——
በአዲስ አበባ የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ኦፊሰር መሆናቸውን ለስድስት በተዳበሏት ቢሮ ውስጥ በምትገኝ ጠረጴዛ ጠርዝ ላይ የተቀመጠች ማስታወቂያ ትመሰክራለች፡፡ ግለሰቡ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ይባላሉ፡፡የተዳከመ ገጽታ ተላብሰው ያደረጓትን ነጠላ ጫማ በእግራቸው እያጫወቱ እንግዶችን ይቀበላሉ፡፡ሲናገሩ እጅግ በጣም በዝግታ በመሆኑም የሚሉትን ለመስማት ጆሮን ፈገግታ ወደ ተለየው ፊታቸው ማስጠጋት ግድ ይላል፡፡
ከፊታቸው የቀረበላቸውን ወረቀት እየተመለከቱ ‹‹ ተነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን ››አሉ፡፡ ምን መነጋገር ያስፈልጋል ለሳምንታት ፊትዎ ለቀረበ ወረቀት መልስ ለመስጠት እንደገና ቀጠሮ ምንድን ነው ?‹‹ልክ ነው፡፡ነገር ግን የምወስነው እኔ አይደለሁም፡፡››
ማን ነው የሚወስነው?››ጥያቄው መልሳቸውን ተሸቀዳድሞ ቀረበላቸው ‹‹እያወቃችሁት ለምን ትጠይቁኛላችሁ ?››፡
የማርቆስ ቢሮ ሀሳቡን በሰላማዊ ሰልፍ አልያም በህዝባዊ ስብሰባ ለመግለጽ የፈለገ ፓርቲን ወይም ሌላ አካልን ጥያቄ በመቀበል እንዲያስተናግድ በአዋጅ ስልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመ ነው፡፡
ግን ኦፊሰሩ የሚመሩት ከመጋረጃው ጀርባ ራሱን ደብቆ አገሪቱን በሚመራ አካል ነው። ኦፊሰሩ ግን ለሚቀርብላቸው ጥያቄ መልስ መስጠት አይችሉም ። ከሰውዬው ጀርባ ያሉ ሀይሎች የወሰኑትን ውሳኔ ማርቆስ ፊርማና ማህተማቸውን በማኖር ያስተላልፋሉ፡፡እርሳቸው የተፈለጉት ለፊርማ ብቻ ነው፡፡
ችግሩ ያለው ማርቆስ ቢሮ ብቻ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ከቀበሌ አንስቶ በየደረጃው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ብትሄዱ የምታገኙት ተቋም አልባ መሆናችንን ነው፡፡ ጉዳዮች የሚፈጸሙት በስልክ ነው፡፡ማርቆስ ይህንኑ ሐቅ እያላቸውም ቢሆን በማመን‹‹ስልክ ተደውሎ ለአንድነቶች እውቅናውን እንዳትሰጡ ተብያለሁ፡፡ ይህንን የከንቲባው ጽህፈት ቤት ሐላፊም አቶ አሰግድ ያውቃሉ›› ብለዋል፡፡
አቶ አሰግድ በበኩላቸው ‹‹ማን እንዳዘዘው አላውቅም ተደውሎለት ከሆነም ዛሬ አነጋግሬው ነገ ምላሹን እሰጣችኋለሁ››የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አሰግድ የከንቲባው ጸሀፊ ቢሆኑም ስለሚመሩት ተቋም አልቀኑም፡፡ተቋሙ በተሰጠው ስልጣን በተቀመጠለት ደንብ መሰረት መስራት እንደሚገባው በመገንዘብ በስልክ የምንመራ አይደለንም በማለት ይቆጣሉ ብዬ ስጠብቅ‹‹ማን እንደደወለለት አጣራለሁ››ብለውን አረፉት፡፡