳለፉ፣
- § በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቃ፤ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አዳነ ግርማ ከ37ዓመት በኋላ የመጀመሪያ የሆነችውን ብቸኛ ጎል ለኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ አስቆጠረ፣
- § ኢትዮጵያየራሷን ሳተላይት ለማምጠቅናየሰው ኃይሏን ከቴክኖሎጂው ጋርለማስተዋወቅ የሚያስችል የሙከራሥራ መጀመሯን፣ በምክትል ጠቅላይሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚዘርፍ አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽንቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ርደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ፣
- § በ2004 ከሃያ ዓመት እስር በኋላ የተፈቱት ከፍተኛ የደርግ አመራር የነበሩት ኮሎኔል ደበላ ዴንሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
- § ድምፃዊታምራት ሞላ ለረጅም ዓመታት ሕክምና ሲከታተል በነበረበት የደም ካንሰር ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፣
- § የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን 6ኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን አድርጋ መረጠች፣
- § የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ዶክተርዮናስ አድማሱ በ69 ዓመታቸውከዚህ አለም በሞት ተለዩ፣
- § በአዲስአበባ በባሕል ሕክምና ታዋቂየነበሩት ሐኪም ማሞኃይሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
- § ከሁለትዓመት በፊት በአምባሳደርነትና በምክትል አምባሳደርነት ማዕረጐች ተሹመው በተለያዩ አገሮች ከተመደቡ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ዐሥራ ስምንት የሚሆኑት ወደ አገር እንዲመለሱ ተደረገ፤ ሁለቱ በድጋሚ ሹመት ወደሌሎች አገሮች ሲመደቡ የተቀሩት ግን በአገር እንዲቀሩ ውሳኔ ተላለፈ፣
- § በኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ፣ በሰማያዊ ፓርቲ እና በባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር አስተባባሪነት፤ በጣሊያን አፊሌ በተባለ ቦታ የተገነባውን የግራዚያኒ ኀውልት እና መታሰቢያ ቦታ በመቃወም፤ ከሰማእታት ኀውልት (6 ኪሎ) አንስቶ እስከ ጣሊያን ኤምባሲ የሚዘልቅ የእግር ጉዞ መጋቢት 8/2005 ጥሪ ተላለፈ፤ ሰልፉን ለማካሄድ የተገኙ አባላት እና የሰልፉ ዓላማ ደጋፊዎች ሰማእታት ኀውልት መሰባሰብ እንደ ጀመሩ ፖሊስ ሰልፉን ሕጋዊ አይደለም ብሎ በኃይል በመበተን እና 40 የሚሆኑ በሰልፉ የተገኙ ሰዎች ለአንድ ቀን ታስረው ተፈቱ፣
- § የኢሕአዴግዘጠነኛ ጉባዔ በባሕርዳር ከተማ ለአራት ቀናት ተካሄደ፣
- § ‹ኢትዮትዩብ› በአሜሪካ አምስተኛ ዓመቱን አከበረ፣ በዕለቱም ‹ለፕሬስ ነፃነት የተጋ› በሚል ዓመታዊ ሽልማት ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተሸላሚ በወኪል ተበረከተለት፣
- § የቀድሞውየኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርመለስ ዜናዊ መታሰቢያ “መለስ ዜናዊፋውንዴሽን” መሥራች ጉባኤበአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያአዳራሽ ተካሄደ፣
- § ላለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ ኮንትራት አማካኝነት በአሜሪካ ስትጎበኝ የነበረችው ሉሲ (ድንቅነሽ) ጉዞዋን ጨርሳ ወደ ሃገሯ ተመልሳ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆነች፣
- § ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ጀርባ የሚገኘው የአቡነ ጴጥሮስ ኀውልት፤ በአዲስ አበባ በመሠራት ላይ በሚገኘው የቀላል ባቡር ግንባታ ምክንያት ከነበረበት ቦታ ተነስቶ ብሔራዊ ሙዚየም እንዲገባ ተደረገ፣
- § በጋምቤላ ክልል አኙዋክ ዞን አቦቦ ወረዳ ልዩ ቦታው ቁርጫ በሚባል አካባቢ 17 ተማሪዎችንና በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሠማራው ሳዑዲ ስታር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሠራተኞች የሆኑ ስድስት ሰዎችን፣ በድምሩ 23 ሰዎችን በጥይት ደብድበው በመግደልና በሽብር ወንጀል ተከሰው ከነበሩት 14 ግለሰቦች መካከል፣ ዘጠኙ በሞት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፣
- § ጋምቤላንለሰባት ዓመታት በፕሬዚዳንትነትየመሩት አቶ ኡሞድኡቦንግ የጋምቤላ ሕዝብዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) እና የክልሉ ምክር ቤትባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከፓርቲውምክትል ሊቀመንበርነትና ከክልሉፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ በመወሰኑ፣ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶጋትሉዋክ ቱት በምትካቸው የክልሉፕሬዚዳንትነት ሆነው ተሾሙ፣
- § የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰጠውን የጥፋተኝነት ብይንና ብይኑን ተከትሎ የተጣለባቸውን የቅጣት ውሳኔ በመቃወም፣ ከነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበው በነበሩት፣ እነ እስክንድር ነጋ ላይ ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ ይግባኝ ካሉትፍርደኞች ውስጥ ከክንፈሚካኤልደበበ (አበበ ቀስቶ) በስተቀር የሁሉም የሥርፍርድ ቤት ቅጣት ውሳኔ እንዲፀና ተደረገ፤ በመሆኑም ክንፈሚካኤልበሥር ፍርድ ቤት ተጥሎበት የነበረው የ25 ዓመት ፅኑ የእስራት ቅጣት ማቅለያውሲያዝለት ወደ 16 ዓመትፅኑ እስራት ተቀነሰ፣
- § የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በ124 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2004 ዓ.ም. ሒሳብን ኦዲት በማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አለመታወቁንና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ደግሞ መንግሥት ማጣቱን አሳወቀ፤ ከዚህ ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር 401.757 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 173.756 ሚሊዮን ብር፣ የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ 155.597 ሚሊዮን ብር የታየባቸው መሥሪያ ቤቶች መሆናቸው ተገለፀ፣
- § የፌደራል ፀረ ሙስና እና የሥነ ምግባር ኮሚሽን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መላኩ ፋንታን ጨምሮ ሌሎች የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በመዋላቸው የክስ የፍርድ ሒደቱ ተጀመረ፣
- § በባሕርዳር ከተማ የፌደራል ፖሊስ አባል የሆነ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ 10 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ወንጀለኛው ፖሊስም ራሱን አባይ ወንዝ ውስጥ ወርውሮ ሕይወቱን አጠፋ፣
- § በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ዣቪየር ማርሻል በ61 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
- § በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ምትክ፣ የአዳማ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ በከር ሻሌ ተሾሙ፣
- § በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት እና በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት እና “ቤተ ክሕነትና መንግሥት በኢትዮጵያ ከ1262-1527” (Church and state in Ethiopia 1262-1527) በተሰኘው መጽሐፋቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
- § አዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓል ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ቢያደርግም የአ.አ መስተዳድር ሰልፉን ጥበያ የሚያደርግ የፖሊስ ኃይል እጥረት አለብን በማለት ለሌላ ጊዜ እንዲያዘዋውሩት ጠየቀ፣
- § የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/የአፍሪካ ኅብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ዋናው ጽ/ቤት በሚገኝበት በኢትዮጵያ አከበረ፣
- § የሕዳሴው ግድብ ቀጣይ የግንባታ ምዕራፍ የሆነው ወንዙን አቅጣጫ የማስቀየስ ሽራ ተከናወነ፣ ይህን ተከትሎም ከሃገሪቷ ፖለቲከኞች ጋር በቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሙርሲ የተመራ ውይይት ሲካሄድ የግድቡ ሥራ እውን እንዳይሆን የሚያደርጉ ሐሳቦች መሰንዘራቸው፤ ይህ ውይይትም በስህተት በሃገሪቱ የብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ ተላለፈ፣
- § ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ መነሻውን የፓርቲው ፅ/ቤት፤ መድረሻ ቦታውን ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ያደረገ፣ በርካቶችን ያሳተፈ እና ከ97 ምርጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄደ፣
- § አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ‹‹ሚሊዮን ድምፆች ለነፃነት›› የተሰኘ፣ ለሦስት ወራት የሚቆይ ሕዝባዊ ንቅናቄ ጀመረ፤ በንቅናቄው ሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ ሠላማዊ ሰልፎችና በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ የተቃውሞ ፊርማ እንደሚሰበሰብ ተነግሯል፣
- § ለቀደሙት 20 ወራት በሽብር ወንጀል ተፈርዶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ፣ ጦማሪ እና አራማጅ እስክንድር ነጋ፤ ከባለቤቱ እና ልጁ ውጪ በሆኑ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ እንዲጎበኝ ሲፈቀድለት የሚጎበኝበት ሰዓትም እንደማንኛውም በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎች እንደሆን ተደረገ፣
- § በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የ2013ቱ የቢግ ብራዘር አፍሪካ ውድድር ከኢትዮጵያ የሄደችው ቤቲ የወሲብ ትእይንና አነጋጋሪ መሆን፣
- § የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሦስተኛውን ጨዋታ በሃገሩ አድርጎ ተጋጣሚውን ደ/አፍሪካን 2-1 በመርታት የቀሪውን ጨዋታ ነጥብ ሳያሳስበው ምድቡን በአንደኝነት መምራቱን ቢያረጋግጥም በማግስቱ በፌዴሬሽኑ ስህተት ብሔራዊ ቡድናችን ሦስት ነጥቦችንና ሦስት ጎሎች የሚያስቀጣውን ጥፋት ማጥፋቱን ተነገረ፣
- § ፓርላማውበ2005ዓ.ምየሥራ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ የሥልጣንሹም ሽር በማድረግ አስር አዳዲስ ሚኒስተሮችሾመ፣
- § የቅዱስጊዮርጊስ እግር ኳስክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስታሪክ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብማጣሪያ ያለፈ የመጀመርያክለብ መሆኑ፣
- § ወጣት የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር መሐመድ አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሚያዘጋጀው ‹ዘ ስትሪም› በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እና ተያያዥ ጉዳዮች የብዙዎችን (በተለይም ማኅበራዊ አውታር ተጠቃሚዎችን) ትኩረት የሳበ እና ያነጋገረ ንግግር አደረገ፤
- § አንድነት ፓርቲ በጎንደርና ደሴ ከተሞች በተመሳሳይ ቀን (ሐምሌ 7/2005) ‹‹ሚሊዮን ድምፆች ለነፃነት›› በተሰኘው ሕዝባዊ ንቅናቄው ሠላማዊ ሰልፎችን አካሄደ፣
- § አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው በ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ አዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በመወዳደር ወደ ፓርላማ ለመግባት ማቀዱን በቃለ ምልልሶች አረጋገጠ፣
§ የአምስት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ፣
§ 1434ኛው የኢድአልፈጥር በዓል በእስልምናእምነት ተከታዮች በተለይበአዲስ አበባ ብሔራዊስታዲየም ሲከበር፣ ፌደራልፖሊስ በዓሉን ለማክበርየተገኙትን በርካታ ሰዎች ላይ እስር እና አካላዊ ጥቃት ፈፀመ፣
§ ሞስኮ በተዘጋጀው የ14ኛው የዓለም አትሌትክስሻምፒዮና ኢትዮጵያ 3ትየወርቅ፣ 3ት የብርእና 4ት የነሃስሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም6ኛ ከአፍሪካ 2ኛሆና አጠናቀቀች፤ ወርቁንያስገኙት ዝነኞቹ የረጅምርቀት ተወዳዳሪዎች ጥሩነሽዲባባ እና መሰረትደፋር እንዲሁም በታሪካችንለመጀመሪያ ጊዜ የሆነውንየ800ሜ ርቀትአሸናፊ መሐመድ አማንናቸው፣
- § የአቡነ ጳውሎስ እና የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሙት ዓመት ለማክበር መንግሥት አረንጓዴ ዘመቻ አደረገ፣ በርካታ ፓርኮችንም በስማቸው ተሰየመላቸው፣
- § ወጣቱ ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ባደረበት ድንገተኛ ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፣
- §
- § ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 26/2005ዓ.ም በአዲስ አበባ ሊያካሂድ ያቀደውን እና ከሦስት ወር በፊት ሲያስተዋቅ እንዲሁም ዝግጅት ሲያካሂድ የከረመበትን ሠላማዊ ሰልፍ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሰልፉ እንዳይካሄድ ከለከለ፣
- § በተለያዩ የእምነት ተቋማት ኅብረት ጠሪነት፤ በመንግሥት ወኪሎችና የኢሕአዴግ አባላት ቀስቃሽነት የሃይማኖት አክራሪነትና ፅንፈኝነትን ለመቃወም በሚል ነሐሴ 26/2005ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሠልፍ ተካሄደ፣
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ኮንጎ ብራዛቪል ላይ ገጥሞ ተጋጣሚውን 2 ለ 1 በመርታት፤ ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቅ አፍሪካን የሚወክሉ 5 ቡድኖች ተለይተው ለሚወጡበት 10 ብሔራዊ ቡድኖች ለሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጥሎ ማለፍ ከገቡት ውስጥ መካተት ቻለ፡፡
2005 ቢደገም አልጠላም!
