በአንድ ጫካ ውስጥ አንድ ከሺ ዓመታት በላይ እድሜ የጠገበ ዋርካ ነበረ፡፡ ዋርካው እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ታላቅ ነው፡፡ በላዩ ላይ አዕዋፍ፣ በሥሩም እንስሳት ይጠለሉ ነበር፡፡ ከፊሉ ፍሬውን ከፊሉም ቅጠሉን ይመገባሉ፡፡ ሌሎቹም ግንዱንና ሥሩን ፍቀው ይበላሉ፡፡ አንዳቸው ለሌላቸው እንስሳትና አዕዋፍ የጠቀሙበት፣ አንዳቸውም አንዳቸውን የበሉበት ዘመን ነበር፡፡ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የሚጋቡበት፣ አንዳቸውም ከሌላቸው ጋር የሚዋጉበት ዘመን አለ፡፡ ፈረስና አሞራ ተጋብቶ ክንፍ ያለው ፈረስ ተወልዶ ነበር አሉ፡፡ ታላላቆቹ እንስሳት በልተዋቸው ዘራቸው የጠፉ እንስሳትም አሉ፡፡
እነዚህ እንስሳት አለመግባባታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ አንዳንዶቹ ወፍነት፣ አንበሳነት፣ ዝሆንነት፣ ድመትነት የሚባል ማንነት እንጂ እንስሳነት የሚባል ማንነት የለም ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንስሳነት የሚባል ማንነት እንጂ ወፍነት ወይም በግነት፣ ፍየልነት ወይም ጦጣነት የሚባል ማንነት የለም ብለዋል፡፡ ከዚህ የተረፉት ደግሞ ሁለቱም አለ ይላሉ፡፤ እስካሁን ግን በአንዱም አልተስማሙም፡፡
ከዋርካው ሥር የሚያርፉት እንስሳት የዋርካው ቅርንጫፎች መቆረጥ አለባቸው የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ ለምን? ሲባሉ እነዚህ ጨቋኝ አዕዋፍ በኛ ላይ ሲዘባነኑ፣ ኩሳቸውን ሲጥሉ፣ ከዚያም አልፈው ከላይ ሆነው እኛን ሲረግጡ የነበረው በቅርንጫፉ ላይ ሆነው ነው፤ የቅርንጫፉ መኖር ግፍና መከራውን፣ ጭቆናና ስቃዩን ስለሚያስታውሰን መቆረጥ አለበት ባይ ናቸው፡፡
ሌሎቹ ደግሞ በዋርካው ሥር ላይ ቂምና ትችት አላቸው፡፡ ይኼ ዋርካ አንድ ቦታ ተተክሎ የቀረው፣ ከመስፋትና ከመደርጀት አልፎ ተራማጅ ያልሆነው፣ ሥሩ ከምድር ጋር ተክሎ ስለተያያዘ ነው፡፡ ሥሩ ባይዘው ኖሮ ስንፈልግ አውሮፓ ወስደን የበረዶ ዛፍ፣ ስንፈልግ ካልሃሪ ወስደን የበረሃ ዛፍ ማድረግ እንችል ነበር፡፡ ሥሩ ቸክሎታል፡፡ ስለዚህ ሥሩ መነቀል አለበት ይላሉ፡፡
ሦስተኛዎቹ ወገኖችም እኛ ስለቅጠሉ እንጂ ስለ ፍሬው የሚያገባን ነገር የለም ብለዋል፡፡ እነዚህ ቅጠል በል የሆኑት እንስሳት በዋርካው ላይ ብቅ የሚሉትን ቅጠሎች ሁሉ እየቀነጠቡ ለመጨረስ በሩጫ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህን ወገኖች ፍሬ በል የሆኑ እንስሳት ተቃውመዋቸዋል፡፡ ቅጠሉ ከሌለ ፍሬው አይገኝም፡፡ ዋካው እንዲያፈራ ቅጠሉን ተውለት የሚል ክርክር አላቸው፡፡ እነዚያኞቹ ግን ስለ እናንተ የማሰብ ግዴታ የለብንም፡፡ እኛ ማሰብ የሚጠበቅብን ስለ ቅጠሉ ብቻ ነው ብለው ዘግተዋል፡፡
