Quantcast
Channel: Amharic News & Opinion
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሒሳብና የግንባታው ጥራት በብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች ይመረመራል፤ ምርመራው እንዲዘገይ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ያስተላለፈው ትእዛዝ የከተማውን ምእመናን አስቆጥቷል

$
0
0
  • ምርመራው እስከ ግንባታው ፍጻሜ ታግዶ እንዲቆይ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የጻፈው ደብዳቤ፣ ጥቅመኛ ግለሰቦች በማጭበርበር ያጻፉት እንጂ የፓትርያርኩ ሐሳብ እንዳልኾነ የተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት ከማስጠበቅ ወደ ኋላ እንዳይል በጥብቅ አሳስበዋል
  • የደብሩ ሰበካ ጉባኤ በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ላይ ቁጥጥሩን ማጥበቅ ጀምሯል፤ ሰበካ ጉባኤው በሌለበት የሚካሔድ የገንዘብ ቆጠራ እንደማይኖርና የተቆጠረ ገንዘብ ዕለቱኑ ሞዴል ተቆርጦለት ወደ ባንክ መግባት እንዳለበት የሚያሳስብ ደብዳቤ ዛሬ ለኮሚቴው ተጽፎለታል
  • የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውን በብቸኝነት ከሚቆጣጠሩት ብርሃኔ መሐሪ ጀምሮ ራሳቸውን በቋሚ ሠራተኝነት የተኩትና የሕግ ተጠያቂነት የሚጠብቃቸው ሦስት የኮሚቴው አባላት ለሰበካ ጉባኤው መመሪያ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ቢኖርባቸውም ብርሃኔ መሐሪ ‹‹ሊቀ ጳጳሱን አስነሣለኹ›› የሚል ዛቻ ይዘዋል
  • ‹‹ለቤተ ክርስቲያንና ለሕዝብ ቆሞ ስደት እንኳ ቢመጣ መቀበል ነው፡፡›› /የድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም/

???????????????????????????????በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ገቢና ወጪ እንዲሁም የሕንፃ ግንባታውን ጥራት ብቃቱ በተመሰከረለትና ገለልተኛ በኾነ አማካሪ ድርጅት እንዲመረመር ወሰነ፡፡

የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ውሳኔን ያሳለፈው፣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የገንዘብ ፍሰትና የግንባታ ጥራት ምርመራ እስከ ግንባታው ፍጻሜው ድረስ እንዲዘገይ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በመዝባሪው ብርሃኔ መሐሪና ጥቅመኞቻቸው ሐሰተኛ መረጃ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ያስተላለፈውን ትእዛዝ አስመልክቶ ትላንት፣ ጥር ፲፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ማምሻውን በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ነው፡፡

በውሳኔው መሠረት፣ በውለታ ከተያዘለት ጊዜ በስድስት ዓመታት የዘገየውና ከስምንት ሚልዮን ብር በላይ የምእመናን ገንዘብ የተመዘበረበትን የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሒሳብና የግንባታ ሒደት የሚመረምረው አማካሪ ድርጅት በጨረታ እንደሚለይና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መጀመሩ ተገልጧል፡፡

ሰበካ ጉባኤው በአስቸኳይ ስብሰባው የደረሰበት አቋም ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ያሳለፈው ውሳኔ የሚፈጸምበትና የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቅ/ሲኖዶሱን አቋም በመጋፋት በመዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ በኩል የጻፈውን ምርመራን የማዘግየት ትእዛዝ ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡

የምርመራው ግኝትም በሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ብርሃኔ መሐሪ እየተደፈረ ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት ለማስከበርና የተመዘበረውን የምእመናን ገንዘብ ለማስመለስ ሕጋዊ መሠረት እንደሚኾን በሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ በደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና ሥራው ከተጀመረበት ከጥቅምት ወር ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. አንሥቶ ምዝበራውን እየተከታተለ ሲያጋልጥ በቆየው የምእመናን ተሟጋች ቡድን ታምኖበታል፡፡