አዲስ ዓመት – በነተበ ሥርዓት
(ሩት ዳግም)
ጊዚያቶች ክንፍ አውጥተው የሚበሩ ይመስላሉ። 2005 አምና ለመሆን በቅቷል። የተፈጥሮን ህግጋት ጠብቆ በዳመና የጠቆረው ዳመና እየገለጠ፣ አበቦች እየፈኩ መድሪቷ የመስከረም ወር መጥባቱን ብታበስርም፤ በክፉ የወያኔ አገዛዝ ቀንበር ስር ለሚማቅቀው የአገሪትዋ ህዝብ ዛሬም እንጉርጉሮው የሀዘን ነው። የኑሮ ውድነቱ፣ የሰብአዊ መብት ጥስቱ፣ ፍትህ ማጣት እና በመሳሰሉ ስር በሰደዱ ችግሮች እግር ተወርች ተቀፍድዶ ነገን በተስፋ ተሞልቶ አዲስ ዓመት ይጠብቃል ማለት ዘበት ነው። ይልቁንም አዲስ ዓመት ይዞት በሚመጣው የኑሮ ጣጣ የሚቆዝመው ህዝብ ቁጥር እልፍ ነው።
‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የሚባል የወያኔ ዕድሜ ማራዘሚያ የተዘጋጀው እቅድ እንደተወራለት በአምስት ዓመት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ህዝብን የሚያሰልፍ አለመሆኑን ሁሉም ተገንዝቦታል። ይልቁንም የህውሃት ግዙፉ ድርጅት ኤፈርት በያዛቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች አመቻቺነት ጥቂት የወያኔ ባለስልጣናትን በሙስና ፈጣን ባቡር ወደ ሚልኒየር፣ ቢልየነር ተርታ መላውን ህዝብ ደግሞ በድህነት ቀፍድዶ ወደአዘቅት የሚያደርስ ሆኗል። በዚህ አሳዛኝ ህይወት ላይ ለሚገኝ ህዝብ አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ መጠበቅ የቀን ቅዠት ነው። ወትሮስ በዘረኝነት፣ በሙስና በሀገር ክህደት ብል እንደበላው ነጠላ የነተበ መንግስት የአገርን ገበና በምን አቅሙ ይሸፍናል??
በአይነ ህሊና የዘመን አሮጌ ልብስ የደረበውን የዘንድሮ ዓመት መለስ ብላችሁ ብትቃኙት ቅንጣት ያህል አስደሳች ነገር ለማግኘት ይከብዳል። በ2005 ዓ.ም. በወያኔ መንግስት የስልጣን ሽኩቻና ሹም- ሽር ያየለበት፤ እስርና ግድያ በአደባባይ የተፈጸመበት፣ ፍትህ ማጣት ያየለበት፤ በኑሮ ወድነት፣ በመብራት መጥፋትና መምጣት፣ በውሃ መቋረጥ፣ በታክሲ፣ ዘይት፣ የስኳርና የስንዴ በመሳሰሉ ሰልፎች መሽቶ እስኪነጋ ህዝብ የሚደክምበት ተስፋ አስቆራጭ የቀን ጨላማ ነበር። በመንግስት ሚድያ ደግሞ “የታላቁ መሪ” አቶ መለስ ውዳሴ “ውርሳቸውን/ሌጋሲያቸውን” እናስቀጥላለን በሚል የማያባራ የቆሸሸ ፖለቲካ ህዝብን ማሰላቸት ሥራዬ ብለው ከርመውበታል። ይሁንና ይህ ወቅት አልፎ የመለስ እኩይ ተግባር፣ ክህደትና ተዘርዝሮ የማያልቅ ክፉ ተግባር ትውልድ ሁሉ በሚማርበት መልኩ በዚያው በሀገራችን፤ በዚያው ሚድያ የሚነገርበት ዕለት ይመጣል።
አሁን ባለው የጨለመ ድባብ አዲስ አመት ሲመጣ ህዝቡ እንደ ወግ ልማዱ
“ከብረው ይቆዩ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው
ከብረው ይቆዩ ከብረው” የሚል የልጆቹን ዜማ ተቀብሎ እያዜመ ነገን በተስፋ ያልማል ማለት የአብዛኛውን ህዝብ ኑሮና የተጫናበትን መከራ ያለማወቅ ነው።
ይሁንና ይቺን መከራኛ አገር ላይ ተፈናጠው እንዳሻቸው ደንገላሳ ለሚጋልቡዋት የህውሀት ባለስልጣናትና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ግን ሁሌም አዲስ ዓመት፤ ሁሌም በዓል ነው ያቺ ቀን እስክትመጣ . . . በሙስና በዘር ፖለቲካ ውርስ በተባለ አስማታዊ ብልሃት ከባዶ ኪስ ተነስተው በአንድ ሌሊት ከሚልኒየር ተርታ የሚሰለፉ የዘመናችንን ጉዶች ማየት የተለመደ ሆኗል።
ግና በመዲናችን በየመንገዱ ዳር ተገጥግጠው ከሚታዩት በመስተዋት ካሸበረቁት ህንጻዎች ጀርባና በየመንገዱ ዳርና በየጎዳናው ድህነት ጠልፎ እንደ ጉድፍ የጣለውን በርካታ ህዝብ ማየት ያማል። እናም የሀገሪቱን የሁለት ዲጂት ዕድገት ቱልቱላና የሆነውን በማመዛዘን የአዲስ ዓመት ፌሽታ ባይገባው ይደንቃል? እፍረት አልባው መንግስት ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ ተመድባለች እያለ እውን ያልሆነውን ህልም ሊያሳይ ቢሞክርም ዩናትድ ኔሽን ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት በ Multidimensional Poverty Index መሰረት ኢትዮጵያ ከመንግስት አልባዋ ሱማሌ ጭምር ተበልጣ ከመጨረሻው የድሀ አገር ተሰልፋለች። የበለጠችው አገር ኒጀርን ብቻ መሆኑ ነው። “ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም !” እንዲሉ።
በሥራ አጥነት፣ በየተልካሻ ምክንያት ከሥራ በተባረሩ፣ በዘራቸው ሳቢያ በተሰደዱ፣ በሃይማኖታቸውና በፖለቲካ አመላካከታቸው ሳቢያ ለእንግልትና ስቃይ በተዳረጉ በርካታ ቤተሰቦች ባሉበት አገር ደስታን ለማጣጣም እንዴት ህሊና ይቀበላል? ለእውነትና ለህሊናቸው ብቻ ስለቆሙ በአሰቃቂ እስር ቤት ታጉረው ከሚወዱት ቤተሰብ በግፍ የተነጠሉ ወገኖቻችንን አስበልተን ምን አይነት የበዓል ድግስ ይኖረናል??
ሀገራችን ኑሮ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትህ ማጣት እንደ ጎርፍ ጠራርጎ ጎዳና ላይ ካወጣቸው እጅግ በላቀ ሁኔታ ለልመና መውጣት አፍረው በየቤታቸው በችግር አለንጋ የሚገረፉት እጅግ እጅግ በርካታ ናቸው፤ ዛሬ ልጆቻውን በቀን አንዴ እንኩዋን ለመመገብ የማይችሉ ቤተሰቦች የተበራከቱበት ሃገር ሆናለች። ታዲያ ዓለምን ያነጋገረው በስደት በየበረሃውና በአረብ ሀገራት የሚያልቀው ወጣት የሁለት ዲጅት ዕድገት ውጤት ይሆን?
በየቤታቸው በችግር የሚጠበሱትን ወገኖች ካነሳሁ ከጥቂት ወራት በፊት ያጋጠመኝን ልጥቀስ አዲስ አበባ ኡራየል አካባቢ አንዲት አነስተኛ ሱቅ የምፈልገውን ዕቃ በመሸማመት ላይ ነበርኩ፤ እናም ከሁዋላዬ አንዲት በእድሜና በኑሮ ጉስቁልና ወገባቸው የጎበጠ ጠይም እናት ብዙ ደቂቃ መቆማቸው ስለሰቀቀኝ “እናቴ እርሶ ግዙና እኔ እቀጥላለሁ” አልኩዋቸው። ሽቁጥቁጥ በሆነ ትህትና መርቀውኝ ባለሱቁን “ቡና ይኖርሃል?” አሉት
“ቡና አለ! ኪሎ ባለመቶ ሃምሳ፣ ባለምቶ ሃያ ወይም ባለመቶውም ጥሩ ነው . . .” በእጁ እየዘጋገነ ሊያሳየቸው ሞከረ
ዓይናቸው ዓይኖቻችንን የሚሸሹ መሰለኝ፣ ጥቂት አሰቡና “ የአስር ብር አድርግልኝ”
“እማማ አያዋጣኝም…’’
“እንግዲያውስ የሩብ ሩብ ስጠኝ’’ ሀዘን፣ ሸንፈት የኑሮ ድካም በደማቁ ጠይም ፊታቸው ላይ ይነበባል።
“በዚህስ ዘይት ትሸጥልኝ?’’ በፌስታል የያዙትን ትንሽ የዘይት ጠርሙስ አውጥተው እያሳዩት
“እኔ ጋር በችርቻሮ የለኝም። እታች ካለው ሱቅ ይሞክሩ” አላቸው
ተስፋ በቆረጠ መንፈስ “ዘይቱ ቢቀርም ግድ የለም። ብቻ ይቺ ቡና ሱስ ነው ያስቸገረች . . .’’ አሉና ወገባቸው ላይ ክታሰረችውን መቀነት ፈትተው ብሩን ቆጥረው ከፍለው ሄዱ።
በዓይኔ ተከተልኳቸው ይህ የበርካታ የሀገራችን እናቶች ኑሮ መሆኑን ባውቅም፤ ያለፉትን የኑሮ ውጣውረድ ወለል አድርጎ የሚያሳይ ገጽታቸው፤ ሽቁጥቁጥነታቸው ለልመና እጃቸውን ለመዘርጋት ያልተረታ መንፈሳቸው፤ ነገር ግን ድህነት አንገዝግዞ ሊጥላቸው ያቃረበው የተጎዳ አካላቸው ከፊቴ ላይ እየተጋረጠ ፋታ ነሳኝ . . . ለምን አንድ ኪሎ ቡና እንኩዋን ሳልገዛላቸው. . . ቁጭት ያዘኝ፤ ደጋግሜ ራሴን ወቀስኩ፤ አሮጊትዋ ግን ከዓይኔ ርቀዋል። ባለሱቁን መኖሪያ ቤታቸውን ጠየኩት። አልፎ አልፎ ወደ ሱቁ እንደሚመጡ ቤታቸውን ግን እንደማያውቀው ነገረኝ። በሌሎቹ ቀናት ደጋግሜ ባለሱቁን ብጠይቀውም አይቶአቸው እንደማያውቅ ነገረኝ። ለባለሱቁ ይህ ደጋግሞ የሚያየው የህይወት ትዕይንት ስለሆን ቁብ አልሰጠውም።
እንግዲህ “ሁለት ዲጂት…” ይህን መሰል የበርካቶችን ህይወት ያለመዳሰሱ ቀልድ ህሊናን ይኮሰኩሳል? በየመንገዱ በጠኔ በህመም ወድቆ በአደባባይ ያለምንም ረጂ ሊሞት የሚያጣጥር ወገን እንደ ዋዛ ማየት በተለመደበት አገር፤ ከየመንገዱ የበቀሉ ደሃውን በግፍ አፈናቅለው በበቀሉ ህንጻዎች መመዘኛ ዕድገትን መለካት ፌዝ ነው። የለየለት ቧልት ነው። በየመንግስት ትምህርት ቤቱ ደጃፍ ብትቆሙ ርሃብ ጉስቁልና እንደለበሱት ልብስ አመድ ያስመሰላቸው ልጆችን በመቶ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠር ታያላችሁ። ከዚህ ሁሉ የኑሮ ቀዳዳ ጥቂቱን አለመድፈን ደግሞ ሌላ ስቃይ ነው። በአንዲት ትንሽ ብልቃጥ ለምትለካ መጠጥ ብቻ 2 እና 3 ሺህ ብር በመክፈል በየዕለቱ ሸራተን በመሳሰሉ ትላልቅ ሆቴሎች በዘረፉት ገንዘብ የሚምነሸነሹ የሞሉበት አገር መሆኑ ደግሞ የአገሪቷ ሥርአት ለመኮላሸቱ ሌላው ማሳያ ነው። በየኮንፌሽየስ እንደተገለጸው በመጥፎ አስተዳደር ስር በሚገኝ አገር የጥቂቶች ብልጽግና የሚያሳፍር ነው። ሰሞኑን የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ኑሮ ጠንቆች ሲል ባስጠናውና ይፋ ባደርገው መረጃ መሰረት ከሚልዮን የሚልቁ በልመና የሚተዳደሩ አሉ። እውነታው ከዚህም ይከፋል።
ይባስ ብሎ የመጨረሻ በሌለው ድህነት ተውጠን አንድ ቁጥር ዘረኛና አምባገነን ስርአት የተጫነብን ምን ፍርጃ ነው ያሰኛል። ኢትዮጵያን በዘር ፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ከፋፍሎ የህዝቡን አንድነት ለማጥፋት የሚጥረውን አገዛዝ መቃወም ደግሞ “አሸባሪ’’ የሚል ታርጋ አስለጥፎ ዘብጥያ ያስወረውራል። በወያኔ እኩየ ስራዓት የህግ የበላይነት የለም፤ ዲሞክራሲ ተደፍጥጡዋል፤ የደህንነት ዋስትና የለም፤ ነፃ ፕሬስ ተረት ሆኗል፣ የብዙሃን ፓርቲ ያልምንም እፍረት ተገፍትሮል። የሲቪክና ሙያ ማህበራት የማሽመድመዱ ተግባር ተከናውኗል።
ይለቁንም ዘረኞች ግፈኞች፣ ወንጀልኞች፣ አምባገነኖች፣ ሙሰኞች እንዳሻቸው ዛሬም እየፈነጩ፤ በተቃራኒው ፍትህና እኩልነት ለህሊናቸው፣ የሚታገሉና የሚዋረዱበት፣ የሚሰደዱበት የሚታስሩበት አገር መሆኑ ያስቆጫል።
በርግጥ የታፈኑ ብሶት ገንፍሎ የነጻነት ደማቅ ፀሐይ የምናይበት ጊዜ እንደሚመጣ ቅንጣት አልጠራጠርም። ያኔ በርግጥም ክረምቱ ያልፋል፣ ምድሪቱም በነጻነት ጸበል ይለመልማል፤ ሰማያችን ከክፉ የዘረኝነት ዳመና ይጠራል። ከተራራ ተራራ “አበባ አየሆሽ” ዜማ ይናኛል።
“የእማምዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት
የአባብዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት” በርግጥም ትርጉም ይኖረዋል። መልካም ዘመን ያምጣልን። አሜን!!
የሐምሌ ጨረቃ! (ክፍል አንድ) – ከአንዱዓለም አራጌ ዋለ (አንድነት ም/ሊቀመንበር ከቃሊቲ ማጎሪያ)
የሐምሌ ጨረቃ!
ከአንዱዓለም አራጌ ዋለ (አንድነት ም/ሊቀመንበር ከቃሊቲ ማጎሪያ)
ክፍል አንድ
(ሊያነቡት የሚገባ)
ከጉልበተኞች ጠመንጃ የሚወጣ ጥይት ስጋን እንጂ እምነትን ሊገድል እንደማይችለው ሁሉ፣ ከቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ተነጥሎ ቅዝቃዜ በዋጠው ጠባብ ክፍል ውስጥ መታሰርም አካልን እንጂ ምናብን (ህልምን) ሊያስር የሚችልበት ጉልበት የለውም፡፡ ከቶስ እንደምናብ ሜዳውን፣ ተራራውን፣ ቁልቁለቱን፣ ዳገቱን፣ ሸለቆውን፣ ኮረብታውን በሰከንድ ክፍልፋዮች ከብርሃን ፈጥኖ በመምዘግዘግ ያለመዛነፍ ያሰበበት የሚደርስ ምን ኃይል አለ? ከጠባቧ ክፍል ውስጥ ‹‹ድርሻህ›› ተብላ በተሰጠችኝ 90 ሴንቲ ሜትር ላይ ቀሪ ህይወቴን አሳልፍ ዘንድ በግፍ ፍርድ ብታሰርም ዕረፍት ለማያውቀው ምናቤ ገለታ ይድረሰውና ይዞኝ ይከንፋል፤ ወደ ምፈልገው አድርሶ ይመልሰኛል፡፡
አንዳንዴ ከጁፒተር ማዶ ያሉ ተንሳፋፊ ዓለማቶችን ቢያስቃኘኝም፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን በሀገሬ ሰማይ ስር በጥቅጥቅ ደመና ላይ አንሳፎ ታላላቅ ወንዞቿን፣ ሃይቆቿን፣ የተንጣለሉ መስኮቿንና ሰማይ ጥግ የሚደርሱ ተራሮቿን በመንፈስ ያስጐበኘኛል፡፡ በተራሮቿ ግርጌና በመስኮቿ እምብርት ላይ ችምችም ብለው የተሰሩ ጐጆ ቤቶችንና በውስጣቸው ለሺ ዓመታት በፍቅር የኖሩ ደሃ ኢትዮጵያውያንን እንደጓደኞቻቸው ከሚመለከቷቸው የቤት እንስሳቶቻቸው ጋ ይታዩኛል፡፡ በየከተሞቹ ከድህነትና ከአፈና ጋር ግብግብ የገጠሙ፣ ከድህነትና ከፖለቲካ አፈና ነፃ ለማውጣት በዓለም ዙሪያ የተበተኑ ወገኖቼን ሳይቀር በአይነ- ህሊና ያስጎበኘኛል፡፡ አንዳንዴ ውሸትን እንደብልህነት፣ አፈናን እንደ አገዛዝ ስልት የወሰዱ አሳሪ ወንድሞቼና እህቶቼ የህሊና ጓዳ ውስጥ ይዞኝ ዘው ይልና ያረበበውን እብሪት፣ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ እርስ በእርስ የሚላተሙ ሃሳቦቻቸውን ፍልሚያ… ያሳየኛል፡፡
እነዚህ ምን አይነት ኢትዮጵያውያን? ምን አይነትስ ወላጆች ናቸው? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ የምናብ ፈረስ ጋልቤ የምጐበኘው የዚህን ዘመን ክንዋኔ ብቻ ሳይሆን የተደራረበውን የዘመን ጉም እየጠራረጉ ያለፉ አያሌ ዘመናትን ወደ ኋላ አስጉዞ ያሳየኛል፡፡ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመናት፡- አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጐንደርን፣ ያልዘመርንለትን የገዳ ዴሞክራሲ ስርዓትንና ሌሎች የጥንት ስልጣኔዎችን በብላሽ ያስኮመኩመኛል፡፡ የኢትዮጵያን የዳር ድንበር ነፃነት ለማስከበር አባቶቻችን ያደረጓቸውን የጀግንነት ውሎዎች በተለይም የጀግንነታችን ማማና የጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን የአድዋን ጦርነት ደጋግሜ አየዋለሁ፡፡ አድዋና መሰል የጀግንነት ማማዎች ላይ ቆሜ ኢትዮጵያውያን በየቀያቸውና በየዘመኑ ሰብዓዊ ክብራቸው ተረግጦ፣ በጭቆና አዘቅት ውስጥ ወድቀው ሲዘቅጡ ይታዩኛል፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ልዕልናቸውንና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ ያደረጉትን ትግል ያሳየኝና መንፈሴን ያበረታዋል፡፡
ታሪክ እንደሚዘክረው ከኋላ ቀሩ የፊውዳል አገዛዝ ነፃ ለመውጣት (በትክክል ወዴት ያመራ እንደነበር መናገር ባይቻልም) የመጀመሪያ አብሪ ጥይት የተተኮሰችው የ1953ቱ የእነ ጄኔራል መንግስቱና ገርማሜ ንዋይን የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ በተደረገበት ዕለት ነው፤ አቤት! እርሱን ተከትሎ የተሻለ ንቃት ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ‹‹ሕዝባዊ መንግስት›› ለመመስረት ያሳየው እንቅስቃሴ! የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለዓመታት የሞቱለት፣ የተጋዙለት፣ የተደበደቡለት፣ የተሰደዱለት… ሰላማዊ ትግል እና ያነሷቸው ጥያቄዎች ጆሮዬ ላይ ደጋግመው አስተጋብተዋል፡፡ በወቅቱ የዘውዳዊ ስርዓት ገበሬዎች፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ አሰምተው፣ በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲገቡ የነበረውን ትዕግስት አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ባነፃፀርኩት ቁጥር እንደ አዲስ እደመምበታለሁ፡፡ ንጉሳዊውን ስርዓት በመቃወም ተደጋጋሚ ሰልፎች ላይ ይሳተፉ የነበሩት እና ዛሬ ለድል የበቁት የቀድሞዎቹ ተማሪዎች፣ የአሁኖቹ ገዥዎች የትምህርት ነፃነትን ከመርገጣቸውም በላይ ቅሬታ በተነሳ ቁጥር የተማሪዎች መኝታ ቤት ድረስ በመዝለቅ ደም ማፍሰሳቸውን ሳስብ፤ ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ንፁሃን ላይ ከውሃ ይልቅ ጥይት ማዝነብ የሚቀናቸውና ተቃዋሚዎቻቸውን በውሸት ድሪቶ ዘብጥያ የሚያወርዱ አምባገነኖች መሆናቸውን ሳስብ የማይፈታ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡
ዘውዳዊ ስርዓቱን የተቃወሙ ሰዎች ከነገስታቱ በላይ ከዘመን ጋር የማይዘምኑ፣ ከአፈሙዝ ጋር የተጋቡ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ የምናብ ፈረሴ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ዓለም በመጣሁበት ሰሞን ከነበረው የጭቆና አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አልመው ወደ ከፋ የአምባገነንነት ገደል የወደቁበትን የእልቂትና የዋይታ አብዮት እየደጋገመ ያስቃኘኛል፡፡ በተፋላሚዎች መካከል የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ባይኖርም አፈ-ሙዝን በአፈ-ሙዝ ለማሸነፍ የተደረገው ደም መፋሰስና ወንድም በወንድሙ አስከሬን ላይ ቆሞ የፎከረበት የእርስ በርስ ጦርነትም ሌላኛው እረፍት የሚነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ የግፍ ቋት የነበረውን ደርግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አሸንፎ በድል አድራጊነት ወደ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሲገባ ሌላ የግፍ ቋት ይሆናል ብለው ያልጠበቁ አያሌዎች ነበሩ፡፡ ረጅሙ የመከራ ሌሊት መልሶ ላይጨልም ነግቷል ብለው ለተሻለ ነገር የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ትንሽ የሚባል አልነበረም፡፡ በአሁኑ አገዛዝ ከቀደሙት ህገ-መንግስታት የተሻለ ህገ-መንግስት ቢፀድቅም ቃልና ተግባር ሳይገናኙ ይኸው 22 ዓመታት አልፈዋል፡፡
እነሆም የሌላ ዙር የአፈና ሰለባ ሆኜ ወደምማቅቅበት እስር ቤት የምናቤ ፈረስ መልሶ አደረሰኝ፡፡ ሌላ ዙር እስር፣ ሌላ ዙር አፈና፣ ሌላ ዙር የህፃናት ለቅሶ፣ ሌላ ዙር የወላጆች ሰቆቃ፣ ሌላ ዙር ውርደት፣ ሌላ ዙር የአጤዎች ቀረርቶ፣ ሌላ ዙር የህዝብ እንባ፣ ሌላ ዙር… ባለንበት መርገጥ ቀጥለናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የከበረና ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የዳር ድንበር ነፃነቱን ማስከበር ቢችልም በአገሩ ሰብዓዊ ክብሩንና ነፃነቱን ከራሱ ገዢዎች አስከብሮ መኖር የቻለበት ዘመን የለም፡፡ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለው የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግል በድቅድቁና ዝናባማው የሐምሌ ጨለማ የምትወጣውን ‹‹ጨረቃ›› ይመስላል፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌለበት የገጠሩ የሀገራችን ክፍል የልጅነቱን የመጀመሪያ ዓመታት እንደእኔ ላሳለፈና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትግል በአንክሮ ለተከታተለ ሁሉ ስርዓቱና ጨረቃዋ የአንድ አባት ልጆች ይሆኑበታል፡፡ የሐምሌ ወር ጨለማ ጥቁር ነው፡፡ እንደግድግዳ ፊት ለፊት ቆሞ ነፍስን ያስጨንቃል፡፡ ጫፉ የማይታይ የጥላሸት ቁልል ይመስላል፡፡ ከጨለማው መደቅደቅ የተነሳ በቅርብ እርቀት ያለ ቁስን እንኳን ለመለየት የሚያስችል ብርሃን የለም፡፡ ወደሰማይ ለሚያንጋጥጥም በጥቁር የደመና ከል የተጋረደ ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን ህልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት የሐምሌ ወርን እየጠበቀች እየደጋገመች የምትወጣው ጨረቃም ወቅቷን ጠብቃ መውጣቷን አላቋረጠችም፡፡ ከአንድ ጥቁር የደመና ኮረብታ ወደሌላው ስትወረወር ለቅፅበት ትንሽ ብርሃን ብትፈነጥቅም ምድሩን እንደቡልኮ የሸፈነውን ድቅድቁን ጨለማ ሰንጥቆ ለማለፍ የሚችል የብርሃን ፍንጣቂ በመልቀቅ የጨለማውን ሀይል መግፈፍ የሚችል አቅም የላትም፡፡ እንዲያውም በብርሃን ጅረት የተሞላው መላ አካሏ በጨለማው ፅልመት ጠልሽቶና ከጨለማው ጋር ተመሳስሎ ይታያል፡፡ የሐምሌ ጨረቃ ወይ ድቅድቁን አትገፋ፣ ወይም የሐምሌን ወር አትዘል በየዘመኑ፣ በየአመቱ ፍሬ አልባ ዑደቷን ቀጥላለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልም እንዲሁ፡፡ እንደ ሐምሌ ጨረቃ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገሩን የህላዌ እድሜ ያህል ከጭቆናው ሌሊት ጋር በየወቅቱ ግብግብ ይገጥማል፡፡ በተለይም ከ1953 ዓ.ም ወዲህ ያሉት 50 ዓመታት ህዝባችን ከአብራኩ ከወጡ አምባገነን ገዥዎች መዳፍ ነፃ ለመውጣት ተደጋጋሚ ትግል አድርጓል፡ ፡ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሰብዓዊ ልዕልናው ባለቤት ለመሆን የሚያስችለውን የተጠና፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የሚመራና ህዝብ የራሱ ያደረገው የፀና ሰላማዊ ትግል በማድረግ ለውጤት አልበቃም፡፡
ለምን? በረጅሙ የሀገራችን ታሪክ የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበርን የመሳሰሉ ገንቢ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ፍልስፍናዎች ማዳበር የመቻላችንን ያህል፤ በሌላ መልኩም አሉታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ፍልስፍናዎች እንዳዳበርን መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ፖለቲካዊ መስተጋብራችን የተፋለሰ እንዲሆን አስተዋፆ አድርገዋል፡፡ በተለይም ከዘመነ-መሳፍንት በኋላ ያለውና በዚያ ዘመን የፖለቲካ ብሒል የተቃኘው ፖለቲካዊ ፍልስፍናችን ከምህዋሩ የወጣ ነው፡፡ በአመዛኙ በፍርሃት፣ በአድርባይነትና በጊዜያዊ ጥቅም የተለወሰ ፍርሃት፣ የማያምኑበትን መናገር፣ በአርምሞ ማሳለፍ፣ ያልሆነውን ሁነን መታየት፣ ነገሮችን በሚስጥር መያዝ፣ ተጠራጣሪነትና በውል ባልታሸ ሁኔታ እራስን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ማራመድ የመሳሰሉትን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል፡፡ በየዘመኑ የሚነሱ አምባገነኖችና የጎበዝ አለቆች ጥላ ስር ለመጠለል መሞከር እነርሱን አይነኬ አድርጐ መቁጠር እራስን ፍፁም አቅመ-ቢስ አድርጐ መረዳት ለገዥዎች ማሸርገድና ቅዳሴ-ማህሌት መቆም አያሌ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ እንደ ፖለቲካ-ጥበብ የሚቆጥሩት አካሄድ ነው፡፡ ይህም ሁሉ በጥልቅ አስተሳሰብና ከዚያም በሚመነጭ እምነት ላይ ቢመሰረት ችግር አልነበረውም፡፡ የተሳሳተ እምነት በማንገብ የጨለማ አገዛዞችን የነፃነት ንጋት ናቸው ብለው የሚዘምሩ፤ በረሃብ ስንሞት በቁንጣን ነው ብለው ሊያሳምኑን የሚዳዳቸው፤ የአገዛዞች ዋልታና ማገር የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በየዘመኑ አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡
ከዘመናት የአፈና አገዛዝ ነፃ ልንወጣ ይገባናል ብለን የምንታገል ወገኖች እንደመኖራችን ሁሉ፤ አገዛዙ የፀሐይ መውጫ ምኩራብ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች እምነታቸውን ያራምዱ ዘንድ መብታቸው ነው፡፡ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ ጨለማው በእርግጥም ጨለማ መሆኑን አይኖቻቸውን ገልጠው እንዲያዩና እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ሞታችን ከጨለማው ጋር ነው ብለው በጨለማው አካልነታቸው መቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ ታግሎ ማሸነፍና እነርሱም ከጨለማ ነፃ እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ ከባዱ የቤት ስራና እስከአሁንም ነፃነት ከእኛ እንዲርቅ ትልቁን አስተዋፆ እያበረከተ ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ‹‹መሃል ሰፋሪው›‹› ኢትዮጵያዊ ይመስለኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር በፖለቲካ ትግል ባሳለፍኳቸው ጥቂት ዓመታት ከባዱ ፈተና የገጠመኝ ከቤተሰቤ፣ ከወዳጆቼና ከቅርብ ጓደኞቼ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እነዚህ ወገኖች ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ ከአገዛዙ ጋር ግብግብ ከመግጠም ይልቅ አንገቴን ደፍቼ ልጆቼን እንዳሳድግ ምክራቸውን በተደጋጋሚ ለግሰውኛል፡ ፡ ለነገሩ ትዳር ባልያዝኩበት፣ ልጆች ባልነበሩኝ ወቅትም ‹‹አርፈህ ተቀመጥ!›› የሚለው ምክራቸው አልተለየኝም ነበር፡፡ ትግል ውስጥ እንዳልገባ የሚሰጡኝ ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ በደም መፋሰስና በሸፍጥ የተሞላ መሆኑ አንደኛው ሲሆን በተጨማሪም ከኢኮኖሚ አዋጭነት አንፃር ፖለቲካ ፈፅሞ የማይመከር መሆኑን ያስረዱኛል፡፡ በመሆኑም አንገቴን ደፍቼ፣ ገዥዎች ወደአጋዙኝ ተግዤ እንድኖር፤ ልጆቼንም እንዳሳድግ ምክራቸውን ለግሰውኝ ነበር፡፡ አሁን እንኳን በእስር ላይ እያለሁ እንደሳይቤሪያ ብርድ አጥንትን ሰብሮ የሚገባና ነፍስን የሚወጋ ምክራቸውን ይልኩልኛል፡፡ ‹‹ነግረነው አልሰማንም››፣ ‹‹ህፃናት ልጆቹን ያለአባት ትቶ እንዴት ይታሰራል?›› ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከመበሳጨታቸው የተነሳ የመጐብኘት መብቴ ቢከበር እንኳን ሊጐበኙኝ እንደማይፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ወንጀልሰርቼ እንዳልታሰርኩ፣ ለመስራትም እንደማላስብና ሰላማዊ የትግል ስልትን የሃይማኖት ያህል እንደማምንበት ወዳጆቼም ሆኑ አሳሪዎቼ እኔ የማውቀውን ያህል ያውቃሉ ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ያም ሆኖ ግን ወዳጆቼ ስርየት እንደሌለው ሃጢያት፣ የአገዛዙ ዋናዎችም የሰማይስባሪ እንደሚያክል ወንጀል የቆጠሩት የተቃውሞ ፖለቲካ ጐራ መቀላቀሌን፣ በሀገሬ አንገቴን ቀና አድርጌ በመራመዴና የማምንበትን በቀጥታ በመናገሬ ነው፡፡ አገዛዙም ይኽን አይነት በፍርሃት የተሸበበ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ይፈልጋል፤ ወዳጆቼም አገዛዙ በግፍ ስላሰረኝ የነቢይነት ደረጃቸውን በመደመምያስባሉ፤ እርስ በእርሳቸው ይመጋገባሉ፡፡ የትችት ጦራቸውን እስር ቤት ድረስ የሚወረውሩት አብዛኞቹ ጓደኞቼ በታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የተማሩና የሚያስተምሩ፣ በመደበኛ ትምህርት ልህቀታቸው በሊቀ- ጠበብትነት ጐራ የሚሰለፉና ይህች ደሀ አገር ከውስን ጥሪቷ ቆንጥራ ያስተማረቻቸው ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ ዛሬ ወዳጆቼ ያሉት ደርሶብኛል፤ ትንቢታቸው ሰምሯል፡፡ አዎ! ልጆቼ በድንገት ከቤት ወጥቶ እስከአሁን ወደቤት ስላልተመለሰው አባታቸው በህፃንነት የአእምሮ ጓዳቸው ውስጥ እያንሰላሰሉና እየተጐዱ መሆኑን በሚገባ እረዳለሁ፡፡ በተለይ ልክ የታሰርኩ እለት የትምህርት ቤትን ደጃፍ የረገጠው የልጄ የሩህ ጥያቄዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ ‹‹ማሚ፣ እኔ አባት የለኝም እንዴ?››፣ ‹‹አባባ መቼ ነው ቤት የሚመጣው?››፣ ‹‹የአንተ ስራ መቼ ነው የሚያልቀው?›› የሚሉ ናፍቆት ያንገበገባቸውን ጥያቄዎች ያነሳል፡፡
እኔ የምከፍለው ዋጋ ይቅርና ልጆቼም በውል በማይረዱት ነገር ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን በጥሞና እገነዘባለሁ፡፡ ቀድሞውንም ያልጠበኩትም አልነበረም የሆነው፡፡ ግና! በልጆቼ ሰብዕና ላይ የከፋ ስብራት እንዳይደርስ እውነተኛ ፈራጅ ወደሆነው ፈጣሪ ከመፀለይ በቀር ምን ማድረግ ይቻለኛል? ይህችን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለው በእስር ቤት ነው፤ ይኸው አሁን ደግሞ ባልጠኑ እግሮቹ፣ ክፉ ደግ ባለየ ህሊናው ከሚያፈቅረው አባቱ ተለይቶ በባዕድ ምድር የፖለቲካ ስደተኛ ሆኖ የሚንከራተተው የናፍቆት እስክንድር ነጋ ህይወት ለዚህ የበቃው አባቱ እንደኔ የወዳጆቹን የአርምሞ ጥያቄ ባለመቀበሉ ጭምር ነው፡፡ አባታቸውን ተመላልሰው መጠየቅ በማይችሉበት እርቀት ላይ የታሰረባቸው የናትናኤል መኮንን ልጆች እንባም ሰብዓዊ ፍጡርን በተለይም የወላጆችን ልብ ምንኛ እንደሚሰብር ግልፅ ነው፡፡ ከሚያስተምርበት አዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከግቢ ውጭ እንደሚፈለግ በስልክ ሲነገረው የጠመኔውን ብናኝ ከእጁ ላይ አራግፎ የወጣው የኦሮሞ ፌዴራሊስ ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ ‹‹የኦነግ አባልና የፌደራላዊ አገዛዙን በኃይል ማስገንጠል አሲረሀል›› በሚል ክስ ተፈርዶበት ከህፃናት ልጆቹ ተለይቶ በዝዋይ እስር ቤት የግፉን ፅዋ እየተጎነጨ ነው፡፡ በእርግጥ አቶ በቀለም እንደ እኛ አርፎ ልጆቹን እንዲያሳድግ ተነግሮት ነበር፡፡ ሌሎች አያሌ ኢትዮጵያውያንና ልጆቻቸውም ተመሳሳይ የመከራ ህይወት እየገፋ ይገኛሉ፡፡ ልጆቻችንና የትዳር አጋሮቻችን እየከፈሉ ያሉት ዋጋ እኛ በእስር ቤት ከምንከፍለው የከፋ ይመስለኛል፡፡
ለጓደኞቼና ለወዳጆቼ የማነሳላቸው ጥያቄዎች ይኖሩኛል፡፡ ነፃነት አልቦ ህይወት ምን ምን ይላል? ለመሆኑ ነፃነትን በገዥዎች ችሮታ የተጐናፀፈው የየትኛው ሀገር ህዝብ ነው? በየትኛው ክ/ዘመን ይሆን? …አባቶቻችን ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ዘመድ አዝማዶቻቸውን ከኋላቸው ጥለው ወደ አድዋ መዝመታቸው ስህተት ነበር እያላችሁን ይሆን? ቴዎድሮስ በመቅደላ፣ ዮሐንስ በመተማ ለሀገር ክብር መውደቃቸው ትርጉም የለሽ ነበር ማለት ነው? ሌሎች አባቶቻችንስ በጉራ፣ በጉንደት፣ በማይጨው እና በአያሌ የጦር አውድማዎች ለሀገር ክብር እንደወጡ ሲቀሩ የሚናፍቋቸው ሚስቶችና የሚሳሱላቸው ህፃናት ልጆች ያልነበሯቸው ይመስሏችኋል? አሉላ አባ ነጋ እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ ለሀገሩ ዳር ድንበር አጥር ሆኖ ጣሊያንና ግብፅን በማስጨነቅ ዛሬ የምንኮፈስበትን ታሪክ ማጐናፀፉ ስህተት ነበር እያላችሁ ይሆን? የእነ በላይ ዘለቀ፣ የእነ አብዲሳ አጋ፣ የእነዘርአይ ደረሰ፣ የእነ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ የእነ አቡነ ጴጥሮስና የሌሎችም ስመ-ጥር ጀግኖቻችን ውሎ በከንቱ ጀብደኝነትና ግብታዊነት የተሞላ ነበር ማለት ነው? እነዚህ ጀግኖች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ክብር ለማስጠበቅ ከቀያቸው ርቀው ሲጓዙ ሞትን ከፊት ለፊታቸው እያዩት የቆሙለት እውነት አመዝኖባቸው እንደነበር ዘንግታችሁት ይሆን? አባቶቻችን በየተራራውና ኮረብታው ስለሀገር ክብር ባይቀበሩ ኖሮ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማግኘት የምንችል ይመስላችኋል? ወይስ የዳር ድንበር ነፃነት ከተከበረ፣ ዜጐች በጭቆና ቀንበር ቢማቅቁ ምንም ክፋት የለውም እያላችሁ ነው? ወይስ ጭቆና ከአብራካችን በወጡ ሰዎች እስከሆነ ድረስ እንደክብር ይቆጠራል እያላችሁ ነው? የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የተከፈለው ዋጋ ጠጋ ብለን ስናየው የህዝብን መሰረታዊ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያነሳ ሳታችሁት? አባቶቻችን ለሀገር ነፃነት የከፈሉት ዋጋ ተገቢ አልነበረም ካላላችሁ በስተቀር ለዜጐች ሉዓላዊነትና ለዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መታገል ስህተት ሆኖ የሚገኘው በምን ቀመር ነው? በዩኒቨርስቲዎች ስለ- ሰብዓዊ ፍጡር ልዕልና የምትማሯቸውና የምታስተምሯቸው ትምህርቶች ‹ነፃነት›ን በተመለከተ ምን ነበር ያሏችሁ? ወይስ ዲሞክራሲና ነፃነት ለእኛ ሀገር አይሰራም እያላችሁ ነው? የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነውን የአድዋን ድል ያስመዘገቡ አባቶች ልጆች ሉዓላዊነታችን ከገዥዎቻችን መዳፍ ነጥቀን ማስከበር ካልቻልን ‹የእሳት ልጅ አመድ› መሆን አይመስላችሁም? ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን ቀንበር እንዲሰብሩ የረዳቻቸው የአፍሪካ አገሮች በዴሞክራሲ ጐዳና በርቀት ጥለውን ሲተሙ፤ የእኛ በጭቆና አረንቋ ውስጥ መዳከር እንዴት ቁጭት አይፈጥርባችሁም? ወይስ የእናንተ ድርሻ ትችትና ታዛቢነት ብቻ ነው? እነዚህ ከፍ ብዬ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች ለምወዳቸው ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆን ‹‹የመሃል-ሰፋሪነት›› ሚና ለመረጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ያሉ ሸንኮፎችን አስቀድመን መግረዝ ካልቻልን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እንደ ሐምሌዋ ጨረቃ አሁንም በከንቱ ብቅ ጥልቅ ከማለት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡ ፡ ምናልባት የሀሳባችሁ ማጠንጠኛ ባለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት ማሳካት ያልተቻለው እንዴት አሁን ይቻላል? የሚል ከሆነ ይኸንን ጥያቄ ማንሳት፣ ለጥያቄውም መልስ መስጠትና በመልሱም ላይ ተመስርቶ በእውነተኛ ነፃነትና ህዝባዊ ልዕልና ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መታገል እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ የተወሰኑ ጥያቄዎችን አክዬ ላንሣ፡ ፡ ሁሉም የግል ጥቅሙንና የአብራኩን ክፋዮች ብቻ በሚያስቡባት ሀገር እንዴት ህዝብ ከአገዛዝ ነፃ ሊሆን ይችላል? በየማጀቱ አገዛዙን በመርገም ነፃ መውጣት ቢቻል ኑሮ ከረጅም ዘመናት በፊት ነፃ አንወጣም ነበር ትላላችሁ? አባቶቻችን ለነፃነት መስዋዕት መሆናቸው ትክክል ነበር የምትሉ ከሆነ የስብዕና መሰረትና የነፃነቶች ሁሉ የበላይ ለሆነው የሰብዓዊ መብት መታገል ትክክል የማይሆንበት አሳማኝ ምክንያት ምንድን ነው? ከገዥዎች መዳፍ ለመውጣት አሳማኝ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ይኽን ከገዥዎች መዳፍ ለመውጣት የሚደረግን ትግል እንዳላየን አይተን ብናልፍ ለሁላችንም የማይቀረው ሞትን ተጋፍጠን ወደመቃብር ስንወርድ በምን አይነት ክብርና የህሊና እረፍት ማሸለብ እንችል ይሆን? የዘወትር ህልማችን ሰብዓዊ ልዕልናችን ተጠብቆ የምንኖርበትንና ልጆቻችን የማያፍሩበትን ሀገር ማውረስ ሆኖ ሳለ የአገዛዙን የጭቆና አርጩሜ በመፍራት ከእምነታችን ውጭ የሆኑ ተግባሮችን ስንፈፅም የምንበጀው እስከመቼ ነው? ለዘመናት እላያችን ላይ ቤት የሰራብንን የጭቆና ቀንበር መስበር በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያልተከወነ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለል የመጣ የቤት ስራ ነው፡፡ በውዝፍ ያደረ ቁምነገር ከቅርሶቻችን ሁሉ የገዘፈና የታሪካችን ፈርጥና የማንነታችንም መደምደሚያ ነው፡፡ በዚህ የሰብዓዊ ልዕልና ጉዳይ ላይ መታገል ሰው የመሆንና ያለመሆንን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ በነፃነት አለመታገል የቤት ስራውን ለልጆቻችን ወዝፎ ማሳደር በጭቆና ቀንበር ለመገዛት ህዝበ ውሳኔ የመስጠት ያህል ይቆጠራል፡፡ በሌላ በኩል ነፃ ለመውጣት እንደቀድሞ ነፃ አውጭ አበጋዞችን መጠበቅ አይገባንም፡፡ ይኽን የምናደርግ ከሆነ ሰማያችን በጭቆና ደመና እንደተሸፈነ ይቀጥላል፡፡ ጥቂቶችን አንጋጠን ስንጠብቅ በውስጣችን ያለውን ትልቅ የነፃነት ሃይል እንዳናይ ግርዶሽ ይሆንብናል፡፡
ይኽን በመሰለው የነፃነት ትግል የሚጀምረው የራስን የከረመና የተሳሳተ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተሳሰብ ከመሞገት ነው፡፡ ከዚያም ከፍ ሲል እንደ ፖለቲካ ባህልና የብልህነት ቁንጮ በመውሰድ ለህፃናት ልጆቻችን ሳይቀር በምክር መልክ የምንለግሳቸው ልዩ ልዩ ያልተሰለቀቁ አሉታዊ አስተሳሰቦችን በቅድሚያ ታግሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ስለሁሉም ፤ሁሉም ስለእያንዳንዱ ግድ በማይሰጠው ሀገር ውስጥ አምባገነኖች የሚዘውሯቸው አገዛዞች መኖራቸው የግድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ስለነፃነት ክብርነት ለማንም ማስረዳት እምብዛም አይጠበቅብንም፡፡ ነፃነት እንደ እንጉዳይ በየዛፉ ስር ያለትልቅ መስዋዕትነት በቅሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ ይኸንን የነፃነትን ውድነት ስንረዳ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር እንደዘመቱት አባቶቻችን ሁሉ ያለነፃነት ከመኖር ይልቅ ህፃናት ልጆቻችን ጥለን፣ ከሞቀ ቤታችን ወጥተን በእስር ቤት የሲሚንቶ ወለል ላይ መጣልን እንመርጣለን፡፡ በነገራችን ላይ ደጋግሜ ከምጠቅሳቸው ጀግኖች ጋር እራሴን እያወዳደርኩ አለመሆኑን አንባቢዎች ልብ እንድትሉልኝ እወዳለሁ፡፡ በታሪክ ኮረብቶች ላይ ከድንቅ የጀግንነት ውሎዎቻቸው ጋር ከፍ ብለው የሚታዩ ጀግኖች ጫፍ የሚደርስ አንዳች ስራ እንዳልሰራሁ ጥሩ አድርጌ እገነዘባለሁ፡፡ አላማዬ የዳር ድንበርን ሉዓላዊነት ከሰብዓዊ ሉዓላዊነት ጋር ማነፃፀር ነው፡፡
ሌላው የአገር ውስጥ ገዥዎችንን እንዴት ከውጭ ሀገር ወራዎች ጋር ያነፃፅራል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሁለቱም የዘመቱት በነፃነታችንና ሰብዓዊ ክብራችን ላይ ነው፡፡ የነፃነት ትርጉም ከሀገር ልጅነትም በላይ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል መንገድ ስንጓዝ ትግላችን ጨቋኝ ወንድሞቻችን ወደልባቸው እንዲመለሱና ሁላችንም በነፃነት የምንኖርባትን የጋራ ሀገር እውን እንድትሆን ከማድረግ ጋር ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ እንዲታመሙና እንዲሞቱ አይደለም ፡፡ በእኛና በልጆቻችን ላይ እያደረሱት ያለው በደል በእነርሱም ላይ እንዲደርስ ፈፅሞ የምንመኘው ነገር አይደለም፡፡ ነ ፃነትን ከውጭ ሀገር ወራሪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ጨቋኝ መጠበቅ መቼም በይደር የሚያዝ ተግባር አይደለም፡፡ ስለሁላችን ነፃነትና ሉዓላዊነት የተዘረጋ የተማፅኖ ቃል እንጂ፡፡ በሀሰት ‹‹አሸባሪ›› ተብለን ዘብጥያ ብንወርድም ትግሉን ከመቀጠል ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ነፃነትን መጠየቅና መታገል ነፃነቱን የተጠማ የነፃነት ታጋይ ሁሉ ድርሻ መሆን ይኖርበታል፤ ይሁንና የናፈቃችኋትን ነፃነት አታገኟትም ብለው ወህኒ መወርወር የአፋኞች የአፈና ተግባር ቢሆንም መንበርከክ ለከፋ መከራ፣ ለበረታ ጭቆና ከማገለጥ ውጪ ትርፍ አልባ ነው፡፡ የአሁኖቹ ገዥዎች እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የተሳሳተ የፖለቲካ ባህላችን ያበቀላቸው መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችን ካልተቀየረ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ሌሎች አምባገነኖችንም ማብቀሉን ይቀጥላል፡፡
በአምስት አመት ውስጥ ማዕከላዊ እስር ቤት ሁለት ጊዜ ስታሰር፤ ሃላፊዎች ተለዋውጠው ባገኛቸውም የሁለቱም ዋና ኃላፊዎች ቃልና ተግባር ግን ትንሽ እንኳ ልዩነት አልነበረውም፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም እንዳገኙኝ የጠየቁኝ አንድ አይነት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ወንድ ከሆንክ ለምን ጫካ አትገባም?›› የሚል፡፡ ወንድነት ማለት አፈ-ሙዝን፤ በማይናወጥ የፍቅርና የወንድማማችነት መንገድ መጋፈጥ፤ ተጋፍጦም ሳይገሉ መሞት ነው ወይንስ በራሳችን ጥላ ሳይቀር እየደነበርን ንፁሃንን መግደል? የሚገርመው እኮ ለአፈ-ሙዝ ፍልሚያ የጥሪ ካርድ የሚበትኑት ወገኖች የደሃ ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾችን ደም ለማፍሰስ እንጂ እነርሱማ ከመኪና ተደግፈው ለመውረድ ምንም የማይቀራቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ በተለይም የአገዛዙ ዋነኛ ሰዎች ይችን ሀገር ለሁላችን ወደሚበጅ ንጋት ይዘዋት ለመውጣት እድሉን ለዓመታት ቢያገኙም ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ይልቅስ እብሪት የሁለንተናቸው ማጠንጠኛ ምህዋር ሆኖአል፡፡ አንዳንዶቹን በጨረፍታ በማየት ለወንድማማችነትና የኢትዮጵያን የባጁ ችግሮች ለመፍታት በጐ አስተዋፆ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፣ ሕዝብን እንኳን ባይፈሩ ፈጣሪን ይፈሩ ይሆናል ብለን ተስፋ ብናደርግም ሁለቱንም እንደማይፈሩና የኢህአዴግ ዋና ሰዎች መለያ የሆነውን እብሪትና ሃኬት የሙጥኝ ብለው መንጐድ ቀጥለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ አገዛዞች ከዚህ የተለየ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ይኸኛው አገዛዝ ከቀድሞዎቹ ለመለየት የሚሞክረው በእውነት ላይ ያልተመሰረተ የፕሮፓጋንዳ ደመራ በማቀጣጠል ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳ ደመራው ህዝቡንም ሆነ አገዛዙን በብርሃን እንዲመላለስ አላደረገውም፡፡ ሊያደርገውም አይችልም፡፡ አገዛዙም ሆነ ህዝቡ ከፍርሃትና ከጨለማ ጉዞ ነፃ ሊወጣ የሚችለው የእውነት ችቦ ለኩሶ ከዚያም በሚገኘው ብርሃን ዙሪያ ተሰባስቦ መወያየት ሲቻል ነው፡፡ ለዜጐች ሉዓላዊነት ክብር የሚሰጥ አገዛዝ ቢኖር የፕሮፓጋንዳ ደመራ አቀጣጥሎ በዙሪያው መጨፈር ባላስፈለገ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተግባር ከቃላት በላይ ይናገራልና፡፡ የአገዛዙን አምባገነናዊ ባህሪዎችና ተግባሮች በመተንተን ከዚህ በላይ ጊዜ ልናጠፋ አይገባንም፡፡ ምንስ የማይታወቅ ነገር አለ? እንኳን የአፈናው ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ቀርቶ ዓለምም በቅጡ ተረድቶታል፡፡ አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ የሚገዛ ቢሆን ለመቃወም ከቤታችን መውጣት ባላስፈለገን ነበር፡፡
ትልቁ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ከ50 ዓመታት በላይ የአገዛዝ ስርዓትን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ለማስወገድ የተደረገው ጥረት፣ የተከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እንዴት እስካሁን ለፍሬ ሊበቃ አልቻለም? የሚለው ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ አሁን ቢያንስ ወደተሻለ ምዕራፍ ትግሉን ለማሸጋገር አልቻሉም? እስከ አሁን በተደራጁ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ ከመታገል ይልቅ በተለየና የራሳችን በሆነ መንገድ አስተዋፆ እናበረክታለን ብለን በተለያየ መስክ ተሰልፈን የምንገኝ ሰዎችም ምን ያህል አስተዋፆ አበረከትን? ብለን ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ጊዜው በተግባር የማይደገፍና የተጠጋገኑ ምክንያቶችን በመደርደር ብቻ ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የአፈናው ሰለባዎች መሆናችንን አለም በቅጡ ተረድቶታል፡፡ አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ የሚገዛ፣ የህግ የበላይነትን የሚያከበር ቢሆን ኖሮ ለመቃወም ከቤታችን መውጣት ባላስፈለገን ነበር፡፡ ትልቁ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ከ50 ዓመታት በላይ የአገዛዝ ስርዓትን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ለማስወገድ የተደረገው ጥረት፣ የተከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ዛሬም ለፍሬ ሊበቃ ያልቻለበትን ምክንያት ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ ስለምን ትግሉን ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸገር ተሳናቸው? ዛሬም ድረስ የተደራጀ የፖለቲካ ትግልን ተቀላቅሎ ከመታገል ይልቅ በተለየና የራሳችን በሆነ መንገድ አስተዋፆ እናበረክታለን ብለን በተለያየ መስክ ተሰልፈን የምንገኝ ሰዎችም አበርክቶአችን ምን ያህል እንደሆነ ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ጊዜው በተግባር የማይደገፍና የተጠጋገኑ ምክንያቶችን በመደርደር ብቻ ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አይደለም፡፡ የነፃነት ጉዳይ ‹ለነገ…› ተብሎ በይደር የሚቆይ አይደለም፡፡
ሀሳብን አወላግዶ ትርጉም መስጠት ከሀሳብ ነጻነት ሊመደብ አይገባም (ሰመረ አለሙ)
ሰመረ አለሙ
ቀደም ሲል ዳግማዊ ጉዱ ካሳ በሚል ስም ለልጂ ተክሌ የጻፈዉን ከግምት በማስገባት እሱ በጠቃቀሳቸዉ ጉዳዮች ላይ መጠነኛ ግንዛቤ ለመስጠት ብእር መምዘዝ ግድ ብሏል።
በመጀመሪያ ደረጃ ጸሀፊዉ ቋንቋዉ ላይ ያለዉን የበላይነት ለመግለጽ እወዳለሁ (ሃሳቡን አላልኩም ልብ በሉልኝ) ወረድ ብዬ ደግሞ ጽሁፉን በስሱ ሳጠናዉ ጽሁፉ በቀጥታ የተነጣጠረዉ ልጅ ተክሌ ላይ ሁኖ ዶ/ር ብርሀኑን አስመልክቶ ልጂ ተክሌ የዘገበዉ በእጅጉ እንዳበሳጨዉ ከጽሁፉ ለመረዳት ከመቻሉም በላይ የጉዱ ካሳ ጽሁፍ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ላይ የተመዘዘ ሰይፍ ነዉ ተብሎ ቢነገር ለክርክር አይዳርግም የሚልም አመለካከት አለ። ጉዱ ካሳ ዲማቶ ከመዉደቃቸዉ በፊት ዘሎ መሀል ገብቶ የቁርጥ ቀን ወዳጂ መሆኑንም አሳይቷል ለዚህም አድናቆት ይቸረዋል።
ብቻ ሲያመጣዉ አንዴ ነዉ የጉዱ ካሳንና፡የልጂ ተክሌን ጽሁፍ ካነበብን በሗላ ደግሞ በጥሩ ኢትዮጵያዊ አቀራረብ ስለ ዶ/ር ብርሀኑ ሌላዉ እንደ ልጂ ተክሌ አንጀቱ የበገነ አንድ ጽሁፍ አስነበበን። አዎ ዶ/ር ብርሀኑ እና አቶ አንዳርጋቸዉ ሊሸፈኑ የሚችሉ ካለመሆናቸዉም በላይ ሊሸፈቱም ግድ ይላል ሁኔታዉን እስከዛሬ በቅርብም በሩቅም ስንከታተለዉ ነበር። መለሰ ዘራዊ በህይወት ቢኖር እና ቢፈልግ እነዚህን ሰዎች የሚፈልጉትን ሰጥቶ ይመልሳቸዉ ነበር ይጠቅማሉ ብሎ ከገመታቸዉ ይህም ግለሰቦቹ ላይ ካለን ጥላቻ ሳይሆን የህይወት ታሪካቸዉን በሚገባ ከመበርበር የተወረወረ አስተሳስብ ነዉ።
ወደ ጉዱ ካሳ ሌላዉ ክፍል ስንሸጋገር ዶ/ር ብርሀኑ ስለ ዋሂቢሰቶቹ ያላቸዉን አመለካከት አስመለክቶ በመደገፍ “ኢትዮጵያዉስጥ የሸሪያ ህግ ተቋቁሞ ኢትዮጵያ የእስላም አገር ትሆናለች የሚል እብድ ነዉ” የሚለዉን የሀጂ ነጂብን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። እዚህ ላይ ጉዱ ካሳ እስላም ይሁን ሌላ እርግጠኛ ባንሆንም ይህን ማረጋገጫ አምነን ዶ/ር ብርሀኑን እንድናምን የተፈለገበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም። እዉነታዉ ግን ሓጂ ነጂብ በጣም ጥበበኛ እንደኛዉ አገላለጽ ደግሞ ጩሉሌ ብለዉ ሊጠሩ የሚገቡ ሰዉ ናቸዉ። ብዙ ንግግራቸዉን ባለፈዉ አምስት አመት ተከታትለነዋል አንዳንድ ስብሰባቸዉንም ተሳትፈናል። ሐጂ ነጂብ እስላሞች ስብሰባና ሌሎች ስብሰባዎች ላይ የሚያወሩት የተለያየ ሃሳብም ነዉ። የህዋትንም መንግስት እንደዛሬዉ ከመጣላታቸዉ በፊት መንግስታችን ነዉ በማለት ሙሉ ድጋፋቸዉን ሲሰጡ የነበሩም ሰዉ ነበሩ። የሀጂ ነጂብ ሚስት ወ/ሮ ዘይነብ ይባላሉ እሳቸዉ የተናገሩትን ሙሉዉን ቃልም ቀድተነዋል “ኢትዮጵያ የእስላም አገር ትሆናለች ማሺ አላህ; አቶ መለሰ ወደ እስልምና ቢመለሱ ይሻሎታል ኢትዮጵያ በሸሪያ ትተዳደራለች” ይላል ቅንጫቢዉ ከዚህም የባሰ አባባል ታክሎበታል። ወ/ሮ ዘይነብ እና ሀጂ ነጂብ አንድ ሀይማኖት አንድ እምነት አንድ የኢስላም አይዲዮሎጂ የሚጋሩ ባልና ሚስት ናቸዉ በየስብሰባዉም ተከታትለዉ የሚሄዱ ናቸዉ።የሚለያዩት ሐጂ ነጂብ እንዲህ ያለ ቋንቋ የሚናገሩት በእስላሞች ዝግ ስብሰባ ነዉ እነ ጁሀርን የመሳሰሉ ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎችን በክብር ሲጋብዙ።
በጉዱ ካሳ ጽሁፍ አቶ አንዳርጋቸዉ ተደጋግመዉ ተነስተዋል እዉነታዉ ግን አቶ አንዳርጋቸዉ ህወአት ሲደናብር እጅ እና እግር ቀጥለዉለት ነብስ ዘርተዉበት ተሸልመዉ ተሸኝተዉ የሚኖሩ ሌላዉ ጩሉሌ ሰዉ ናቸዉ። አቶ አንዳርጋቸዉ ሕወአት ኢትዮጵያን ሲወርር የፕሮፓጋንዳ ሀላፊ ሁነዉ የሰሩ የህወአት የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸዉ እንዲህ ያለዉ ስልጣን ለትግሬዎችም ቢሆን ለመስጠት ደጋግሞ ማሰብን የሚጠይቅ ነበር ለትግሬዉ ድርጂት። ዶ/ር ብርሀኑን በተመለከተ የህወአት ልዩ አድናቂ ከመሆናቸዉም በላይ ለመለስ፤ ለበረከት ስምኦን ለሰየ አብረሀ ልዩ አመለካከት የነበራቸዉ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵየ በነበሩበት ጊዜ ከፕራይቬታይዜሺን ፕሮግራም ምን ያህል ሊያተርፉ እንደሚችሉ ሲያሰሉ የነበሩ ግለሰብ ናቸዉ። ታዲያ ሁኔታዉ ይህ ሁኖ ሳለ እነ ጉዱ ካሳ በ ኢቫንጀሊካን ሰበካ መንገድ ተጉዘዉ ኢሳትን፤ ከረንት አፌይርስን እና ሌሎች ደካማ የሚዲያ ተቋማትን በመጠቀም ግንቦት 7ን ከምንም በላይ አገዝፎ ለኢትዮጵያ አሳቢ አስመስሎ መሪዎቹ አንዳርጋቸዉ ጽጌና ብርሀኑ ኢትዮጵያን ካለችበት የሚያድኑ አድርገዉ አቅርበዉልናል። ይህ እንዴት ይተገበራል? ቀላል ነዉ ጸረ ኢትዮጵያን ሀይሎችን አስተባብሮ ኢትዮጵያ ላይ መዘመት (ኦነግ፤ኦብነግ፤ሻቢያ፤ግብጽ………………) እንግዲህ እነዚህ ሀይሎች ናቸዉ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የሚችሉት ጎበዝ ተደፍረናል ትዉልዱን እያዩም መቀለጃ አድርገዉናል ቀደም ያለ ጊዜማ ቢሆን እንዲህ ያለ ቀልድ ለ አሳቢዉም ያስፈራ ነበር።
እንደእዉነቱ ከሆነ አንድን የሚዲያ ተቋም ተቆጣጥሮ እንደ ሂትለር ፕሮፓጋንዳ ህዘብን አደንዝዞ አማራጭ አሳጥቶ ህዘብን ዉዥምብር ዉስጥ መጨመር ለአንድ ህዝብ አማራጭ አይሆንም አለፍ ሲልም ወንጀል ይሆናል። ዛሬ ሁኔታዎች ተለዉጠዋል በኢትዮጵያ ስም ተቋቁመዉ ከላይ የተመለከትነዉን አይነት የተወላገደ አስተሳሰብ እኛ ዉሰጥ ፈጥረዉ የራሳቸዉን እቅድ ለሚያሳኩ ዜጎች ወገን ዞር በሉ ብሏል። ይህን ክስረት የተረዱ የዜና ድርጅቶችም ከሉበት ከፖለቲካ አቅዋም እና ትርፍ ሊያመጣልኝ ይችላል ከሚለዉ አመለካከት ተላቀዉ በመጠኑ በራቸዉን ከፍተዋል መሆንም ያለበት ይኸዉ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ጥቃት የሚመለከትን ዜጎች ሁሉ ያገባናል። አለም አቀፍ የፖለቲካ ተልእኮ ያለዉ የዋሃቢስቶች እንቅስቃሴ በማጭበርበር ፖለቲካ ኢትዮጵያዉያንን ሲያምስ ይህ ነገር ሊታሰብበት ይገባል እያልን በጽሁፍም በቃልም ሀሳብ ስናቀርብ ከወያኔ በላይ ወያኔ ተብለን ዉርጅብኝ ቀርቦብናል። ይህ ማንንም አይረዳም እዉነት ከአጀማመሯ ብትቀጥንም በሗላ ግን እየገዘፈች እንደምትሄድ የተፈጥሮ ህግ ያሳያል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህ የአዲሱ እስላም እንቅስቃሴ ያደረገዉን የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ፤ የንብረት ዉድመት፤አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ዜጎችን መግደል ነጻ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ዘግበዉታል ታድያ እነሱን ኪሳራ ዉስጥ የሚከት ሁኔታ ሲፈጠር ወያኔ ነዉ ያደረገዉ የሚለዉ የፌዝ አነጋገር እየተለመደ መጥቷል። እነዚህ ማስረጃዎች ህዝቡ ዘንድ እንዳይደርሱ ቢደረግም፤የኢትዮጵያ ሚዲያዎችን በማጭበርበር እና ግፊት በማድረግ ህዝቡ ዘንድ እንዳይደርስ ጫና ቢደረገም ለሀገራቸዉ በጎ የሚያስቡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ለእይታ አቅርበዉታል አንባቢ በጉግል ከተመለከቱት ከብዙ በጥቂቱ ተመልካቹን የማያሳቅቀዉን ብቻ መርጠን አዉጥተነዋል ቀሪዉን ብርታት እና ጥናቱ ያላችሁ ዜጎች የዚህን ኢሰብአዊ ስራ መመልከት ትችላላችሁ።1. http://www.youtube.com/watch?v=C7EUWDLXok4 ፣ 2. http://www.youtube.com/watch?v=JwKtoBDDwTQ፣ 3. http://www.youtube.com/watch?v=A-ZynRrv0uU፣ 4. http://www.youtube.com/watch?v=QX9gILYFLkg