እነዚህ ቅጠል በል እንስሳት ስለ ሌላው የዋርካው ክፍል አይመለከተንም ባይ ናቸው፡፡ ለእኛ ጉዳዩ የቅጠል ጉዳይ እንጂ የዋርካ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ብለው ቅጠሎችን በሚያማምሩ ባለ ቀለም ላስቲኮች ሸፈኗቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ የዋርካውን ሕይወት ማሳጠር ብቻ ሳይሆን የሌሎችን እንስሳት የመኖር ሕልውናም አደጋ ላይ ጣለው፡፡ ቅጠሉ ከተሸፈነ ይወይባል፣ አየርና ፀሐይ ወስዶ ለዋርካው ምግብ የሚሠራም አይኖርም፡፡ ዋርካውም ሕይወቱ በጭንቅ ሆነ፡፡ ቅጠል በሎቹ ለቅጠሎች የሠሩት ጌጥ እንደ መቃብር ላይ ጌጥ ሆነ፡፡
ሌሎች ደግሞ መጡ፡፡ ይህንን ዛፍ ዋርካ ብለን መጥራት፣ ግንዱንም፣ ቅርንጫፉንም፣ ቅርፊቱንም፣ ቅጠሉንም፣ ፍሬውንም በአንድ ዋርካ ስም መጥራት የለብንም አሉ፡፡ የዚህ ዋርካ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተወሰኑ ዘመናት በፊት ቅርንጫፎቹ እንደዚህ አልበዙም ነበር፣ ከመቶ ዓመታት በፊት እነዚህን ሥሮች አልሰደደም ነበር፣ ከሺ ዓመት በፊት ደግሞ በዚህ ውፍረት መጠን አልነበረም፡፡ አሁን በዚህ መጠን ስናገኘው ዋርካ አልነው እንጂ በየጊዜው ሌላ ስም ነበረው፡፡ ችግኝ ነበረ፣ ቁጥቋጦ ነበረ፣ ዛፍ ነበር፣ ሌላም ነበረ፡፡ ይህንን ሁሉ ታሪክ ዋርካ ብለን መጥራት የለብንም ይላሉ፡፡ ዋርካው ችግኝ እያለ፣ ቁጥቋጦ እያለ፣ ዛፍ እያለ የሠራው ነገር አይመለከተንም ባይ ናቸው፡፡
ክርክሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ሀብት ማለት ጥቅም ነው፡፡ አንዳች ግላዊ ጥቅም የማታገኝበት ሀብት ያንተ አይደለም ማለት ነው የሚሉ ደግሞ ተነሡ፡፡ እነዚህ ዋርካው በዝቷል፣ ሰፍቷል፤ ስለዚህ ከቅርንጫፉም፣ ከጎንና ጎኑም እየፈለጥን በመሸጥ መጠቀም አለብን ይላሉ፡፡ ዋርካው በሥሮቹ አማካኝነት የሚስበውን ውኃና አፈር ለጎረቤት ዛፎች እየሸጥን መጠቀም አለብን የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ የዚህ ተቃዋሚዎች ደግሞ ዛፉ የሚስበው ውኃና አፈር ለቅርንጫፎቹ አልበቃ ብሎ ቅጠሎቹ ደርቀው፣ እንጨቶቹ ጠውልገው እየታዩ እንዴት ለሌላ እንሰጣለን፡፡ የራሳችን እያረረብን እንዴት የሰው እናማስላለን፣ ራሷ ሳትጠና ልታቋቁም ሄደች የተባለው ሊደርስብን አይደለም ወይ ይላሉ፡፡