His Grace Abune Enbakom Archbishop of Dire Dawa and West Haraghe

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም
የድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ከተካሔደበት ምሽት ቀደም ብሎ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በጻፈው ትእዛዝ ቁጣቸው የተቀሰቀሰና ቁጣው ያስተባበራቸው በርካታ ምእመናን ከድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ጋራ መወያየታቸው ተዘግቧል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ በኩል በልዩ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ ላይ ቅሬታቸውን ሲገልጹ የቆዩት ምእመናኑ፣ የቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ አማሳኝነቱ በተደጋጋሚ በተካሔዱ ኦዲቶች በተጋለጠ መዝባሪ ግለሰብ የተሳሳተ መረጃ ላይ ተመሥርቶ አፈጻጸሙ እንዲዘገይ መታዘዙ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል፤ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መቋጫ እንደሚያገኝ ተስፋ ያደረጉበትን የደብሩን ችግርም የሚያወሳስብ ነው፡፡

ሰበካ ጉባኤው ማስፈጸም የሚገባው የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ መኾን እንዳለበት ያሳሰቡት ምእመናኑ፣ በሁለተኛ የምርጫ ዘመኑ ላይ የሚገኘው ሰበካ ጉባኤ ውሳኔውን በማስተግበር የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት የማያስከብርና የምእመናንን ገንዘብ የማያስጠብቅ ካልኾነ በአዲስ ምርጫ ወደሚተኩበት ርምጃ እንደሚቀጥሉ በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢና ወጪ፣ የግንባታው ጥራት በብቁና ገለልተኛ ባለሞያዎች እንዲመረመር የተላለፈውን የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚያግድ ደብዳቤ ማምጣት በራሱ ችግር እንዳለ እንደሚያሳይ የገለጹት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በበኩላቸው፣ ‹‹ኦዲት ይደረግ፤ ነጻ እናውጣችኹ ሲባል ይደረግ ይሉ ነበር፤›› ካሉ በኋላ ደብዳቤው የተጻፈው በጥቅም በተሳሰሩ ግለሰቦች የተንኰል አካሔድ እንጂ በሙስና ላይ ጠንካራ አቋም እንዳላቸው የሚያምኑባቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ጉዳይ ላይ ሁለት ተፃራሪ ውሳኔዎችን ማስተናገድ እንደማይችሉ ብፁዕነታቸው ገልጸው ለቤተ ክርስቲያንና ለሕዝብ ቆሞ የሚመጣውን መከራ መቀበልን እንደሚመርጡ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ለቤተ ክርስቲያንና ለሕዝብ ቆሞ ስደት እንኳ ቢመጣ መቀበል ነው፤ ደግሞም አብረን ነው የምንሰደደው›› በማለት የመከሩት ብፁዕነታቸው፣ በመጨረሻ የሰጡት መመሪያ ሰበካ ጉባኤው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚያስፈጽምበትን መነሻ እንዲያቀርብ ነበር፡፡

በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔና ብፁዕነታቸው መመሪያ መሠረት ሰበካ ጉባኤው ማምሻውን ለአስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ ምርመራው በብቁና ገለልተኛ በኾነ አማካሪ ድርጅት እንዲካሔድ የጋራ አቋም ወስዶ ለሀ/ስብከቱ አስታውቋል፡፡ ብፁዕነታቸው የቃለ ዐዋዲውን አንቀጽ ፳፱ ድንጋጌ በማስታወስ በሰጡት የሥራ መመሪያ፣ ለሰበካ ጉባኤው ተጠሪ የኾነው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ከደብሩ አስተዳደር ለሚተላለፍለት መመሪያ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት ሲኾን አስተዳደሩም አካሔዱን ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በግልባጭ ያስታውቃል፡፡

ዘግይቶ እንደተሰማው፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር አገልግሎት፣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የኦዲት ምርመራ የሕንፃ ሥራው እየተካሔደ ጎን ለጎን መከናወን እንደሚችል በመግለጽ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ለሀ/ስብከቱ ያስተላለፈው እስከ ግንባታው ፍጻሜ  የማዘግየት ትእዛዝ እንዲስተካከል ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ደብዳቤ ጽፏል፡፡

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ሓላፊ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት በ፳፻፫ ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ላይ ያካሔደውና በ47 ገጾች የተጠናቀረው የኦዲት ምርመራ ሪፖርት እንዳረጋገጠው፣ ከብር 1.8 ሚልዮን በላይ (1‚864‚372.33) ብር ከደንብና መመሪያ ውጭ ለተቋራጭ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

ከመዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ጋራ ባለመግባባት ራሳቸውን ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ባገለሉ ሐቀኛ ምእመናን ጥያቄና በወቅቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፈቃድ የተካሔደው በዚኹ የኦዲት ምርመራ፣ ከደንብና መመሪያ ውጭ ለተቋራጩ የተከፈለው ብር 1‚864‚372.33 የአፈጻጸም ሕጋዊነት በአስቸኳይ እንዲስተካከልም ለሀ/ስብከቱ ጽ/ቤትና ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ የማስፈጸም ሓላፊነት ተሰጥቶ ነበር፡፡

የማስተካከያ ርምጃውን ለመውሰድና የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ የሚጠይቀውን ቀሪ የገንዘብና ጊዜ መጠን ተጥንቶ እንዲቀርብ ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ የነበረ ሲኾን ይህም እስኪከናወን ድረስ በቀድሞው ዐይነት አሠራር ምንም ዐይነት አዲስ ክፍያ ለተቋራጩ እንዳይፈጸም ተወስኖም ነበር፡፡

ግና ምን ያደርጋል፤ የአንድ ሰው ዘርፍ ከኾነው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምሕንድስና አገልግሎት ጋራ በጥቅም የተሳሰረውና ራሱን ለሰበካ ጉባኤው ሳይኾን ለቀድሞው ፓትርያርክ ተጠሪ ያደረገው የመዝባሪው ብርሃኔ መሐሪ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የ1.8 ሚልዮን ብሩን ክፍያ ከደንብና መመሪያ ውጭ የፈጸመው በቀድሞው ፓትርያርክ ቀጥተኛ ትእዛዝ መኾኑን በመግለጽ ሪፖርቱ እንዲስተካከልለት እስከማስገደድ ደርሶ አመከነው እንጂ፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቁጥጥር አገልግሎት ኦዲት ልኡክ የተጠቀሰውን ምርመራ ከማከናወኑ ከወራት በፊት ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ተገንጥለው የወጡ ስድስት አባላትን ጨምሮ በከተማው ምእመናን ዘንድ መልካም ስም ያላቸው 10 አባላት ያሉት የተሟጋቾች ቡድን የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ባካሔደው ኦዲት፡-

  • የሒሳብ ምርመራው እስከተደረገበት ግንቦት ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ድረስ በውጭና በሀገር ውስጥ ከሚኖሩ ምእመናን የተሰበሰበው ብር 11‚388‚096.23 መኾኑን አረጋግጧል፤
  • ተቋራጩ ውል በተገባበት በመስከረም ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ተጨማሪ ዕሴት ታክስን ጨምሮ በ2‚984‚562.51 ወጪ በሁለት ዓመት ጊዜ ተጠናቅቆ በ፳፻ ዓ.ም. ማስረከብ የነበረበት ቢኾንም ከውለታው ውጭ የኾኑ የይገባኛል ጥያቄዎችን በማንሣትና ከሥራ ተቋራጭ የሚጠበቀውን የውል ግዴታ ሳይወጣ ደብሩን ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎት ቆይቷል፤
  • የሒሳብ ምርመራው እስከተካሔደበት ጊዜ ድረስ አሳማኝ በኾነም ባልኾነም መንገድ በደረሰኝ የወጣው ወጪ 5 ሚልዮን ብር ሲኾን ይህ ስሌት ጠቅላላ ገቢ ከኾነው 11.8 ሚልዮን አንጻር ከ5 ሚልዮን ብር በላይ ለምዝበራ መጋለጡን አሳይቷል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13695

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>