እዚህ ላይ እነዚህን ሰዎች ኮትኩቶ እዚህ ያደረሳቸዉ የህወአት መንግስት መሆኑን አንባቢ እንዲረዳዉ ያስፈልጋል ሆኖም የህወአት ትግራይ ቢኮተኩታቸዉም አድራጊዎቹ እነሱ በመሆናቸዉ ለዚህ ወንጀል በህብረት ተጠያቂ መሆናቸዉም ሊሰመርበት ይገባል። እዚህ ላይ ታማኝ በየነም ምንም እንኳን ቀደም ባለዉ ጊዜ ለሀገሩ ብዙ ዉለታ የዋለ ዜጋ ቢሆንም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በነ ዶክተር ብርሀኑ ተጋልቦ የኦነግ ወዳጂ ሁኖ ወደ ኢትዮጵያን መንደር የተኮሰዉን ሳናነሳ ልናለፍ አንፍለግም።ይህንን ነገር አስመልከተዉ ታማኝ በየነን አንዳንድ ጥንቃቄና ትምህርት የሚያስፈለገዉን ጉዳይ የዘገቡ ወገኖች (ዲ/ን ሙሉጌታ) በመኖራቸዉ ታማኝ በየነም ከዚህ ይማራል ብለን እንገምታልን ሌሎች ታማኝ በየኖችም ጥንቃቄን ያደርጋሉ ብለን እናምናለን።
ዛሬ ነገሮች ተለዉጠዋል ኢትዮጵያን የሚጎዳ ማንኛዉም አይዲዮሎጅ፤እምነት፤እይታ የሚዲያ ተቋማትን በሞኖፖሊ ይዞ ኢትዮጵያዊነትን የማፈን እንቅስቃሴ ጊዜዉ አልፎበታል ተጎጂዎቹም ከማንም በላይ የሚዲያ ተቋማት እና ይህን የሚያራምዱ ድርጂቶች እና ቡድኖች ይሆናሉ። በጊዚያዊ ጥቅም ተገፋፍተዉ ታላቁን ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያን ማጣት ከጥቅም ጉዳቱ ስለሚያመዝን ቆም ብለዉ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ኪሳራ በብዙ የኢንተርኔት የዉይይት መድረክም ጭምር ተመልክተናል በብዙ መቶዎች ያስተናግዱ የነበሩ በወረደና በጸረ ኢትዮጵያ አቋማቸዉና ተልእኮዋቸዉ ዛሬ ክፍላቸዉን ሬሳ የወጣበት ቤት አስመስሎታል። ህዝቡ የሚፈልገዉን ስለሚያዉቅ ዛሬም ተቋማት በጊዜያዊ የቴርሞ ሜትር መለኪያ ብቻ ሳይወሰኑ የረጅም ጊዜ እይታችሁን መዝኑ እንላለን።
እንግዲህ መባል ያለበት ተብሏል ካጠፋሁም በዚህ ተቆጡኝ semere.alemu@yahoo.com
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሸንጎ በአዲስ አበባ የተጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ ይደግፋል – የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
(A MUST READ) አበበ ገላው ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሰጡት መልስ
በነገራችን ላይ አቶ አበበ ገላው ስለ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ቢጠየቁ የአቶ አንዳርጋቸው አቋምና አገላለጽ ይጋራሉ ወይስ አቶ አበበ ገላው የተጠመቁበት በጥቂቱ AI USA, AI London, HRW, CPJ, State Department, Freedom House ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚሉትን በመጋራት አለቃቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በመቃወም “አቶ ኢሳይያስ የመሰለ የለየለት ነፈሰ ገዳይ፣ አረመኔ፣ ፣ ሰው በላ፣ አንባገነን መሪማ በዚህ ምድር የለም ተፈልጎም አይገኝም።“ በማለት ይገልጽዋቸውና ይሞግቱ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ በእውነቱ ነገር ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ሚዛናዊ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ፣ ገለልተኛና የሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሆነ ሚድያ ማቋቋም ሊጠይቀን ነው።
ሙሉ የጽሑፉ ይዘት ለማንበብ ቀጥሎ የተቀመጠውን ሊንክ ይጫኑ http://salsaywoyane.wordpress.com/
የሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተነገረ! (ድምፃችን ይሰማ)
ድምፃችን ይሰማ
ከሁለት ወራት በፊት በሰው እጅ ሕይወታቸው የጠፋው ሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ በመንግስት ደህንነቶች ታፍኖ ተውስዶ መታሰሩ ተሰማ፡፡ በደሴ አረብ ገንዳ አካባቢ ነዋሪ የነበሩትና መንግስት ለፖለቲካ ጥቅም ሲል ገድሏቸዋል ተብሎ በስፋት የሚታመነው ሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ በመንግስት ደህንነቶች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ አሁን ያለበት ቦታ በውል መታወቅ አልቻለም፡፡ እንደ አከባቢው ምንጮች ከሆነ የሼኽ ኑሩ ልጅ የታሰረው ከአባቱ ግድያ ጋር በተያያዘ ‹‹አባቴን ያስገደለው መንግስት ነው!›› በሚል በዙሪያው ላሉ ሰዎች በመናገሩ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ወጣት ተመሳሳይ እስር ሲያስተናግድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት በፊትም ተመሳሳይ ንግግር በመናገሩ በደህንነቶች ለቀናት ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ማስፈራሪያና ምክር ተለግሶት ተፈቷል፡፡ ሆኖም ከተፈታ በኋላም የመንግስት ደህንነቶች ያስጠነቀቁትን ‹‹ከአሁን በኋላ አባቴን መንግስት አስገድሎታል እንዳትል!›› የሚል ምክር ጥሶ በመገኘቱ ለድጋሚ እስር ተጋልጧል፡፡
መንግስት ከሼኽ ኑሩ ግድ ጋር በተያያዘ ለሳምንታት የዘለቀ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲያካሄድ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ዘመቻ ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ተቋማት መግለጫ በማውጣት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም በበርካታ የገጠር ከተሞች በተሌም በአማራ ክልልና ደቡብ ወሎ ‹‹ሕዝቡ የሼኽ ኑሩን ግድያ እንዲቃወም›› በሚል የግዳጅ ሰልፍ እንዲወጣ ከመደረጉም በላይ ‹‹ግድያውን የፈጸሙት ሙስሊሞች ናቸው›› በሚል ‹‹መንግስት እርምጃ ይውሰድ!›› የሚል መልእክቶች በተከታታይ በመንግስት ሚዲያዎች ሲያሰራጭ ነበር፡፡ ሆኖም ከሼኽ ኑሩ ግድያ ጋር በተያያዘ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ምንም ንክኪ እንደሌለውና ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚያደርገው ተቃውሞ ፈጽሞ ይህን መሰል ጸየፍ ድርጊቶችን የሚስተናግድበት መርህ እንደሌለው በማስረገጥ፤ በዋነኝነትም የእንቅስቃሴው መርህ የሆነው ‹‹የምንሞትለት እንጂ የምንገድልበት አላማ የለንም›› መፈክር ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብም በሃይል እርምጃዎች የማያምንና የሚሰነዘርበትን ዱላ በጸጋ ከመቀበል ውጪም አጸፋ የሰጠበት አጋጣሚ እንደሌለ በአስረጂነት ቀርቧል፡፡
አሁን የት እንደታሰር በውል የማይታወቀውና ከቤተሰብ ጋር እንዳይገኛኝ የታቀበው የሼኽ ኑሩ ወንድ ልጅ የገለጸው ሀሳብ አብዛኛው ህብረተሰብ የሚያምንበትና በተለይም በደሴ ከተማ ሕዝብ ዘንድ ግድያውን መንግስት እንደፈጸመው በስፋት የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በተለያዩ ወቅቶች ከሼኅ ኑሩ ግድያ ጋር በተገናኘ የመንግስት ረጅም እጆች መኖራቸው የሚያመላክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ሼኅ ኑሩ ከመንግስት ሀላፊዎች ጋር በቅርበት ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም በሞታቸው የመጨረሻ ወቅቶች ግን ከአካባቢው አስተዳደር ሀላፊዎችና የጸጥታ ሹሞች ጋር በአካሄድና መርህ ላይ ባለመስማማታቸው ስብሰባ ረግጦ እስከውጣትና ዳግም አብሮ የመስራት ፍላጎት እንደሌላቸውም ሲገልጹ ነበር፡፡ መንግስት ሞታቸውን ተከትሎም የአስከሬን ምርመራ እንዳይደረግና የቀብር ስነ ስርአቱ በአፋጣኝ እንዲፈጸም በማስደረግ የግድያው ሁኔታ ተሸፋፍኖ እንዲቀር ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ የሼህ ኑሩ ግድያ ‹‹በመንግስት የተፈጸመ ድራማ ነው›› ሲል ሕብረተሰቡ ደጋግሞ መግለጹ ይወሳል፡፡
አላሁ አክበር!