የዋርካው ግንድ ተገቢ ቦታ አልተሰጠውም የሚሉም አሉ፡፡ ሥሩንና ቅርንጫፉን የሚያገናኘው፣ ዋርካውንም የተሸከመው ግንዱ ሆኖ እያለ የሚደነቀውና የሚመሰገነው ግን ቅርንጫፉ ነው፡፡ አበባ የሚያወጣውና የሚለመልመው ቅርንጫፉ ነው፡፡ የሚንዠረገገውና ግራ ቀኝ የሚሰፋው ቅርንጫፉ ነው፤ ለምን? ብለው ይጠይቃሉ፡፡
አንዳንዶቹ በዛፉ ሥር የተጠለሉ እንስሳት የወፎቹን ድምጽ መስማት እንፈልግም እያሉ ነው፡፡ ሌሊት ሌሊት ተነሥተው ከዕንቅልፍ ለምን ይቀሰቅሱናል፡፡ ለምን አንተኛበትም? ደግሞም ዜማቸው ከጥንት እስካሁን ተመሳሳይ ነው፡፡ አዲስ የወፍ ዜማ አልመጣም፤ በቃ፤ ወይ ድምጻቸውን ይቀንሱ አለበለዚያም የጠዋት ዝማሬያቸውን ያቁሙ እያሉ ነው፡፡ ወፎቹም በበኩላቸው እነዚህ አራዊት ምድርና ሰማዩን እያደባለቁ የሚለቁትን ግሳት ወይ ይቀንሱ ወይም ያቁሙ ብለው ይከራከራሉ፡፡
ሁሉም በየራሱ ብቻ ነው የሚሰባሰበው፡፡ ግንዱን የሚመገቡት ‹የግንድ ሰንበቴ› አላቸው፣ ቅርንጫፉን የሚበሉት ‹የቅርንጫፍ ማኅበር› መሥርተዋል፤ ሥሩ ላይ ያሉት ‹ሥር ጽዋ› አቋቁመዋል፣ አሁን ግራ የገባቸው እንደ ዝንጀሮና ጦጣ ከላይም ከታችም የሚሆኑት እንስሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ቅርንጫፉም ላይ መሬቱም ላይ የሚኖሩ እንስሳት ምን ዓይነት ማኅበር ማቋቋም እንዳለባቸው ተቸግረዋል፡፡
በአንድ ወቅት አንድ ዘንዶ መጥቶ በዋርካው ሥርና ቅርንጫፍ ላይ በነበሩት እንስሳት ላይ አደጋ አድርሶ ነበር፡፡ በዚያ አደጋ ምክንያትም ብዙ እንስሳት ተሰድደው ወደ ሌሎች ዋርካዎች ሄደዋል፡፡ እነዚህ የተሰደዱ የዋርካው እንስሳት በዋርካው ዙሪያ ካሉት እንስሳት ጋር አንዳንድ ጊዜ አይስማሙም፡፡ የዋርካው እንስሳት እዚያ ማዶ ሆኖ ከመጮህ ጎበዝ ከሆናችሁ እዚህ አትመጡም? ይሏቸዋል፡፡ የተሰደዱት እንስሳትም ‹‹ወኔ የሌላችሁ፣ ድፍረት ያጣችሁ፣ ፈሪዎች›› ብለው ይመልሳሉ፡፡
ዋርካው አሁንም አለ፡፡ እየተፈለጠም እየተቆረጠም ቀጥሏል፡፡ በላዩና በታቹ ያሉት እንስሳት ግን የሚያስማማቸው ነገር አላገኙም፡፡ እስካሁን የተስማሙበት ነገር ቢኖር በዛፉ ላይ በመኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ሚዲያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደቀረበ ሰው፣ ሁሉም የራሱን ድምፅ ብቻ ነው መስማት የሚወደው፡፡ የሚፈልጥ ሊፈልጥ፣ የሚቆርጥ ሊቆርጥ፣ የሚልጥ ሊልጥ፣ የሚከልል ሊከልል፣ የሚለቅም ሊለቅም፣ የሚንጥ ሊንጥ፣ የሚቀነጥስ ሊቀነጥስ፣ የሚነቅል ሊነቅል፣ ሁሉም በየወገኑ ተዘጋጅቷል፡፡ ዋርካው ዋርካ ሆኖ እንዳለ እንዲቀጥል ማን ያትርፈው?
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው